በፀጥታ ስም የህዝብን ድምፅ ማፈን ይቁም! || ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ

በፀጥታ ስም የህዝብን ድምፅ ማፈን ይቁም! || ዶ/ር ቃልኪዳን ነጋሽ

ዛሬ በዲላ ከተማ ሊካሄድ የነበረዉ ሰላማዊ ሰልፍ ከላይ በወረደ ቀጭን ትዕዛዝ በፈዴራል እና የክልል ፀጥታ አካላት ጣልቃ ገብነት ትላንት ከረፋዱ ላይ ተከልክሏል። ከምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች የተፈናቀለዉን የጌዴኦ ህዝብ ድምፅ ለማሰማት የተጠራዉ ሁሉን አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለሁለተኛ ግዜ እየተራዘመ መሆኑ ነዉ።

መንግስት ሰላማዊ ሰልፉን ለምን እንደፈራዉ ግልፅ አይደለም። “ከክልልና ከፌዴራል ፀጥታ በኩል በደረሰን መረጃ መሰረት… በሰላማዊ ሰልፍ በተጠራ ህዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ” የሚለዉ ምክኒያት ያስገርማል። በህዝብ ላይ ጭፍጨፋ እና ዕልቂት ሲፈፀም ግድ ያላለዉ መንግስት ደርሶ “በህዝብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ” እያለ ለህዝብ አሳቢ ተቆርቃሪ ሲሆን ማየት እጅግ ይደንቃል።

ለመሆኑ በህዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ ያለመዉ አካል ማን ይሆን የሚለዉ ጥያቄ መጠየቅ ይኖርበታል። ምናልባትም እራሱ መንግስት ወይም ከላይ የተጠቀሱት የፀጥታ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ። በደብዳቤዉ ባይካተትም ሰልፉን በከለከለዉ (ባስከለከለዉ) የፀጥታ አካል (አካላት) የተሰጠዉ ምክንያት ኦነግ በአከባቢዉ ካለዉ እንቅስቃሴ አንፃር የፀጥታ ችግር ስላለ የሚል ነበር። “ከኦነግ የሚመነጭ የፀጥታ ችግር ስላለ ፀጥ በሉ” የሚለዉን የመንግስት ሎጅክ “ኦነግ የማፈናቀል ስራዉን በተሳካ ሁኔታ እስኪያጠናቅቅ ፀጥ በሉ” ብለን ሰምተነዋል። ወይስ ኦህዴድ እንደለመደችው በኦነግ ስም እየነገደች ነዉ???

ሌላዉ የሚገርመዉ ነገር ለህዝብ አሳቢዉ ፀሃዩ መንግስታችን በአንድ በኩል ኦኔግ በአካባቢዉ ካለዉ እንቅስቃሴ አንፃር ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ሰልፍ ይቅርባችሁ እያለ በሌላ በኩል ተፈናቃዩን ህዝብ በኦነግ ቁጥጥር ስር በዋሉ አካባቢዎች እና ከኦነግ ዉግያ በገጠመባቸዉ አካባቢዎች በግዳጅ ለሶስተኛ ግዜ ጭኖ ለማስፈር መራራጡ ነዉ። እዉነታዉ መንግስት ከህዝብ ሞት እና እልቂት በላይ ሰላማዊ ሰልፍ ይፈራል። ሰሞኑን (ከቀናት በፊት) የተለመደዉን ፌክ የእርቅ ስነ ስርዓት ተከትሎ የመጣዉ የተዋከበ ተፈናቃዮችን አስገድጄ ለ3ኛ ግዜ መልሳለሁ ዉሳኔም አንዱም ምክንያት ሰልፉን ፍራቻ እንደነበር ለመረዳት ይቻላል።

ለማንኛዉም ሰላማዊ ሰልፉን በተደጋጋሚ እንዲራዘም ያደረገ መንግስት “ላልተወሰነ ግዜ” የሚለዉን ቀልዱን ትቶ የተቆረጠ ቀን እንዲሰጠን እንፈልጋለን። ህዝብ ላይ የሚፈፀም በደል እና ጥቃት ማስቆም ያልቻለ መንግስት ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ቢከለክል እና እድሜዉን ለአንድ ሀሙስ ቢያስረዝም ነገ የባሰ ማዕበል መጥቶ እንደሚወስደዉ ሊረዳዉ ያስፈልጋል።

በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ባልተፈቀደ ሰልፍ የወጡ ሰልፈኞች እየጨፈሩ በዞኖቹ ያለዉን የጌዴኦ ህዝብ እንዲገሉ እና እንዲያፈናቅሉ የፈቀደ መንግስት የዲላ እና የአካባቢዉ ልጆች ቲሸርት ለብሰን የህዝቡን ድምፅ እናሰማ ብለዉ የመንግስት ቢሮዎችን ነጋ ጠባ እያንኳኩ ቆይተዉ የተፈቀደላቸውን ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል ብዙ ያስተዛዝባል።

ወይስ እኛም ሰልፍ እንዲፈቀድልን ክልልነት እንጠይቅ? ክልልነት የሚፈታዉ ችግር አይደለም የገጠመን ብለን እንጂ እሱንም ፈርተን እንዳይመስላችሁ የተዉነዉ። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሌሎች በክልሉ ያሉ ብዙ ዞኖች እንዳረጉት ሁሉ በማንኛዉም ሰዓት መወሰን ይቻላል። የጋራ አገር እንስራ ብለን እንጂ ከደረሰበት መጠነ ሰፊ ጥቃት አንፃር ጌዴኦ እንደዉ ክልል ይቅርና አገር መጠየቅ ያንሰዋል?

በፀጥታ ስም የህዝብን ድምፅ ማፈን ይቁም!

ኢህአዴግ በአፈና የሚመጣ ፀጥታ ዘላቂነት እንደማይኖረዉ ሌላዉ ቢቀር ከራሱ ታሪክ ይማር!

ፍትህ ለጌዶኦ ህዝብ!

ፍትህ የመፈናቀልና ሞት ፅዋን እንዲጎነጩ ለተፈረደባቸዉ ኢትዮጵያዊያን!

LEAVE A REPLY