የዛሬ ረቡዕ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ረቡዕ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. በቤንሻንጉል ክልል ዛሬም ጸጥታ አለመረጋጋቱን ነዋሪዎችን ጠቅሶ የአማራ መገናኛ ብዙኻን ድርጅት ዘግቧል፡፡ በተለይ የፓዌ ወረዳ ጸጥታ ገና አልተመለሰም፡፡ በማምቡክ ወረዳ ደሞ ዛሬ ባገረሸ ግጭት የአንድ ሰው ሕይወት በማለፉ ውጥረቱ ነግሷል፡፡ ነዋሪዎች ቆታ እና አይሲዳ በተባሉ አካባቢዎች ተገድለው ጫካ ውስጥ የተጣሉ ሬሳዎችን ማንሳት አልቻልንም፤ ጫካ የጠፉ ከብቶቻችንም ማፈላለግ አልቻልንም ይላሉ፡፡

2. የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ እና አንድነት ሀገር ዐቀፍ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ችግሮች በቅደም ተከተል እንዲፈቱ ጉባዔው አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ጠይቀዋል፡፡ የሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር ኢድሪስ ባደረጉት ንግግር…

3. የዐለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ለጉብኝት አዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውንም የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ ባለፈው ወር ለባንኩ የተሾሙት አዲሱ ፕሬዝዳንት ሌሎች ሁለት የአፍሪካ ሀገራትንም ይጎበኛሉ፡፡

4. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የፍርድ ቤት እገዳ እንዲነሳለት ጠይቆ ከሳሾች እንደተቃወሙት ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በ98 ከሳሾች ሳቢያ 18 ሺህ ባለዕጣዎች ተጠቃሚነታቸው መስተጓጎል የለበትም፤ እገዳው ወደፊትም በዕጣ ቤቶችን እንዳላስተላልፍ አግዶኛል፤ ቤቶቹን ባለማስተላለፌ በቀን ከ5 ሚሊዮን፣ በወር ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ሊደርስብኝ ይቻልል፤ ከዕጣ የታገዱት ቤቶችም የባንክ ወለድ ዕዳ ያስከትሉብኛል በማለት እግዱ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡ ከሳሾች በበኩላቸው መቶ በመቶ የከፈሉ 21 ሺህ ተመዝጋቢዎች እንዳሉ ገልጸው እገዳው ከተነሳ በቤቶቹ ላይ ያላቸው መብትና ጥቅም እንደሚጎዳባቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዝያ 30 ቀጥሯል፡፡

5. የኦሮሞ-ሱማሌ ሕዝብ ለሕዝብ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ መድረኩ ግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች ከሱማሌ ክልል ከተፈናቀሉበት የታች አምናው ግጭት ወዲህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በመድረኩ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ ኡጋዞች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አባ ገዳዎችና የኦብነግ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ የሱማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር ወደፊት ሁለቱ ሕዝቦች ወሰናቸውን ከፍተው በንግድ መተሰሰር አለባቸው ብለዋል፤ በአዳማ ዙሪያ ያሉ ተፈናቃዮችን ገብኝተውም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና የማቋቋሚያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሕዝቦቹን ግንኙነት ለማጠናከር የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትወርክ በሱማሌኛ ቋንቋ ስርጭት ይጀምራል ብለዋል፡፡

6. ኢትዮ ቴሌኮም ሃብቱን በውጭ ኩባንያ እያስመረመረ መሆኑን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ መርማሪው የእንግሊዙ ፕራይስ ወተር ሃውስ ኩፐር የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ካሁን በፊት የኢትዮ ቴሌኮምን የፋይናንስ አስተዳደርና የሒሳብ አያያዝ ሥርዓት አደራጅቷል፡፡ ጥናቱ እስከ 6 ወራት ሊፈጅ ይችላል፡፡ የሃብት ግምቱ ሲጠናቀቅ ዲሊዮት የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያና ኧርነስት ኤንድ ያንግ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ደሞ ኢትዮ ቴሌኮም በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ባለሃብቶች ሲዘዋወር የአክሲዮን አወቃቀርና ሽያጭን በተመለከተ እንዲያማክሩ ተቀጥረዋል፡፡ የአማካሪ ኩባንዎችን ወጭ ዐለም ባንክና ለጋሽ ሀገራት ይሸፍናሉ፡፡ አጠቃላይ ሂደቱ የሚመራበት ረቂቅ ሕግ ገና በፓርላማ አልጸደቀም፡፡

7. አራተኛው የ“ጣና ፎረም” ስብሰባ ከነገ ወዲያ ዐርብ በባሕር ዳር ከተማ ይካሄዳል፡፡ መድረኩ በአፍሪካ ቀንድ በሚቀያየሩት ጅኦፖለቲካዊ ሁኔታዎች ላይ ይመክራል፡፡ በተለይም ተቀያያሪው ጅኦፖለቲካ በአፍሪካ ኅብረትና ተመድ ጸጥታ ሥራዎች ምን አንድምታ እንዳለው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክር ፎረሙ በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY