የዛሬ ሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ሰኞ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ ግጭት 18 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀሰው በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ሲሆን መነሻው በመኪና ጭነት ክፍያ ሳቢያ በተነሳ ጠብ እንደሆነ የአማራ መገናኛ ብዙኻን የአማራ ክልልን ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮሎኔል አለበል አማረን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ለሶስት ቀናት በቀጠለው ግጭት የሽናሻና ጉሙዝ ብሄረሰብ ተወላጆች ከአማራ ብሄረሰብ ተወላጆች ጋር የተጋጩ ሲሆን ከሟቾቹ 11ዱ ከአማራ ብሄረሰብ ናቸው፡፡ ፌደራል ፖሊስ ከአማራ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር ፓዌ ከተማ ላይ የጋራ ዕዝ አቋቁመው ግጭቱ እንዳይዛመት በማድረጋቸው ከትናንት ጀምሮ ተረጋግቷል፡፡

2. ባለፉት 9 ወራት ኢትዮጵያ ከወጭ ንግድ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ አግኝታለች፡፡ ሸገር ንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው ገቢው ከሃች አምናውም ይሁን በዕቅዱ ከተያዘው 3.1 ቢሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ ገቢው የተገኘው ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እና ከግብርናና እንስሳት ውጤቶች ነው፡፡ ላኪዎች ማሟላት የሚገቧቸውን መስፈርቶች አለማሟላታቸው፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ተፈላጊ ግብዓቶች በቀላሉ አለመገኘታቸውና ኮንትሮባንድ ለገቢው ማሽቆልቆል ምክንያት ናቸው፡፡

3. 100 ያህል የከባድ መኪና ሹፌሮች ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን DW ዘግቧል፡፡ ከሰልፈኞቹ በተለያዩ ቦታዎች በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ ሹፌሮች አሉበት፡፡ አፈና፣ ግድያ ይፈጻማል፤ በሕገ ወጦችም ገንዘብ እንጠየቃለን ብለዋል- ሰልፈኞቹ፡፡ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጣቸው ሥራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉም አስጠንቅቀዋል፡፡ ሥራ ላይ ሳሉ ባልታወቁ አካላት የተገደሉ ሼፌሮችን ፎቶም ይዘው ታይተዋል፡፡ በርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ያነጋገራቸው ባለሥልጣን የለም፡፡

4. በሰሞኑ የቤንሻንጉል ግጭት የተጠረጠሩ 15 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ በተቀሰቀሰባት ማምቡክ ከተማና በዙሪያዋ ባሉ 5 ቀበሌዎች ግጭቱን ለመፍታት ሕዝባዊ ውይይት ዛሬ መጀመሩን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ግጭቱ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኻን ተጋኖ ቀርቧል- ብለዋል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

5. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻንጊ አየር መንገድ ሽልማትን አሸንፏል፡፡ ሽልማቱን ያሸነፈው በአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የመንገደኞች ብዛት ዘርፍ ከፍተኛ የመንገደኞቹን ዕድገት በማሳየት ቀዳሚ በመሆኑ እንደሆነ አየር መንገዱ በትዊተር ገጹ ገልጧል፡፡ ቻንጊ የቻይና አየር መንገድ ነው፡፡

LEAVE A REPLY