1. ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡ ጃንጥራር አባይ የጠቅላይ ሚንስትሩ የኮንስትራክሽን ጉዳዮች አማካሪ፣ ጠይባ ሐሰን የጠቅላይ ሚንስትሩ ማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ፣ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ እና ገዛኸኝ አባተ ደሞ የኢትዮጵያ ሆቴሎችና ቱሪዝም ማሰለጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አድርገው ሹመዋል፡፡
2. የአዲስ አበባ ከተማ መሰተዳድር ለቀበሌ ቤቶች የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እያዘጋጀ መሆኑን ካፒታል አሰነብቧል፡፡ ዐላማው ማን ምን ዐይነት የቀበሌ ቤቶችን እንደያዘ መረጃ መሰብሰብና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን መከላከል ነው፡፡ ምዝገባውን የሚያካሂደው የከተማዋ መሬት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ነው፡፡ ቀበሌ ቤቶች በሙስናና በሕገ ወጥ መንገድ ለሌሎች ይተላለፋሉ፡፡ እስካሁን ከተመዘገቡት 153 ሺህ ቤቶች መካከል ለባለቤትነት ምስክር ወረቀት ብቁ ሆነው የተገኙት 26 ሺህ ያህሉ የባለቤትነት ምስክር ወረቀት ወደሚሰጡ የወረዳ አስተዳደር ቢሮዎች ተልከዋል፡፡
3. በደቡብ ክልል በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ 28 ጉማሬዎች ሞተው መገኘታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡ ጉማሬዎቹ መሞት የመሩት ካፈው ዕሁድ ጀምሮ ነው፡፡ የሞታቸው መንስዔ አልታወቀም፡፡ የፓርኩ ሃላፊ ባህሯ ሜጋ 15ቱ ጉማሬዎች ባንድ ቀን እንደሞቱና በዕድሜ አንጋፋቸዎች በብዛት እንደሞቱ ተናግረዋል፡፡ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እና ከሰበታ ብሄራዊ እንስሳት ጤና ምርምር ማዕከል የተውጣጣ ቡድን ወደ ቦታው ማምራቱን የዘገበው ደሞ ፋና ብሮድካስት ነው፡፡
4. በረከት ስምዖን እና ታደሠ ካሳ አራት ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡ አንደኛው ክስ ተከሳሾቹ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳጥረው የዳሽን ቢራ ፋብሪካን 50 በመቶ የአክስዮን ድርሻ ያለአግባብ በመሸጥ በጥረት ኮርፖሬት ላይ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረሳቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ክስ “ስማርት ኤሌክትሪክ ውሃ ዊንድ ጄኔሬተር ኩባንያ” ከጥረት ኮርፖሬት 1.3 ቢሊየን ብር ቢተላለፍለትም ኩባንያው ወደ ሥራ አልገባም የሚል ነው፡፡ በሦስተኛው ክስ “ድቬንትስ ዊንድ” ለሚባል ኩባንያ የባንክ ዕዳ ከጥረት ኮርፖሬት አንዲከፈለው በማድረግ ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረስ የሚሉ ክሶች ተጠቅሰውባቸዋል፡፡ ከግልና የመንግስት ባንኮች ራሳቸው ያለባቸውን ብድርም ጥርት እንዲከፍል አድርገዋል- ይላል ክሱ፡፡ ተከሳሾቹ መቃወሚያቸውን በጽሁፍ ማቅረባቸውን የአማራ መገናኛ ብዙኻን ዘገባ ያመለክታል፡፡
5. የቡሬ-አሰብ መንገድ ዛሬ ጧት ተዘግቷል፡፡ DW እንደዘገበው መንገዱ የተዘጋው ከኤርትራ በኩል እንደሆነ የአፋር ክልል ኮምንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገልጧል፡፡ መንገዱ የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም ስምምነትን ተከትሎ ባለፈው ታሕሳስ ነበር የተከፈተወ፡፡ ለጊዜው ምክንያቱ ባይታወቅም ምናልባት የድንበር ንግዱን መስመር ለማስያዝ ሊሆን እንደሚችል የአካባቢው ነዋሪዎች ግምት አላቸው፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለዛሬው ርምጃ የተባለ ነገር የለም፡፡ ቀደም ሲል የሁመራ-ኦምሃጃር፣ የራማ-አዲኳላ እና የዛላንበሳ ዐዲ ቀይህ መንገዶች መዘጋታቸው ይታወሳል፡፡
6. ዛሬ በሦስት ቦታዎች የሕክምና ተማሪዎች እና ተለማማጆች ተቃውሞ ስልፍ አድርገዋል፡፡ አዲስ ስታንዳርድ እንደዘገበው ተቃውሞ በጥቁር አንበሳና ቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል እና ጎንደር ዩኒቨርስቲ ነው የተደረገው፡፡ የጥቁር አንበሳ ሕክምና ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት በአርሲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ ፖሊስ የፈጸመውን ድብደባ ተቃውመዋል፤ ጥፋተኞችም በሕግ ይጠየቁ ብለዋል፡፡ የተለያዩ ትምህርት ተቋማት የሕክምና ተማሪዎች የሥራ ዕድል ዕጦት እና ሌሎች አስተዳደራዊ ጥያቄዎቻቸው እንዲሟሉላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ሸገር በበኩሉ አድማ ላይ የሰነበቱት የጅማና አርሲ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬ ወደ ሥራ እንደሚመለሱ ዘግቧል፡፡
7. የጊንጪ ከተማ አስተዳደር ለዐመታት ከኖርንበትና ከምንነግድበት ቤት ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያና አፈናቅሎናል- ብለዋል ነዋሪዎች፡፡ ሸገር አቤቱታ አሰሚዎቹን ጠቅሶ እንደዘገበው አስተዳደሩ ከመኖሪያ ቤታቸው እና ንግድ ቦታቸው ያስለቀቃቸው ያለ በቂ ውይይት እና ጊዜ ነው፤ አቤቱታ አሰሚዎቹ አሰተዳደሩ ምትክ ቦታዎች አልሰጠንም ብለዋል፡፡ አስተዳደሩ በበኩሉ ርምጃው የተወሰደው ለልማት ሲባል ነው፤ የተወሰኑት ደሞ የራሳቸው ቤተ እያላቸው የቀበሌ ቤቶችነ ስለያዙ ለቤት አልባ ድሃዎች አከፋፍያለሁ ይላል፡፡