የዛሬ ሐሙስ ዐበይት ዜናዎች- ከዋዜማ

የዛሬ ሐሙስ ዐበይት ዜናዎች- ከዋዜማ

1. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ያቀረቡለትን 3 ሹመቶች አጽድቋል፡፡ የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው ለሳምንታት ክፍት ለቆየው ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ተሹመዋል፡፡ የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ደሞ መከላከያ ሚንስትር ሆነዋል፡፡ ዐመት ሳይሞላቸው ከመከላከያ ሚንስትርነታቸው የተነሱት አይሻ መሐመድ ወደ ቀድሞ መስሪያ ቤታቸው እና በአዴፓው ጃንጥራር አባይ ተይዞ ወደነበረው ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ተዛውረዋል፡፡ ሹመቶቹ የጸደቁት በ1 ተቃውሞና በ5 ድምጸ ተዓቅቦ ነው፡፡ ገዱ በቃለ መኻላ ስነ ሥርዓቱ ላይ አልተገኙም፡፡

2. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰሞኑን መንግሥት ድጋፍ እንዲያድርግለት ለመጠየቅ መዘጋጀቱን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት ግን የካፒታል ድጋፉን የሚለቀው ባንኩ የወሰዳቸውን ማሻሻያዎች አጥጋቢ ከሆኑ ብቻ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከሦስት ዐመት በፊት መንግሥት ለባንኩ ማገገሚያ የ2.5 ቢሊዮን ብር ድጎማ ቢሰጠውም ብዙም መሻሻል አላሰየም፡፡ ባንኩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ብድሮችን ማስመለስ ባለመቻሉ ሕልውናው አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሲሆን አጠቃላይ ካበደረው 46 ቢሊዮን ብር 40 በመቶው የተበላሸ ብድር እንደሆነ ራሱ አምኗል፡፡

3. የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) ሽመልስ አብዲሳን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መሾሙን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ ሽመልስ የምክር ቤቱ አባል ስላልሆኑ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ በለማ መገርሳ ተይዞ የቆየውን ርዕሰ መስተዳድርነት ደርበው ይይዛሉ፡፡ ሽመልስ እስከዛሬ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የነበሩ ሲሆን ቀደም ሲል በክልሉ የከተማ ቤቶችና ልማት ቢሮና በሌሎች ሃላፊነቶች ሰርተዋል፡፡

4. ኦዴፓ የማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊውን አለሙ ስሜን (ዶ/ር) አንስቶ በምትካቸው የድርጅቱ ገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ሃላፊውን አዲሱ አረጋን መመደቡን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ አዲሱ እስከዛሬው ሹመታቸው ድረስ የኦዴፓ ገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ሃላፊ ነበሩ፡፡ ቀደም ሲልም የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡

5. የአማራና ቅማንት ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር ያለመ ጉባዔ ዛሬ ተካሂዷል፡፡ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን ተገኝተዋል፡፡ ለጉባዔው ከክልል፣ ወረዳዎች፣ ዞኖች፣ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ከሐይማኖት ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡ ዕርቀ ሰላሙም በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡

6. የኦጋዴን ብሄራዊ አርነት ግንባር (ኦብነግ) በሱማሌ ክልል ቀብሪደሃር ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ እያካሄደ መሆኑን በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ በስብሰባው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር ተገኝተውለታል፡፡ ሕዝባዊ መድረኩ ኦብነግ ወደ ሰላማዊ ትግል ከተመለሰ ወዲህ በክልሉ ሊያካሂዳቸው ያቀዳቸው ተከታታይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች አካል ነው፡፡

7. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ቻይና ያቀናሉ፡፡ የጉዟቸው ዐላማ Belt & Road Forum for International Cooperation በተሰኘው ሁለተኛው የቻይና ዐለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ መድረክ ላይ ለመሳተፍ መሆኑን ፎርቹን አስነብቧል፡፡ በጉባዔው 40 የሀገራት መሪዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡ ጉባዔው “Belt and Road Cooperation: Shaping a Brighter Shared Future በሚል መሪ ቃል እኤአ ከሚያዚያ 26 እስከ 27 ይካሄዳል፡፡

LEAVE A REPLY