ያን አዳራሽ፣ ያንቀለም፣ ያን ያልሞላ ቤት ወንበር አውቀዋለሁ። ስንት ጊዜ አፍጥጨበታለሁ። አንዳች ነገር አገኝበት ይመስል ድል ቀላውጫለሁ። እና አሁንም ….የነሱን ዓይን ዓይን እያየን ፣ አስላለፍ እየቃኘን… የወረት ድል እየተመኘን፣ የፖለቲካ ጥልፍልፍ ጨዋታን እየዳኘን…. ቀረን አልኩ።
አሁኑም እነሱን ከነሱ እየጠበቅን፣ ተስፋ እየቆመርን፣ መርዝን ከመርዝ እየቀመምን አለነው። ከጅብና ቀበሮ ይልቅ የጊንጥና የቀበሮ ህብረት ይሻለናል…. እንዳልን… ከኢህአዴጎቹ ቆንጆ እንደመረጥን… በድክመትና አልጫነታችን… በወረትና አጫብጫቢነታችን እያላገጥን አጨብጭበን ቀረን። ለማንኛውም… ደህና ደህና ስድቦችን ውግዘትና ትችቶቻችንን አለመጣል ነው። ነገ ያስፈልጉናል – ሪሳይክል እናደርጋቸዋለን።
ጊዜው አልፏል ወይም አልፎባቸዋል ብለን ራሳችንን አለመሸነግል ነው። ነገ እሚያምረንን አናውቀም። አይረባም ብለን ከቆሻሻ መጣያው የጣልነው ያምረናል። ይጣፍጣል ብለን ከገበታው ያኖርነው ያቅረናል። ስሜትና ጣዕማችን መችና እንዴት እንደሚለወጥ አናውቀውም። እና ለኦህዴድም፣ ለህወሓትም፣ ለብአዴንም የተጠቀምነው ፤ ከዚህ በፊት የተናገርነው የተቸነው ሁሉ ይጠቅማልና አለመጣል ነው። ሰዎቹ እንደሁ ጥንድም ነጠላም እየሆኑ ይዟዟሩ ይሆናል። መቸም እኛም እየተዟዟርን ሁሉንም ሰድበናል ሁሉንም አመስግነናልና ካሁን በኋላ እጣችን እነሱኑ ማዟዟር ብቻ ሊሆን ይችላል። ግን እባካችሁ ፣ ፖለቲካ እኮ እንደዚህ ነው፣ ጨዋታው እንዲህ ነው… እያላችሁ አትሸንግሉኝ… የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነውም አትበሉኝ።
ጠላትም ወዳጅም የለንም ሁላችንም እኛው ነን። እነሱም እነሱ ናቸው። እኛም በብርሃን ፍጥነት ጠብና ፍቅራችንን ቀያይረን መግለጽ እምንችል ድንቅ ሰዎች ነን። ፍሬ ነገሩ ግን ይህ ነው፣የተነጋገሩትን ሳይነግሩን እነሱ ግን ተነጋግረው በየወንዙም ቢሆን ተማምለው አብረው ሄዱ። ጥንካሬያቸው አብሮነታቸው ነው። የተለያዩ ሆነው አንድ ናቸው። እኛ አንድ ነን እያልን እልፍን ነን። ተዘላልፈውም እንዳይሆኑም ተደራርገው ሲያልቅ ግን አብረው ናቸው። ጠባቸውን ፍቅር አድርገው ይወጣሉ።
እኛ ግን እንወዳቸዋለን እምንላቸው ተቃዋሚዎቻችንን የገቡበት እየገባን ስናሳድድ እንውላለን። ሞተው እንኳ አንምራቸውም። አገር ታይቶ ኢህአዴግ ይሰጠዋል ብሏል ሌኒን። አብይን የሰጠን ኢህአዴግ ነገ ደግሞ….አይይ ረሱት መሰል ማን እንደሆነ ሳይነግሩን ሄዱ። ደህና ዋሉ!