1. ቻይና እስካለፈው የፈረንጆች ዐመት ለኢትዮጵያን ያበደረችውን ብድር ወለድ ሰርዛለች ብሏል የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት፡፡ ለ“ቤልት ኤንድ ሮድ” ጉባኤ ቻይና የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከቻይና ጋር የ1.8 ቢሊዮን ዶላር የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያና ማሰራጫ ላይ ተፈራርመዋል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ለኢትዮ-ጅቡቲ 2ኛ ኤሌክትሪክ መስመርና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ሃይል አቅርቦት ይውላል፡፡ አዲስ አበባን ለሚያስውበው ፕሮጀክት ገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች የቴክኒክ፣ ትብብርና ምግብ ዕርዳታ ስምምነቶችም ተፈርመዋል፡፡ ቻይና ቀደም ሲል ለኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ሐዲድ ዝርጋታ የሰጠችውን ብድር መክፈያ ጊዜ ከ10 ወደ 30 ዐመት ማራዘሟ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በጠቅላላው የ15 ቢሊዮን ዶላር የቻይና ብድር አለባት፡፡
2. የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ የሞቱት ጉማሬዎች ተመዘርዘው ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አለኝ ማለቱን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ በአካባቢው የተሰማራው መርማሪ ቡድን ምርመራውን እንደቀጠለ ነው፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት በጊቤ ፓርክ 28 ጉማሬዎች በፓርኩ ባልታወቀ ምክንያት ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል፡፡
3. የዲፕሎማቲክ መብት ባለው የጀርመን ተራድዖ ድርጅት (ጅአይዜድ) ስም በሐሰተኛ ሰነዶች የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን ከውጭ ሲገቡ ጉምሩክ ላይ መያዛቸውን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ በዚሁ ወንጀል የተጠረጠሩ 3 የጅአይዜድ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የወጡ በማስመሰል የተሰሩ የተጭበረበሩ ሰነዶችን ተጠቅመው ነበር ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ለማስገባት የሞከሩት፡፡ ከተያዙት መካከል መድሃኒቶች፣ የሞባይል ስክሪኖች፣ ካሜራዎችና የመኪና መለዋወጫዎች ይገኙበታል፤ ግምታቸውም የ219 ሚሊዮን ብር ያህል ነው፡፡
4. በባሕር ዳር የሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና በፈለገ ሕይወት እስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ የሆስፒታሉ አገልግሎት እክል ገጥሞታል፡፡ ሸገር እንደዘገበው በሆስፒታሉ የሕክምና ትምህርት ተስተጓጉሏል፤ ሕሙማንም አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም፡፡ የሆስፒታሉ አስተዳደር የዩኒቨርስቲው የሕክምና ተማሪዎች ታካሚዎችን አልጋ ላይ ጥለው አድማ መትተዋል ሲል ይከሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕክምና ተማሪዎች ማኅበር በበኩሉ ሰሞኑን በተለያዩ ተቋማት የሕክምና ተማሪዎች ያነሷቸው ቅሬታዎች የመላው ሕክምና ተማሪዎችና ሐኪሞች የሚመለከት መሆኑን እንደገለጸ DW ዘግቧል፡፡
5. ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አንድን የወንጀል ተጠርጣሪ ትውልደ ኢትጵያዊ ለአሜሪካ አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑ ጥያቄ ማስነሳቱን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ተጠርጣሪው ዮሃንስ ነሲቡ በ2 ሰዎች ግድያና ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር በአሜሪካ እንደሚፈለግ ዐቃቤ ሕግ ይጠቅሳል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ከአሜሪካ ጋር ወንጀለኛን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት የላትም፤ ዐቃቤ ሕግም ለውሳኔው ሥልጣን የለውም ይላሉ የሕግ ባለሙያዎች፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪውን እንዲመረምርም ሆነ አሳልፎ እንዲሰጥ ከአሜሪካ ጥያቄ ስለመቅረቡ ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ጠበቆች ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ላይ እግድ እንዲጥል ጠይቀዋል፤ ፍርድ ቤቱ ግን አሳልፎ የመስጠት ጉዳይ አልተነሳልኝም በማለት የተጠርጣሪው የአካል ደኅንነት መብት እንዲጠበቅ አዝዞ መዝገቡን ዘግቷል፡፡
6. ከታንዛኒያ እስር ቤቶች 288 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን አስፈትቻለሁ- ብሏል በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ፡፡ 253ቱ የተፈቱት ከኡኮንጋ እና ሴጋሪያ ከተባሉ እስር ቤቶች ሲሆን ቀሪዎቹ ደሞ ከሞሮጎሮ እስር ቤት ነው፡፡ ስደተኞቹ በተለያዩ ወንጀሎች እስር ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆኑ ዛሬ ሌሊት ሀገራቸው ይገባሉ፡፡ ቀደም ሲልም ኢምባሲው 600 ያህል እስረኞችን ከታንዛኒያ አስፈትቷል፡፡
7. የአማራ ክልላዊ መንግሥት ሰሞኑን በማሕበራዊ መገናኛ ብዙኻን ለተሰጡት አስተያየቶች ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በቅርቡ አምቦ ላይ በተካሄደው የአማራ-ኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ላይ ኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ሕገ መንግሥዊ ጥቅም እንዲከበር እንታገላለን በማለታቸው በመገናኛ ብዙኻን ተተችተው ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ የበላይ መመሪያችን ነው፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ጥቅምና ለተፈጥሮ ሃብት የጋራ አስተዳደር ላይ ክልሉ ለሚኖረው ጥቅም ለመታገል የግድ ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም- ብሏል የክልሉ መግለጫ፡፡ ነጠላ አጀንዳዎችን ነጥሎ ከማውጣት ይልቅ ትልቁ ስዕል በሆነው የሁለቱ ሕዝቦች ዘላቂ ግንኙነት ላይ ማተኮር እንደሚገባም አስምሮበታል፡፡