ዶ/ር አብይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው። በሥራቸው የአየር ኃይል; የምድር ጦር; የፖሊስ ሠራዊት … በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጁ ኃይሎች አሉ። ከዚህ በተጓዳኝ ማንኛውንም መረጃ አነፍንፎ ማግኘት/ማሰባሰብ; አጠናቅሮና ተንትኖ ማቅረብ የሚችል; በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የሚታገዝ የደህንነት መ/ቤት አለ። በተዋረድ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ያለው አደረጃጀትም (ክፍተቶች እንደሚኖሩት ቢገመትም) ዛሬም እንዳለ ነው።
በዚህ ሁኔታ; መንግሥት ህግና ሥርዓትን ለማስከበር የማይችለው ምን ይዞት ይሆን? የመንግሥት ተቀዳሚ ተልዕኮና ተግባር ህግና ሥርዓት ማስከበር መሆኑን ያለማቋረጥ እየወተወትን ነው። የህዝቡ መሠረታዊ ፍላጎትም ይኸው ነው። ህዝቡ ከምንም በላይ በሰላም ወጥቶ መግባትና የዳቦ ፍላጎቱን ማሟላት ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ዋስትናው አስተማማኝ ሠላም ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን እዚያም እዚህም ሠላምን የሚያውኩና የህዝቡን ሥጋትና ፍርሃት የሚጨምሩ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው። በዚህ ሁኔታ; ነገ – ከነገ ወዲያ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማንም በእርግጠኝነት መናገር/መገመት አይችልም። መንግሥትም የመረጃና ደህንነት መዋቅሩን ተጠቅሞ ሠላምን ሊያደፈርሱ የሚችሉ ግጭቶችና ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አዝማሚያውን ገምግሞ የመከላከል እርምጃ ሲወስድ አይታይም። ሠላምን የሚያደፈርሱ ግጭቶችና ችግሮች ሲፈጠሩም የመንግሥት ኃይሎች ፈጥነው መድረስና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ እንደማይችሉ የታዘብንባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው።
ብዙውን ጊዜ የመንግሥት ኃይሎች የሚደርሱት ዜጎች ከተገደሉ; ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉና ሊመለሱ የማይችሉ ጉዳቶች ከደረሱ በኋላ ነው። አንዳንዴማ መንግሥት መረጃውም የሚደርሰው በጣም ዘግይቶና (በሶሻል ሚዲያው ሳይቀር ሲንሸራሸር ከርሞ) ፀሐይ ከመታው በኋላ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም; ዜጎች መንግሥት የተጣራና/የተረጋገጠ መረጃ እንዲሰጣቸው ደጋግመው ሲወተውቱ ይሰማል። ከዚህ ጋር በተያያዘም; መንግሥት ተገቢውንና ትክክለኛውን መረጃ በወቅቱ ለህዝብ የመስጠት ኃላፊነትና ግደታውንም የዘነጋ ይመስላል።
አሁን ሁሉም በየጎጡ የሚያንቀሳቅሰው ኃይል እየፈጠረና/እያጠናከረ ነው። በፈለገ ጊዜ የፈጠረውን/የገነባውን ኃይል ሊያንቀሳቅስና የራሱን እርምጃ ሊወስድ ይችላል። ከዚህም በተጓዳኝ; ለፈለገው ዓላማ; በፈለገው መንገድ መረጃ ማሰራጨት የሚችልባቸው ሚዲያዎች ባለቤት ሆነዋል; እየሆነም ነው። ከዚህም በመነሳት ህዝቡ ትኩረቱን ወደነዚህ ኃይሎች ማዞሩ ግድና የሚጠበቅም ነው። በዚህ መሐል ግን አሁንም የሚነሳ ጥያቄ አለ።
የዶ/ር አብይ መንግሥት; መንግሥታዊ አቅሙን ለመጠቀምና ህግና ሥርዓትን ለማስከበር የያዘው ምን ይሆን? በዚህ ሁኔታ; መጨረሻውስ ምን ይሆናል? ወይስ ከመጋረጃ በስተጀርባ ለእኛ የማይታዩንና የማናውቃቸው የረቀቁ የደህንነትና የመከላከያ ሥራዎች እየተሠሩ ይሆን? ወይስ እዚያም እዚህም ለሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤ የሆኑ ስሜቶች በሂደት ሊሰክኑ ይችላሉ በሚል መንግሥት ሆደ ሰፊነቱን እያሳዪን ይሆን? ይህም ቢሆን ሊያግባባን አይችልም። አገር በሙሉ የሥርዓት አልበኞች መፈንጫ ሲሆን መንግሥት በራሱ ምክንያት ዝምታን ከመረጠ በዜጎች ህይወትና ደህንነት ላይ አጉል ቁማር መጫወት ይሆናል።
ለማንኛውም ጉዳዩ አሳሳቢና አነጋጋሪ ነው።
የዶር አብይ መንግሥት ህግና ሥርዓትን ለማስከበር ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው?