ይህን ወቅታዊ ሃተታየን በመፍትሄው ልጀምር። ጥንታዊዋንና ባለ ታሪኳን ኢትዮጵያን ከብሄር ተኮር እልቂት፤ ከድህነት፤ ከፍልሰት፤ ከስደት፤ ከጥገኝነትና ከኋላ ቀርነት ኡደት ራሷን እንደ አንዲት አገር እና ሕዝቧን እንደተባበረ ሕብረ-ብሄራዊሕዝብ ነጻ ለማውጣት ከተፈለፈገ፤ ዘረኝነት፤ ጠባብ ብሄርተኝነት፤ የብሄር ትምክኸተኛነት፤ ጽንፈኛነት፤ “የኔ ብቻ” ባይነትና ብሄር ተኮር እልቂት መቀረፍ አለበት። አለያ፤ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት አይቻልም።
በዚህ ሃተታየ የምከራከረው ብሄር ተኮሩ ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ለሰላምና ለእርጋታ፤ ለፍትሃዊና ለዘላቂ እድገት ጸርና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው የሚል ነው። ይህን ዛሬ እነደ አዲስ ክስተት እየታየ ብዙ የሚተችበትን ጽንሰ ሃሳብ በመረጃዎች ተደግፌ ለኢትዮጵያዊያን ያቀረብኩት ዓለም ባንክ በአማካሪነት ስሰራ በነበረበት ወቅት በ 2010 በታተመው፤ Waves:- Endemic Poverty that Globalization Can’t Tackle but Ethiopians Can በተባለው መጽሃፌ ነው።
“Government policy mistakes generations will cite” በሚለው ምእራፍ የሚከተሉትን አምስት የህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት አገር አጥፊና ሕዝብ አድካሜ የአመራር ስህተቶች አቅርቤ ነበር። እነዚህም፤
- ኢትዮጵያ የባህር በሮቿን ማጣቷ ለኢኮኖሚዋና ለደህንነቷ አደገኛ መሆኑ፤
- መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት በዘውግ ማዋቀራቸውና የክልል አስተዳደር ተቋማዊ ማድረጋቸው የተደበቀ ቦምብ፤ እልቂትንና ግጭትን የሚያስከትል መሆኑ፤
- መለስ ዜናዊ የተከተለው “አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግሥት” ገቢን፤ ሃብትንና የበላይነትን የሚያጠናክረው ለገዥው ፓርቲ፤ ለታማኝ ግለሠቦች፤ ለዘውግ ልሂቃን፤ ለመንግሥትና ለፓርቲ ባለሥልጣናት መሆኑ፤
ከላይ ከሶስተኛው ፖሊሲ ጋር አብሮ የሚሄደው ተጨማሪ ክስተት፤ በየጊዜው ምርጫዎች ይካሄዱ ሲባል አሸናፊው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ መሆኑ፤ ጠንካራና የተባበረ ብሄራዊ “ተፎካካሪ ፓርቲ” አለመኖሩ የኢህአዴግን አሸናፊነት አስቀድሞ ለማወቅ የሚቻል መሆኑ፤
በአሁኑ ሁኔታ የምጨምረው ህወሓት በኦዴፓ ቢተካም ባይተካም መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የማይቻል መሆኑ፤
- አንቀጽ 39 እስካልተነሳ ድረስ የዘውግ ፓርቲዎችና ልሂቃን ታማኝነትና ተገዢነታቸው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ሳይሆን ለራሳቸው የዘውግ ፓርቲና ለዘውጋቸው መሆኑ። ይህ የተከፋፈለ ታማኝነት ( Divided loyalty to the ethnic party or ethnicity you belong to rather than to the Ethiopia and all Ethiopians) ያስከተለው እልቂት፤ ግፍና በደል በየትም አገር ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ መሆኑ፤
- ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት የዓለምን ሕዝብ ለማባበልና የውጭ ምንዛሬ ድጋፍን ለማግኘት በሚያስችል ስልት፤ ገዥው ፓርቲ “የሰብአዊ መብቶችን አክብሮ፤ የዘውጎችን እኩልነት አጠናክሮ፤ የሕግ የበላይነትን ተቀብሎ፤ መድብለ ፓርቲነትና ፉክክር እንዲካሄድ አድርጎ” ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ተምሳሌት አደርጋለሁ የሚል የማጭበረበሪያና የማባበያ ዘዴዎችን መጠቀሙን እና፤
ደርግ ያወጀውን የመሬት አዋጅ ለህወሓትና ለተባባሪዎች የዘውግ ፓርቲዎች በሚጠቅም መንገድ በብዙ ሚሊየን ሄክታር የሚገመመት ለም መሬትና ወንዝ ለምርጥ የአገር ውስጥ ኢንቬስተሮች፤ ከሰላሳ ስድስት አገሮች ለመጡ የውጭ ኢንቬስተሮች፤ ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በዝቅተኛ ዋጋ መሸጡ አደገኛ መሆኑ፤ በተለይ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች፤ ዘላኖች፤ ለተራው ኢትዮጵያዊ የከተሜ ሸማች የመሬት እጥረትና የዋጋ ግሽበት የሚያስከትሉ መሆናቸው በመረጃ ቀርበው ነበር።
በወቅቱ መጽሃፉን ያነበቡት ግለሰቦች ሁሉ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በገፍ ወደ አገር ቤት እንዲሰራጭ መክረውኝ ነበር። አልተቻለም፤ ህወሓት አይፈቅድም ነበር። መጽሃፉ ከተጻፈ ክዘጠኝ ዓመት በኋላ ዛሬም የማጠናክረው መሰረተ ሃሳብ ተመሳሳይ ነው።
ብሄር ተኮሩ ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር መቀየር አለባቸው። የጠ/ሚኒስትር ዶር ዐብይ አህመድ መንግሥት ለታላቋ ኢትዮጵያና ተቻችሎ ይኖር ለነበረው ለመላው ሕዝቧ ሊያበረክት የሚችለው ጥሪት በአስቸኳይ በባለሞያዎች የሚመራና የተዋቀረ የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ማቋቋምና ይህ ኮሚሽን ጥናትና ምርምር አካሂዶ፤ ከሌሎች አገሮች ልምድ ጋር አነጻጽሮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጮችን ማቅረብ ነው። ውሳኔ ማድረግ ያለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጅ የፖለቲካ ልሂቃን ሊሆኑ አይችሉም። ከአሁን በኋላ መረባረብ ያለብን በዚህ አርእስት ዙሪያ ነው።
የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ለእያንዳዳችን የምታሳፍር ሆናለች። አገሪቱ ወይንም ሕዝቧ አይደሉም የሚያሳፍሩት። የፖለቲካ ልሂቃን፤ አድር ባይ ምሁራን፤ የክክልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው የሚያሳፍሩት። አንድ ቀን በሰሜን ሸዋ የሚኖረው ሕዝብ ሰላማዊና የሚፋቀር ሕዝብ ተምሳሌት ነው ተብሎ በበነገታው በቦምብና በከባድ መሳሪያ ንጹሃን የሚጨፈጨፉበት፤ ቤተ ክርስቲያን የሚቃጠልበት አካባቢ ሲሆን አደጋ አለ ማለት ነው።
ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ሩዋንዳ ሄዶ የሩዋንዳ ሕዝብ ዘውግ መደራጀት፤ የዘውግ ጥላቻ ማዛመት በሕግ የተከለከለ መሆኑን በአይኑ አይቷል። በብሄር መደራጀት፤ በብሄር ጥላቻን ማዛመት፤ በብሄር አመካኝቶ መግደል፤ ማስፈራራት፤ ቤትና ንብረት ማቃጠል በሕግ እንዲከለከል ማድረግ ወቅታዊና ወሳኝ የፖሊሲ ጥያቄ ነው። ከሩዋንዳ የጥፋት ልምድ ለመማር መቻል ግዴታችን ነው። ብልህነት ነው።
ለዘውግ ታማኝነቱ ይቁም
የዝውግ ታማኝነትና ኢትዮጵያዊነት አብረው አይሄዱም። ዘረኝነትና ጎጠኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አብረው አይሄዱም። ዘመናዊነትና ጠባብ ብሄርተኝነት አብረው አይሄዱም። በምእራብ አገሮች ስንኖር ዘመናዊ፤ ወደ ኢትዮጵያ ስንሄድ ጎጣዊ፤ ኢ-ሰብአዊና ኢ-ፍትሃዊ የምንሆንበት ዘመን ማቆም አለበት።
የኢትዮጵያና የግዙፍ ሕዝቧ አጀንዳ ከዘውግና ከኃይማኖት በላይ መሆን አለበት። ወደ ታች የወረደው ስነ ምግባራችን ከፍ እንዲል ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ አለብን።
ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ በአሜሪካ ለምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በላኩት ደብዳቤ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጡት፤ የምንፈልጋትና በቅንነት የምናስባት ኢትዮጵያ “የበለጸገች፤ የሰለጠነች፤ አንድነቷ የተጠበቀ፤ በዓለም ፊት በሞገስና በኩራት የምትቆም፤ ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት፤ ዜጎቿ የትም የሃገሪቱ ክፍልበሰላምና በጤና የሚኖሩባት” ኢትዮጵያ መሆን አለባት። መላው የጥቂር አፍሪካ ሕዝብ በዜግነት አምኖና ተባብሮ ችግሮችን ለመፍታት በሚሞክርበት በሃያ አንደኛው ምእተ ዓመት እንዴት በዓለም እውቅና ያላትን አገር ወደ ኋላ እንጎትታታለን።
እኔ በአሜሪካ ሆኘ የአዲስ አበባን ከተማ ሕዝብ ሁኔታ ሳስበው ለአገራችን ሕዝብ አፍራለሁ፤ ለአገራችን እሰጋለሁ። ይህ ሁኔታ በፍጥነት፤ በውይይት፤ በጨዋነት፤ በመደማመጥና በመደጋገፍ መፈታት አለበት። ዘመናዊነት ማለት አብሮነትን ማጠናከር ማለት ነው። አብሮነት ደግሞ በብሄር ተኮር አጥር ስኬታማ ሊሆን አይልም።
አገር ወዳዱና ጀግናው አጼ ቴዎድሮስ መስዋት የሆኑላትን፤ አጼ ዮሃንስ የአገራቸውን ክብር ለመታደግ ሲዋጉ በጠላቶች እጅ የሞቱላትን፤ “እምየ ምኒልክ” እና ጀግናዋና ጥበበኛዋ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በብልሃት እቅድ አውጥተው፤ ወርቃማውን የኢትዮጵያን ሕዝቧን አስተባብረው፤ “ከኣንተ በላይ የጀግና ጀግና ሕዝብ የለም”በሚል መንፈስና ስትራተጅ የአድዋን ድል ለተከታታይ ትውልድ ያስተላለፉልንን ታሪካዊዋንና ታላቋን ኢትዮጵያን እኛ እንድንታደጋትና ዘመናዊ እንድናደርጋት እንጅ፤ እኛ የራሷ ልጆች እንድንበታትናት አይደለም። በኔ እምነት፤ የኢትዮጵያ ጀግናና ታላቅ ሕዝብ ከተባበረ ሊፈታው የማይችለው አንድም ችግር አይኖርም። ታላቅና ዘመናዊ ለመሆን ከፍተኛ እምቅ ኃብት ያላትን ኢትዮጵያን ዝቅ አናድርጋት።
እስኪ ለአንድ አፍታ፤ እያንዳናችን፤ ሁሉን አውቃለሁነትን፤ ግለሰባዊነትን፤ ዘረኝነትን፤ ዘውገኛነትን፤ ጥላቻን፤ ምቀኝነትን፤ ጽንፈኛነትን፤ ጠብ-ጫሪነትን፤ ገጀራ ያዢነትን፤ ጡንቻማነትን፤ ቀረርቶንና ፉከራን ወዘተ ወደ ገደሉ አፋፍ አስቀምጠን እያንዳንዱን ብርቅ ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ወይንም በዜግነቷ፤ በሰብአዊ መብቱ ወይንም መብቷ እንዲኖር እናስብ፤ በልባችን እንቅረጽ። “ለኔ” ከሚለው እሴት ወጥተን “ለኛ” ወደሚለው እናዘንብል። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚያስከትለው ዓለም እጅግ በጣም አስደናቂ እንደሚሆን አልጠራጠርም።
የውጭ ጠላቶቿ እንዳይደፍሯት በሚል መንፈስ፤ ጀግንነት፤ ኢትዮጵያዊና ሕዝባዊ አንድነት፤ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ክብር፤ ለሉዐላዊነቷንና ነጻነቷን ዓለም ባደነቀው ቀናእይነቱ የታደገው ሕዝብ በራሱ ልጆች የፖለቲካ ስልጣን ስግብግብነት እየታመሰ ነው። ኢትዮጵያን ስንት ጊዜ በራሷ ልጆች ደካማነትና የሥልጣን ስግብግብነት ወድቃ እንድትነሳ እንፈርድባታለን?
መለስ ዜናዊና ቡድኑ በ1991 በመሰረተው የዘውግ ልሂቃን ስብስብና ልሂቃኑ በ1994 ዓ.ም. ያለ ሕዝብ ተሳትፎና ውይይት በመሰረቱት ብሄር-ተኮር ሕገ መንግሥት፤ልዩነቶችን የሚያሰፋና የሚያጠናክር የክልል አስተዳደር እና የመገንጠል መብትን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛና ወሳኝ ሚና ተቀብሎና እንከን የለውም ብሎ፤ ታሪካዊዋን ኢትዮጵያን ለመታደግ አይቻልም። የዘውግ ጥላቻ፤ ፉክቻና አብሮነት ተደጋጋፊ አይሆኑም።
ብሄር ወይንም ዘር ተኮር ጥላቻና ግጭት፤ የእልቂት እልቂት እንደሚያስከትል በሩዋንዳ አይተናል። የሩዋንዳው መሪ ፖል ካጋሚ በሩዋንዳ ሕገ መንግሥትማንኛውም ዜጋ የብሄር ጥላቻን እንዳያካዲ ሕገ ወጥ ያደረገው ብሄር ተኮር የርስ በርስ እልቂት እንዳይደገም ነው። በተመሳሳይ፤ የጋና መንግሥት በጋና የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘውግ የማንነት መለያ ሳይሆን፤ በዜግነት መብት መከበር ብቻ፤ ማለትም በጋናዊነት እንዲደራጁ ደንግጓል።
በህወሓት መሪነትና በመለስ ዜናዊ አቀነባባሪነት፤ የኢትዮጵያ የዘውግ ልሂቃን በሜዳ ተስማምተው ያጸደቁትና ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮና ተባብሮ ችግሮችን የመፍታት ዓላማ መሰናክል የሆነው ብሄር ተኮሩ ሕገ መንግሥትና የክልሉ የከፋፍለህ ግዛው አስተዳደር እንዳለ ለመቀበል አይቻልም። ምክንያቱም፤ አብሮነትን፤ ብሄራዊ እርጋታን፤ እርቅ፤ ሰላምንና በኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያ የተከበረውን አንድነት ለማጠናከር አይቻልም። ያለምንም ጥናት፤ ምርምርና መረጃ ዛሬ በየቦታው የተከሰተውን ሰው ሰራሽ የርስ በርስ ብሄር ተኮር ግጭት ዋጋ አስከፋይነት በጽሞና ባለማየትና ገንቢ አማራጭ ባለመስጠት፤ በዘውግ መደራጀት ልክ “የሕክምና ባለሞያዎች በሞያቸው እንደሚደራጁት ነው” የሚሉ ክፍሎች መኖራቸው ብዢታውን አጠናክሮታል። በሞያ በመደራጀትና በዘውግ በመደራጀት መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም። ግንኙነት የላቸውም።
በተጨማሪ፤ በብሄር ተኮሩ ሕገ መንግሥትና “የከፋፍለህ ግዛው” በሆነው በብሪቲሾቹ ሞዴል የተቀነባበረው የክልል አስተዳደር ላይ “ምንም አይነት ድርድር አይቻልም” የሚለው የህወሓትና የኦዴፓ አቋም ስር የሰደደውን ብሄር ተኮር ጥላቻ፤ የመሬት ነጠቃ፤ ቅርሚት፤ ግጭትና የንጹህ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰት ሊፈታው አይችልም። እንዲያውም አባብሶታል።
የተባበሩት መንግሥታት፤ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያ ባለሞያዎችና ሌሎች የሚያቀርቡት ዘገባ የሚያሳየው ክስተት አለ። ይኼውም፤ በጥቅሉ ሲታይ፤ 8.3 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ( Humanitarian Assistance) ያስፈልጋቸዋል። የሚፈለገው የወጭ ፈሰስ በዝቅተኛ 28 ቢሊየን ብር ነው።ግጭቶች በሰላም፤ በውይይትና በፍትህ ካልቆሙ በስተቀር ችግሩ ይቀጥላል።
የወገኖቻችን አሰቃቂና አላስፈላጊ ረሃብ፤ በተለይ የእናቶችን፤ የእርጉዞችን፤ የሽማግሌዎችን፤ የሕጻናትን አሰቃቂ ሁኔታ ሳስብ፤ የደቡብ አፍሪካው አለን ፔይተን “Cry My Beloved Country” በተባለው መጽሃፉ ላይ ያቀረበው ትዝ ይለኛል። የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ስቃይና እልቂት የተካሄደው በነጭ ዘረኞች ነው።
የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ አንድ ዓመት ሆኖታል። ከዚያ ወዲህ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተካሄደው ብሄር ተኮር ግጭት ለሶስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጥ ፍልሰትና ስደት ምክንያት ሆኗል። የችግሩ ጥልቀትና ስፋት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ የተለያየ ቢሆንም አሉታዊው ውጤት ግን ተመሳሳይ ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ያሳፍራል፤ ያሰቅቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መረባረብ፤ ጥልቀትና ስፋት እንዲይዝ ማድረግ ያለበት በብሄር ጥላቻና ዛቻዎች ላይ አይደለም። ዋናው ትኩረት መሆን ያለበት የድህነትን መጠን ብሄርና ክልል ሳይለዩ መቅረፍ ነው። ዛሬ የድህነት መጠን 25.6 በመቶ ከሆነ፤ ይህ መጠን በ2030 ወደ 3.9 በመቶ ዝቅ እንዲል መረባበረብ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያኮራል፤ በዓለም ሕዝብ ያስከብራል።
የእያንዳንዱ ዜጋ ክብርና መብት ካልተከበረ፤ ለዚህ ሌላው አብዛኛው ዓለም ለደረሰበት ዓላማ የደረሰበት ዓላማ ደግሞ መሰረት የሆነው ሰላምና እርጋታ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ስኬታማ ካልሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከደረሰበት አሰቃቂ ድህነትና የኑሮ ግሽፈት ለማውጣት አይቻልም። ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ ይህን ብሄራዊ ዓላማ እንደሚጋሩ አምናለሁ። ሆኖም፤ በመሬት ላይ የሚታየው ሃቅ የተለየ ነው። ከአንድ ዓመት የለውጥ ሂደት በኋላ መሰረታዊ፤ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጥ አለ ለማለት አልችልም። ይህ ቢሆን ኖሮ በአደባባይ ቆመው “እልል በይ አገሬ” ከሚሉት መካከክል ፊት ለፊት የምቆመው አንዱ እኔ ነኝ።
መካድ የሌለበት ሃቅ አለ። ይኼውም የዶር ዐብይ መንግሥት ሥልጣን ከመያዙ በፊት የነበረው ሁኔታ ከመቸውም በበለጠ ደረጃ እጅግ በጣም አስጊ ነበር። “የርስ በርስ ጦርነት ይካሄዳል፤ ኢትዮጵያ ልትፈራርስ ትችላለች”የሚሉ ኃይሎች ብዙ ነበሩ። ይህን መርሳት የለብንም። ሆኖም፤ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና “ብዙ የኢትዮጵያ ዜጎች በመሬት ላይ ሲታይ መሰረታዊ ለውጥ የለም” ይላሉ ብሎ የጠቀሰው አግባብ አለው። አንድ የውጭ አገር ታዛቢ ወይንም ዲፕሎማት Daily Mail March 31, 2019 ባቀረበው ዘገባ ተጠይቆ በሰጠው ዘገባ የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ “One Man Theatrics” በሰማይ ላይ የተንሳፈፈ መሆኑን አስምሮበታል። አል ጃዚራም ተመሳሳይ ዘገባ አቅርቧል። አንድ ግለሰብ ብቻውን ተግዳሮቶችን ሊፈታ አይችልም። ጠንካራና የማይበገሩ ብሄራዊ ተቋማት ያስፈልጋሉ። የኔም ትኩረት ከዚህ ላይ ነው።
ዛሬ በጌድዮ የተከሰተው ሰው ሰራሽ ፍልሰትና ረሃብ ለእናቶች፤ ለህጻናት፤ ለእርጉዞች፤ ለሽማግሌዎችና ለበሽተኞች እንዴት አሰቃቂ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል። የኢትዮጵያ ሜድያዎችና ከመቶ በላይ የሚገመቱት “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ክፍተቱን በሚገባ ያወቁት አይመስለኝም።
በጌድዮ፤ የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ቁጥር 800,000 በላይ ነው ሲባል፤ የእነዚህ ወገኖቻችን መብት ተነጥቋል እንደማለት ነው። በተመሳሳይ፤ በጎንደር 90,000ወገኖቻችን በጠለላ እንዲኖሩ ተገደዋል። ለእነዚህ ወገኖቻን የክልልና የፌደራል መንግሥት ሃላፊዎች በጋርና በተናጠል የተቀነባበረ ጥረት ማድረግ ግዴታቸው ነው። እኔ ከመስራቾቹ አንዱ የሆንኩበት ግሎባል አላያንስ የተባለው ድርጅት የተቻለውን እያደረገ ነው። ኢትዮጵያዊያንም የሚያደርጉት ጥረት እጅግ በጣም የሚያኮራ ነው። ሆኖም፤ መሰረታዊው ስርዓት ወለድ ችግር ካልተፈታ ነገ ደግሞ ሌላ ፍልሰትና ስደት እንደሚኖር መገመት አስቸጋሪ አይደደለም።
በተለይ የፌደራሉ መንግሥት የዜጎችን ሰብአዊ ክብርና መብት የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት። ይህ ወገንተኝነትንና አድልዎን ከመቅረፍ አንጻር መታየት ያለበት አደራ ስለሆነ ትላንት ህወሓትን ከሥልጣን አውርደናል የሚሉ ኃይሎችና ክፍሎች ትግሉ ገና የተጀመረ እንጅ ያልተፈጸመ መሆኑን ማወቅ አለባቸው የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ትላንት “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” ያሉ ክፍሎች የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደም ደማችን ነው ወደሚባልበት ደረጃ መሸጋገር አለባቸው።ትላንት “የሕግ የበላይነት ይከበር” እያሉ ይጮሁ የነበሩ ኃይሎች እርስ በርስ መጠፋፋት የሕግ የበላይነት ጥሰት ነው ብለው የሚደፍሩበት ወቅት ዛሬ ነው። በሚቀጥለው ገጽ የሚታየው ህጻን መለያው ሰብእነትና ኢትዮጵያዊነት ነው፤ብሄር አይደለም። የኔ ወይንም የአንተ ወይንም የአንች ልጅ ወይንም የልጅ ልጅ ልጅ ሊሆን ይችላል። እሱን አይቶ የማያለቅስ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። መጠፋፋት ማንንም አይጠቅምም። መጠፋፋት ዝቅ አድርጎናል።
ታዳሚዎች ትኩረት እንዲሰጡት ለናሙና ያክል የሚከተለውን ከግሎባል አላያንስ ቡድን የተገኘ፤ በተለይ የልጆችንና የህጻናትን አሰቃቂ ህይወት የሚያሳይ ፎቶግራፍ አቅርቤያለሁ።
የሚያሳፍር የወገኖቻችን ሰቆቃ
ይህ ኢትዮጵያዊ ሕጻን ነገ ኢንጂኔር፤ ሃኪም፤ አስተማሪ ወይንም ሌላ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያዊነት ማለት ለዚህ ሕጻን ድምጽ ማሰማት ነው። ሰብአዊ መብት ይከበር ሲባል ዘውግ፤ ኃይማኖት፤ ጾታ ወይንም እድሜ አይለይም።
ብሄር ተኮር ግጭትና እልቂት አሰቃቂና አሳፋሪ ነው የምልበት መሰረታዊ ምክንያት በንጹህ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን እልቂት፤ ረሃብና ሌላ ሰቆቃ በማጤን ነው። እንደዚህ ያሉ ችግሮች ተደጋጋሚ ሲሆኑ የፖሊሲው፤ የሕገ መንግሥቱ፤ የአመራሩ፤ የአስተዳደሩና የተቋማቱ መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው ብለን የመጠየቅ ሃላፊነት አለብን። አገራችን እንወዳለን ስንል ሕዝቧንም እንወዳለን ማለት መሆን አለበት። ኢትዮጵያን እንወዳለን ስንል ይህች አገር እንዳይነገድባት ደፍረንና ተባብረን አንድነቷንና ሉዐላዊነቷን በየቀኑ ማስተጋባት አለብን። ራስና ጥቅም ወዳድ ሆነን አገር ወዳድ ለመሆን አንችልም።
“በብሄርተኮሩ ሕገ መንግሥትና በክልሉ አገዛዝ ላይ” መደራደር አይቻልም የሚሉት ህወሓትና ኦዴፓ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። አብረንና ተመካክረን የፈጠርነውና ለሶስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን መፍለስ፤ ለስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊየን ወገኖቻችን ጥገንነት ምክንያት የሆነው አገዛዝ አይደፈርም ማለታቸው ነው። በምርኩዝ የሚንገዳገደው ኢኮኖሚ ቢንገዳገድና ተራው ኢትዮጵያዊ በዋጋ ግሽፈት ቢሰቃይም ለእኛ ደንታ ቢስ ነው ማለታቸው ይሆናል።
ዋናው የለውጥ ትኩረት የስነ-ምግባር፤ የባህርይና የፖለቲካ ባህል ለውጥ ነው።
ዘውግ ተኮር ባህርያችን መሰናክል ስለሆነ ወደ ገደሉ ጫፍ እናቁመው (Let us park our dysfunctional behavior at the edge of the cliff) ያልኩበት መሰረታዊ ምክንያት ብሄር ተኮሩ አገዛዝ ጊዜ ያለፈበት መሆኑን ለማጠናከር ነው። መቶ ፓርቲዎችቢቋቋሙ የሚታዩትን ተግዳሮቶች አይፈቱም። “ተፎካካሪ” ፓርቲ የሚባለው ቃል ራሱ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም፤ ተፎካካሪዎቹ አብዛኛውን ጊዚያቸውን የሚያጠፉት በሹክቻ ላይ ነው። ራሳቸውን በማሞገስ ላይ ነው። ከኢህአዴግ ጋር አቻ ለአቻ ሆኖ የሚወዳደርና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስብ ፍኖተካርታ ይዘው ለመቅረብ አልቻሉም። ጊዚያቸውንና እውቀታቸውን የሚያጠፉት በገመድ ጉተታ ላይ ስለሆነ፤ ህብረብሄራዊ ፓሪት ለመፍጠር አልቻሉም።
የፍኖተ ካርታ አማራጭ ስል ምን ማለቴ ነው?
እኔ የምለውን ብትንቁትም ባይሆን ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ ያሉትን እንደ አማራጭ ላቅርበው። የምንመኛት ኢትዮጵያ “የበለጸገች፤ የሰለጠነች፤ አንድነቷ የተጠበቀ (እኔ የምጨምረው ለድርድር የማይቀርብ)፤ በዓለም ፊት በሞገስና በኩራት የምትቆም፤ ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት፤ ዜጎቿ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሰላምና በጤና የሚኖሩባትን” አገር ነው።
“ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ራሳቸው በጋራ ሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የሚበጅ ፍኖተ ካርታ ለማቅረብ ባይችሉም፤ ከላይ የጠቀስኩትን መርህ ለመቀበል የማይችሉበት መሰረታዊ ምክንያት የለም። የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት አማራጭ ማቅረብ ያስፈልጋል። አማራጭ ለማቅረብ መወያየትና መድፈር ያስፈልጋል። ሕብረ-ብሄራዊነት የሚጠቅመው አንድን ቡድን ወይንም አንድን ዘውግ ብቻ አይደለም።
አይቻልም እንጅ ቢቻል ኖሮ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢጠየቅ ከመቶዎቹ ፓርቲዎች መካከል ብቃትና ጥራት ያለው “ተፎካካሪ ፓርቲ” አያገኝም።
የፈለገውን ያክል ስብሰባዎችና ውይይቶች ቢካሄዱም፤ ችግሩ በአድርባይነትና በአጎብዳጅነት ሊፈታ አይችልም። ውይይቶቹ በሕዝቡ ሰቆቃ ላይ ቢሆኑ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችላል። የጌድዮን፤ የጎንደርን፤ የኦሮሞን፤ የሶማሌን፤ የለገጣፎን፤ የቡራዩን ወዘተ እናቶችና ህጻናት የኑሮ ሁኔታ አይተን ራሳችንና ህሊናችን እንመራመር።
የማይካደው ሃቅ አንድ ነው። በራሳችን አለመግባባትና በራሳችን ድክመት ምክንያት፤ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታላቅ ሕዝብ ዝቅ እያደረግናቸው ነው። ከመቶ በላይ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሉ” የሚለው ተረት ይመስላል። ተረት የሚሆነው ሕዝቡ የሚፈልገው፤ የሚመኘው፤ ተስፋ የሚያደርገውና እነዚህ ፓርቲዎች የሚያደርጉት የሰማይና የመሬት ያክል እርቀት ስላለው ነው። “ላም አለኝ በሰማይ” እንዲሉ የሚሽከረከቱት በሰማይ እንጅ በምድር ላይ አይደለም። በመሬት ላይ የተከሰቱት ሰው ሰራሽ ችግሮች በጌድዮ፤ በጎንደር፤ በለገጣፎ ወዘተ ይታያሉ።
የአሁንና የወደፊቱ ታላቅ ጦርነት መካሄድ ያለበት ወገን በወገኑ ላይ ብሄር ተኮር ግፍና በደል በመፈጸም አይደለም፤ ሊሆንም አይገባውም። ወንድማማቹን የትግራይንና የዐማውራን ሕዝብ ከሚለያዩት በላይ የሚያቀራርቡት እሴቶች ብዙ ናቸው። የዐማራውና የዐማራው ሕዝብ ቢፈልግም ሊለያይ አይችልም፤ ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፤ ተዛምዷልል። ችግሩን በውይይት እንጅ በጦርነት ሊፈታው አይችልም። በተመሳሳይ በኦሮሞውና በሶማሌው ኢትዮጵያዊና በሌሎች መካከል የተካሄደውና የሚካሄደው ግጭቱ ለማንም አይበጅም። ፉክቻው ቆሞ ትኩረቱ ድህንነትን፤ ረሃብን፤ ብሄር ተኮር ጥላቻንና ኋላ ቀርነትን ለመቅረፍ መሆን አለበት የምለው ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንባትን ኢትዮጵያን ለመመስረት ይቻላል የሚለው እምነቴ ጠንካራ ስለሆነ ነው። እንቅልፍ ሊነሳን የሚገባው ሥልጣን፤ ዝናና የግል ጥቅም ማሳደድ ሳይሆን የሕዝቡ ሰቆቃ ነው።
መጀመሪያ በኢትዮጵያ ብሄራዊ አንደነት ላይ ተመሳሳይ እምነት ይኑረን። ኢትዮጵያን በአንድነት ሆኖ ከመገንባት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። የኢትዮጵያን ሕዝብ በዱላና “በገጀራ” ማስፈራራት ኢ-ሰብአዊ እምነትና ድርጊት ከመሆኑም በላይ፤ ይህን ታላቅ ሕዝብ ፈጽሞ አለማወቅንም ያሳያል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጫኑትን አደጋዎች በጋራ ቀርፎ ፍትሃዊና ተከታታይ እድገት ስኬታማ ለማድረግ የሚቻለው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የአገሪቱ ታላቅነት፤ ክብር፤ ነጻነትና ሉዐላዊነትባለአደራዎች ስንሆን ነው። አባቶቻችን በጋራ ሆነው ስኬታማ ያደረጉትን ታላቁን የአድዋን በዓል በጋራ አክብረን ዛሬ በዘውግና በቋንቋ መለያየታችን ታላቅ ለመሆን የምትችለውን ኢትዮጵያን ዝቅ እያደረግናት መሆኑን መገንዘብ አለብን። ጠባብ ብሄርተኝነት አደጋ ፈጣሪ ፍልስፍና ነው።
እኔ የፌደራል መንግሥት እንደሚያስፈልግ አምናለሁ። ችግሩ የፌደራል ስርዓት አይደለም። የተለያዩ ሞዴሎች አሉ። የምከራከረው ብሄር ተኮሩ ፌደራሊዝምና ክልላዊነት፤ በተለያዩ ወቅቶችና በተለያዩ ቦታዎች፤ በተደጋጋሚ ግጭቶችን ፈጥረሯል፤ ሶስት ሚሊየን ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል። ኢትዮጵያ ወደ ከፍተኛ የምግብ እርዳታ ልመና ተሸጋግራለች።
“ተፎካካሪ ፓርቲዎች” በእነዚህና በሌሎች አስኳል ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ምን አይነት አቋም ወሰዱ? በአንገብጋቢው የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይ ላይ ምን አይነት ግንዛቤ አላቸው? ችግሩን ለምን ይፈሩታል፤ ማንንስ ይፈራሉ? ችግሮችን ፈርተው ወይንም ሸሽተው “ተፎካካሪ” ሊሆኑ አይችሉም።
“ተፎካካሪ ነን” የሚሉ ፓርቲዎች “በዘውግ” መደራጀት ልክ በሞያ እንደመደራጀት ነው” ማለትን ከቀጠሉ፤ የፖለቲካ ምሁራንና ልሂቃን ቢያንስ ባለፉት 28 ዓመታት ብቻ የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን ዘውግ ተኮር እልቂት፤ ስደት፤ የኃብት ውድመት፤ ሌብነት፤ የሶስት ሚሊየን ሕዝብ ፍልሰትና ሌላ የተያያዘ ቀውስ መሰረታዊ ምክንያት (Root, systemic and structural causes) አላጤኑትም ማለት ነው። በአይን የሚታየው ሃቅ አለ። በአዲስ አበባ የተካሂደውና አሁንም የሚካሄደው የማንነትና የባለቤት ጥያቆ ያላስፈላጊ ፍልሰትን፤ ፍርሃትን፤ የርስ በርስ ግጭትን ፈጥሯል።
በአይን የሚታይ ሌላ ሃቅ አለ። በጎንደር ብቻ 90,000 ሕዝብ በጠለላ ይኖራል። በጌድዮ በብዙ መቶ ሽህ የሚገመት ሕዝብ በረሃብ ይሰቃያል። ይህ ሁሉ ሰው ሰራሽ ነው፤ ከብሄር ተኮሩ አገዛዝ ጋር የተያያዘ ክስተት ነው።
የፖለቲካ ልሂቃን ፖለቲካ ፓርቲዎች ሆኑ ሌሎች በተከታታይ፤ በተለይ ኢህአዴግ የፖለቲካ ሥልጣን ከያዘበት ከሩብ ምእተዓመታት በላይ ሲካሄድ የቆየው ብሄር ተኮር ፍልሰት፤ እልቂትና መከፋፈል ለአብሮነትና ለኢትዮጵያ ዘላቂነት አደጋ የፈጠረ መሆኑ እየታወቀና እየተተቸ፤ ዛሬም እንደ ትላንቱ በዘውግ መደራጀት አግባብ አለው የሚሉ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ብዙ ናቸው። እኔ የምከራከረው ብሄር ተኮር ፌደራሊዝምና የክልል አስተዳደር አደገኛ መሆኑ ተጨማሪ መረጃ አያስፈልገውም ነው። ብሄር ተኮር አመለካከትና የፖለቲካ አደረጃጀት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በሌላ በኩል ግን፤ በማንኛውም ዓለም የሚሰራው በዜግነት የተመሰርተ ፌደራሊዝም ወይንም ሌላ አይነት ሕዝብ ተወያይቶ የተቀበለው አማራጭ ያዋጣል።
የዘውግ ፖለቲካንና የፖለቲካ አደረጃጀትን የሚደግፉ ኃይሎች፤ በተለይ ጽንፈኞችና ጠባብ ብሄርተኞች የሚያራምዱት ፍልስፍና “እኛ” ኢትዮጵያዊያን የሚለውን ሳይሆን፤ “ኬኛ” የሚለውን ነው። አዲስ አበባ የሁላችንም ናት በማለት ፋንታ አዲስ አበባ “ኬኛ” የሚለው ብሂልና የፖለቲካ መስመር፤ አምስት ሚሊየን ህብረ-ብሄር ነዋሪዎች የባለቤትነት መብት የላቸውም፤ “መጢዎች” ናቸው እንደማለት ነው።አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ ናት። በተጨማሪ፤ ይህች ዘመናዊ ከተማ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ተወካዮች ከተማ ናት። የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት፤ የአካባቢ ድርጅቶች፤ የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዲፕሎማቲክ ስብስቦች ከተማ ናት። ታላቋን ከተማ ዝቅ አናድጋት። አዲስ አበባ ዝቅ ማድረግ ኢትዮጵያንና ትላቁን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዝቅ ከማድረግ አይለይም። ለዚህ ነው አፍሪካዊያን የሚስቁብን!!
አዲስ አበባና ሌሎች ከተማዎች በዘውግ አጥር ተከልለዋል ከተባለ ብልጽግና፤ ዘመናዊነትና ህብረ-ብሄራዊነት ሊያብቡ አይችሉም። ከተሜነት ከዘመናዊ እድገት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። ከተሜነት ማንኛውም ዜጋ የሚኖርበት፤ ቤትና ሌላ ንብረት የሚያካብትበት ቦታ ማለት ነው። በዚህ አስኳል የፖሊሲ ጉዳይ ላይ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ምን ይላሉ?
በኔ እምነትና ጥናት፤ የአዲስ አበባ ከተማ የአንድ ዘውግ ከተማ ናት ብሎ መከራከርና ነዋሪዎቹን በልዩ ልዩ ዛቻና በትር ማስፈራራት አገሪቱን ወደ አላስፈላጊ አደጋ እንደ ማሸጋገር ይገመታል። ነጻ ነን የሚሉት “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” በዛቻ ላይ ምን ይላሉ?
እኛ ኢትዮጵያዊያን ከራሳችን መጥፎ የአገዛዝ ታሪክና ከሌሎች የርስ በርስ ግጭትን አጥፊነት ከቀመሱ አገሮች፤ ለምሳሌ፤ ከሩዋናድና ከደቡብ አፍሪካ ለመማርና አዲስ የአብሮነት ምእራፍ ለመክፈት እንችላለን። ሕዝቡ የሚፈልገው ይኅን አዲስ አቅጣጫ እንጅ የርስ በርስ ጦርነትን አይደለም።
“ተፎካካሪ ፓርቲዎችና” የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት
ዛሬ በኢትዮጱያ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይንቅሳቀሳሉ፤ አብዛኛዎቹ የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው። መሪዎቻቸው ሕዝብን ሳያማክሩና የህዝብን እምነትና የማይናጋ ድጋፍ ሳያገኙ ልክ እንደ አካደሚክ ውይይት ሕዝብ ወክሎናል የሚል የልሂቃን ውይይትና ድርድር ያደርጋሉ። ሕዝብ ሳይመርጠውና ሳይወክለው በሕዝብ ስም፤ ለሕዝብ ውሳኔ
የሚያደርግ ቡድን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በተከታታይ አይተናል። ኢትዮጵያ እንደ ገና ከማይመለስ አደጋ
ጫፍ ላይ ደርሳለች እየተባለ ይነገራል። እኔ ኢትዪኦጵያ አትፈርስም የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፤ ከአርባ ዓመታት በላይ ሰከራከርበት የቆየሁበት አቋም።
በቅርቡ the New York Times; the Guardian, the International Crisis Group እና ሌሎች በዓለም የታወቁ ተቋማት የሚሉት አገራችን ገና ያልተፈቱ ችግሮች አሏትና ጠ/ሚንስትር ክቡር ዶር ዐብይ አህመድ የጀመሩት ሰላማዊ፤ መሰረታዊና ገንቢ የለውጥ ሂደት ብዙ መሰናክሎች ገጥመውታል የሚል ነው። በአሁኑ ወቅት፤ ጠ/ሚንስትሩ የሚመሩትን የለውጥ ሂደት ከመደገፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም። ፈተናዎች መኖራቸው እንዳለ ሆኖ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈ ስለሆነ የአሁኑንም ፈተና ያልፈዋል የሚል እምነት አለኝ። የኢህአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከመያዙ በፊትና በኋላ በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት ሁሉ፤ ጠንካራና አንድቷ የተከበረ ኢትዮጵያን ለመመስርት ይቻላል;፡ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ እንዳስቀመጡት የእያንዳንዳችን ጥረት መሆን ያለበት “የበለጸገች፤ የሰለጠነች፤ አንድነቷ የተጠበቀ፤ በዓለም ፊት በሞገስና በኩራት የምትቆም፤ ዲሞክራሲና ፍትህ የሰፈነባት፤ ዜጎቿ የትም ክፍል በሰላምና በጤና የሚሩባትን ኢትዮጵያ መገንባት ነው (ለዲያስፖራው የተጻፈ ደብዳቤ፤ March 28, 2019)።
ይህን መርሆ ስኬታማ ለማድረግ ግን ብሄር ተኮሩና በክልል አጥሮች የተበከለው አስተዳደር መቀየር አለበት።
የሚጽፉትንና የሚያቀርቡትን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ባልቀበልም፤ የውጩ ተቋማትንና ግለሰቦችን ትንተናና ትችት የማየው ከዚህ ብሩህ የለውጥ እንቅስቃሴ አንጻር ነው።
የታወቀው የጥናትና የምርምር ተቋም፤ International Crisis Group, Report No. 269, February 21, 2019, ባቀረበው ዘገባና ምክር እንዲህ ብሏል። “At the top of Prime Minister Abiy Ahmed’s priority list must be the restoration of security through calming of ethnic tension and violence. To encourage a positive national tone, Abiy should develop a governance style that matches his inclusive rhetoric.” Among other things, inclusion of stakeolders “can help dispel the impression shared by some that he is governing from a closed circle of co-ethnic and regional advisrors.” የካብኔውና የሌላው የፖሊሲና የውሳኔ ባለሥልጣናት ስርጭት የኢትዮጵያን ሕዝብ ስርጭት ማንጸባረቅ አለበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ የዐማራውና የኦሮሞው ወጣት ትውልድ በህወሓት አልሞ ተኳሾች የተጨፈጨፈው ህወሓት መራሹን አፋኝ፤ ገዳይና ዘራፊ ቡድን ስለተቃወመ ነው። ህወሕትን በኦዴፓ ሆነ በሌላ የብሄር አምባገነን ቡድን ለመተካት አይደለም። ስለዚህ፤ ከላይ የቀረበውን ምክር እኔም እጋራለሁ። የኢትዮጵያ 110 ሚሊየን ሕዝብ ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይን አልመረጣቸውም። የመረጣቸው ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ የዘውግ ፓርቲዎች ስብስብ ነው። ይህ ገዢ ፓርቲ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን አላነሳም፤ በዘውግ መደራጀትን አላነሳም። እንዲያውም፤ ኦዴፓና ህወሓት ተመካክረውም ባይሆን ለየብቻቸው “ዘውግ ተኮሩ ሕገ መንግሥትና ክልላዊው አገዛዝ ለድርድር አይቀርብም” የሚል አቋም ወስደዋል።
እኔ ጠ/ሚንስትሩ ይህን አቋም ይጋራሉ የሚል እምነት የለኝም፤ እሳቸው ከሚናገሩት ጋር ይጋጫል። “ተፎካካሪ ፓርቲዎችስ” ምን ይላሉ? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለባቸው ፓርቲዎቹ ናቸው።
እኔ የምከራከረው፤ ኢትዮጵያን ከደረሰባት አስጊ የዘውግ ግጭትና የመፈራረስ አደጋ ለመታደግ የብሄር ተኮሩ ፌደራል አገዛዝ በዜግነት መተካት አለበት ነው። በዚህ ላይ የጠ/ሚንስትሩ አቋምም ቢሆን ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። “Abiy has
avoided taking a clear position on ethnic federalism. Though he rode a wave of regional and ethnic grievance to his current position, since assuming high office he has made frequent reference to Ethiopiawinet (ኢትዮጵያዊነት)-, a term invoking national unity rather than decentralization.” እኔ ከዚህ ትንተና የምለየው ፌደራሊዝም ሥልጣንን ለሕዝብ ከመስጠቱ ላይ አይደለም። ስልጣን የሕዝብ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ስልጣን የሕዝብ ይሁን ስል ግን የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት መጠበቅ አለበት የሚል አቋም አለኝ። ይህ አቋም በዘውግ ብቻ “የኔ መሬት፤ የኔ ከተማ፤ የኔ ክልል” ከሚለው ይለያል። ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም መለያያ ነው። መለያያ ስለሆነ በጥናትና በምርምር፤ በሕዝብ ውይይትና ድምጽ የሚወሰን ሌላ አማራጭ ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱ መጽሃፍ ቅዱስ ወይንም ኮራን አይደለም። የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም አቋማቸውን መመራመር አለባቸው፤ ዓለም ንቋቸዋል!!
“ተፎካካሪ ፓርቲዎች” በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ይውሰዱ የምለው ወሳኝ ብሄራዊና ሕዝባዊ ጥያቄ ስለሆነ ነው። እያንዳዱ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር፤ ቤትና ንብረት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ መብትእንዲኖረው ያስፈልጋል። ዘመናዊነት ማለት ይኼው ነው። አብሮነት ማለት ይኼው ነው!!
የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመኖር፤ መሬት፤ ቤትና ሌላ ንብረት የመያዝ፤ የመንቀሳቀስ፤ የመናገር፤ የመምረጥና የመመረጥ መብት ካልተከበረ የማንም መብት አይከበርም። ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ለዚህ መብት ማነቆ ሆኗል። በ March 14, 2019,
the Guardian, Shadow Falls over Ethiopia’s Reforms በሚል እርእስት በጌድዮ ስለተከሰተው ብሄር ተኮርና የሚያስደነግጥ የአንድ ሚሊየን ወገኖቻችን ፍልሰት፣ ረሃብ፤ ከርሃብና ከጠለላ ጋር የተያያዘ በሽታ እንዲህ ሲል ጠቁሟል። “Despite reports of lynchings, rapes and beheadings, the Ethiopian government is trying to force people displaced by conflict to return to their villages.” የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች እንደሚሉት፤ በእነዚህ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰው ሰው ሰራሽ ረሃብ “full-blown humanitarian crisis” ደረጃ ላይ ደርሷል። “The dire situation facing millions of people forced from their homes by conflict, and the new regime’s approach to their plight, has invited a more sceptical response from some observers.”
የዓለም ሕዝብና ልዩ ልዩ መንግሥታት ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድን ከፍ አድርገው ያመሰግኑትን ያህል፤ በእነዚህና በሌሎች ብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ላይ በደረሰው ፍልሰትና ረሃብ ምክንያት የዐብይን መንግሥት የአስተዳደር ችሎታ መጠራጠር መጀመራቸው በዘገባው ላይ ተጠቁሟል። በኔ እምነት ግን፤ እኒህ መሪ ብቻቸውን የደለበውንና ስር የሰደደውን ብሄር ተኮር አገዛዝ ለመቅረፍ አይችሉም። “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” የሚፈተኑበት አንዱ አስኳል ጉዳይ በለውጡ ላይ ያላቸው አቋምና ተሳታፊነት ነው።
በሶስተኛ የምጠቅሰው ዘገባ በታወቀው የዩጋንዳው ተወላጅና በኮለምቢያ ዩንቨርስቲና በማክሬሪ በሚያስተምረው ምሁር በ ፕሮፌሰር ማህሙድ ማህዳኒ በ ኒውዮርክ ታይምስ January 3, 2019 The Trouble With Ethiopia’s Ethnic Federalism በሚል አርእስት የተጻፈውን ሃተታ ጭማቄ ነው። “The 1994 Constitution, introduced by Prime Minister Meles Zenawi and the Ethiopian People’s Revolutionary Democratic Front governing coalition, recast the country from a centrally unified republic to a federation of nine regional ethnic states and two federally administered city-states. It bases key rights — to land, government jobs, representation in local and federal bodies — not on Ethiopian citizenship but on being considered ethnically indigenous in constituent ethnic states. “
መለስ ዜናዊ፤ ቡድኑና የዘውግ አጋሮቹ የወደፊቱን የግጭት፤ የንትርክ፤ የመበታተን በር ከፍተው መለስ አልፏል። ለአሁኑና ለተከታታይ ትውድ ያላለፈው አደገኛ “ጥሪት” ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጽንፈኛነት፤ ሌብነትን፤ ጠብ ጫሪነትን፤ ጥላቻን፤ ስጋትና ፍርሃትን ጭምር ነው። ይህ የፖለቲካ ባህል መቀበር አለበት።
የችግሩ እምብርት ይኼው ነው። ለውጥ አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ሆኖ ቢገኝም፤ ህወሓትና ኦዴፓ “በዘውግ ተኮሩ ሕገ መንግሥትና በክልላዊው የአስተዳደር ቅርጽ “መደራደር አይቻልም” ይላሉ። ጠ/ሚንስትሩ ይኼን ፈተና እንዴት እንደሚወጡት መልስ የለኝም። ፕሮፈሴር ማህዳኔ ችግሩን ሲያብራራ እንዲህ ይላል። “The reforms by the
country’s new prime minister are clashing with its flawed Constitution and could push the country toward an interethnic conflict…..As in the Soviet Union, every piece of land in Ethiopia was inscribed as the ethnic homeland of a particular group, constitutionally dividing the population into a permanent majority alongside permanent minorities with little stake in the
system. Mr. Zenawi and his party had both Sovietized and Africanized Ethiopia.” ይህ ከጽንሰ ሃሳቡ
ጀምሮ የተዛባ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ሕዝብን ከሕዝብ እየከፋፈሉ ለመግዛትና ለማጋጨት ወሳኝ መሆኑን በመረጃ አቅርቤዋለሁ። በተጨማሪ፤ ለመገንጠል እንዲያመች የታሰበ እንጅ ለብሄራዊ አንድነት የተመሰረተ አይደለም።
ባለፉት ሃያ ስምንት ዓመታት በተደጋጋሚ በሚታይ፤ በሚዳሰስ፤ በሚለካና በሚዘገንን ደረጃ እኔ ብቻ ሳልሆን የዓለም ተመልካቾች ያሳሰቡት ይህ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት እንደሚችል ነው። ተመራማሪውና ምሁሩ
እንደሚለው “Like much of Africa, Ethiopia is at a crossroads. Neither the centralized republic instituted by the Derg military junta in 1974 nor the ethnic federalism of Mr. Zenawi’s 1994 Constitution points to a way forward. Mr. Abiy can achieve real progress if Ethiopia embraces a different kind of federation — territorial and not ethnic — where rights in a federal unit are dispensed not on the basis of ethnicity but on residence. Such a federal arrangement will give Ethiopians an even chance of keeping an authoritarian dictatorship at bay. The system of ethnic federalism was troubled with internal inconsistencies because ethnic groups do not live only in a discrete “homeland” territory but are also dispersed across the country. Nonnative ethnic minorities live within every ethnic homeland.
ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ በራሳቸው ፓርቲ፤ ማለትም በኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አማካይነት በኢህአዴግ መመረጣቸው አያከራክርም። ሆኖም፤ እኒህን መሪ ብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን የወደዷቸው፤ ያከበሯቸውና የደገፏቸው የአንድ ፓርቲ ወይንም የአንድ ዘውግ ተወካይ በመሆናቸው አይደለም። ይህንማ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልቀበልም ብሎ ህወሓትን ከሥልጣን አውርዷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እኒህን መሪ በቀጥታ ባይመርጣቸውም፤ በተዘዋዋሪ ግን የቆሙበትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መአከል ያደረገ እሴትና መርሆ በማክበር እንደ ኢትዮጵያዊ መሪ ተቀብሏቸው ቆይቷል። “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞትኢትዮጵያ” የሚለው የተቀደሰና ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ተደፍኖና ተቀብሮ የነበረው ብሄራዊ መስፈርት አብቦ ስር ይሰዳል የሚል እምነቴ አሁንም ጠንካራ ነው።
ጠ/ሚንስትሩ በቅርቡ በውይይት ላይ የተናገሩት ፍሬ ነገር ከላይ የጠቀስኩትን መተኪያ የሌለው መንፈስ፤ እሴትና መርሆ ያጠናክራል። “ይህችን ታላቅ አገር ተቀራርቦ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም…..ኢትዮጵያ አትበተንም፤ አንተ እስከ ሃሳብህ ትበተናለህ እንጅ” ብለዋል።
በኔ ጥናትና ምርምር፤ ለኢትዮጵያና ለ 110 ሚሊየን ሕዝቧ ገና በቀላል ቋንቋ ያልቀረበው የፍኖተ ካርታ አካል ሕዝቡን የሚያሳትፍና የሥልጣኑ ባለቤት የሚያደርግ ዲሞክራሳዊ መስተጋብር እና ይህንን መስተጋብርና አቅጣጫ የሚያጠናክሩ ብሄራዊ ተቋማት አለመመስረታቸው ነው።
በመጨረሻ፤ “ተፎካካሪ ፓርቲዎች” የሕዝብን ልብና ትርታ ለመሳብ የሚችሉት የኢትዮጵያ ነጻነትና ሉዐላዊነንት ለድርድር አይቀርብም በሚልና የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት እንደ ብረት የጠነከረ ነው ብለው በማንም ኃይል እይናጋም ለማለት ሲደፍሩ ነው። የተባበረ ሕዝብ ድህነትን ይቀርፋል፤ ያልተባበረ ግን የኑሮና የገቢ ልዩነቶችን ያጠናክራል።
እነዚህን አቅጣጫዎች መገንዘብና ለውጡ ስር እንዲሰድ ማድረግ የተቀደሰና የተከበረ ዓላማ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትንር!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ይለምልም!!