በብሔር መደራጀት መብትህ ነው። ባህልህን፣ ቋንቋህን፣ ታሪክህን እና ሌሎች የማንነትህ መገለጫ የሆኑ እሴቶችህን የማጎልበት እና ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰባሰብ እና የበኩልህን ማበርከት መብት ብቻም ሳይሆን የትውልድ ግዴታህም ነው። አንተ የተውከውን ባህልህን፣ ቋንቋህን እና እምነትህን ትውልድ አይረከበውም። የሁሉም ብሔረሰብ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪካዊ ትውፊቶች ናቸው አንድ ላይ ሆነው ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ የሚያሰኟት። ባለንበት ሥልጡን ዘመን ባህልን፣ ቋንቋን እና ሌሎች የማንነት መገለጫ ትውፊት የሆኑትን ሃብቶችህን ለማስጠበቅ የደም ግብር አያስፈልግም። አለም የደረሰበት ሥልጣኔ ማንንም ሳትገድል፤ እራስህንም በከንቱ ደመ ከልብ ሳታደርግ ከነ ባህልህ እና ቋንቋህ የምትበለጽግበት እና እንደ እንቁ የምትደምቅበት ዘመን ላይ ነህ ያለኽው።
ከትምህርትም ዘመናዊ ትምህርት ቀስመኽ፣ ሳይንሳዊ ምርምር በሚካሄድባቸው የእውቀት መፍለቂያ ተቋማት ውስጥ አልፈህ፣ እንደ ዘመኑ ሰው ሌላው አለም የተጫማውን ተጫምተህ፣ የለበሰውን ለብሰህ፣ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚም ሆነህ እንደ ባቢሎን ዘመን ሰው ማሰብህ ምነዋ? የምትጣላበት ብታጣ በመቶ አመታት ወደ ኋላ እያየህ እንዲህ ነበርኩ፣ እንዲያ ነበርክ እየተባባልክ ዛሬህን የምታጨልም ጉድ ፍጥረት መሆንስ ምነዋ? አንተ በጎነጎንከው የዘር ፖለቲካ በልቶ ያልጠገበው ወገንህ በየጥሻው እየታረደ ሲጣል እና ከቅዮው እየተፈናቀለ በየዱሩ ሲንከራተት እያየህ ከመጸጸት ይልቅ ሞቱን እየደገስክ በግፍ ክምር የምትቆታች ግፈኛ መሆንህስ ምነዋ? በዘመናዊ እውቀት ታግዘህ ከድህነት አረንቋ ታላቅቀኛለህ ቦሎ በተስፋ ሲጠብቅህ ለኖረው ድሃ የአገርህ ልጅ ውለታውን እምትከፍለው እረብ በሌለው የፖለቲካ ንትርክ ሰክረህ በሞቱ በመዘባበት ነው ውይ?
ልንገርህ ወዳጄ ፡ –
– አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ ምንም ብትማር ምሁር ልትሆን አትችልም፤ በሳይንሳዊ ትምህርት ያፈራኽው እውቀት በዘር ሰንሰለት ታጥሮ የጋን ውስጥ መብራት ትሆናለህ እንጂ፤
– አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ ጥሩና ቅን ፖለቲከኛ ልትሆን አትችልም፤ ድካምህ ሁሉ በሃሰት ትርክት እና በሸር በሕዝቦች መካከል መበላለጥ እና ልዩነትን ማስፋት ነው እና የማንነት ፖለቲካ ነጋዴ እንጅ፤
– አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ ጥሩ ጋዜጠኛ ልትሆን አትችልም፤ በሰላ አንደበትህ እና ብዕርህ ሌሎችን ስታጠለሽ፣ ስትነቁር እና በማህበረሰቦች መካከል ያለውን ቅራኔዎችን ስታራግብ የምትውል ቃለኛ እንጅ፤
+ አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ልትሆን አትችልም፤ የእኔ የምትለው እና ሌላ ብለህ የፈረጅከው ወይም እንደ ሰው የማትቆጥረውን የህብረተ ክፍል ስታበላልጥ፤ የአንዱ ቁስል የሚያምህ የሌላውን ስቃይ መሳለቂያ የምታደርግ ወይም እንዳላየ የምታልፍ የብሔር መብት አቀንቃኝ እንጅ፤
– አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ መንፈሳዊ ወይም የሃይማኖት አባት ወይም ሰባኪ ልትሆን አትችልም፤ እግዚያብሔር በአምሳሉ የፈጠረውን የሰውን ልጅ በአንተ የብሔር መለኪያ እየሰፈርክ ያንተ ያልሆነውን ከሰው ተራ የምታወጣ ብሔረተኛ መሲህጂ እንጅ፤
+ አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ ጥሩ ጠበቃ፣ ጥሩ ሃኪም፣ ጥሩ ዳኛ፣ ጥሩ ፖሊስ፣ ጥሩ ወታደር፣ ጥሩ የሕዝብ አገልጋይ ልትሆን አትችልም፤ ሥራህ ሁሉ በመድሎ፣ በማግለል እና በቅናት መንፈስ የተደነቃቀፈ ፍትህ እና ርትዕ የምታጓድል፣ በማህበረሰቡ ውስጥ መድልዖን የምታሰርጽ ሰንካላ ሙያተኛ እንጅ፤
+ አክራሪ ብሔረተኛ ሆነህ ጥሩ የአገር እና የሕዝብ መሪ መሆን ይቅርና እወክለዋለው የምትለው ብሔር መሪም ልትሆን አትችልም፤ መሪነት ሰፊነትን፣ ብልሃትን እና አቃፊነትን የሚጠይቀ ትልቅ ኃላፊነት ነው እና፤
ብሔረተኝነት በራሱ አግላይ ነው። ስታከረው እና የፖለቲካ ፍላጎትህ ማሳለጫ መንገድ ስታደርገው ከአግላይነቱም አልፎ ሌላውን ሰው በቃላት እና በድርጊት ለማጥቃት በር ይከፍታል። አግላይ የሆነው ብሔረተኝነት በብዙ አገራት በተለይም በምዕራቡ አለም ጨምሮ አለ። መገለጫው የቆዳ ቀለም፣ የዘር ግንድ፣ የቋንቋ ወይም ኃይማኖት ላይ ያነጣጠረ ሊሆን ይችላል። ብሔረተኝነት ከአግላይነት ወደ ጥቃት የሚሸጋገረው ግን በተወሰኑ ስፍራፎች ብቻ ነው። ይኽውም የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ወይም በሥልጣን ላይ ያለው አካል ጭምር እራሱ የብሔር መድሎዎን ደጋፊ እና አራማጅ በሆነበት ወይም ሥርዓት አልበኝነት ነግሶ አክራሪ ቡድኖች ከመንግስት በላይ አቅም ባገኙበት ስፍራ ብቻ ነው።
አውሮፓ ውስጥ ስር የሰደደ ዘረኝነት አለ። ዘረኝነቱ በማግለል እና በመድሎ ደረጃ በየቦታው ይታያል። ይሁን እና ዘረኝነትን የሚጠየፍ፣ እንደ ወንጀል የሚቆጥር እና የማያበረታታ ማህበረሰብ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓት እና መንግስት ስላለ ዘረኞቹ ሊደራጁ ይችላሉ ነገር ግን የማንንም መብት ሊጥሱ እና ማንም ላይ በቃላትም ሆነ በድርጊት ጥቃት ሊሰነዝሩ አይችሉም። ይህን ያደረገ ሰው በሕግ ይጠየቃል። ስለዚህ የናዚ ደጋፊዎች ባሉበት እና አክራሪ ዘረኞች ባሉበት መንደር ሳይቀር ከአፍሪቃም ሆነ ከሌላው አለም የመጣ ሰው ደረቱን ነፍቶ ይኖራል። በሰላም ውሎ በሰላም ያድራል። ዘረኛውም መጤዎቹን ወይም የማይፈልጋቸውን ሰዎች እያየ እና ውስጥ ውስጡን እየተቃጠለ ከማጉረምረም ባለፈ ምንም ማድረግ አይችልም። ይህ ማላት ግን አልፎ አልፎ ችግር አይኖርም ማለት አይደለም። ነገር ግን ከሕግ ማዕቀፍ አይወጣም።
በአገራችን እየከረረ የመጣው ብሔረተኝነት መስመሩን ከሳተ ውሎ አድሯል። ከህግ ቁጥጥርም ውጭ ወጥቷል። ለዚህም ሁለት ነገሮች አስተዋጽኦ አድርገዋል። አንደኛው መንግስት ሕግ በማስከበሩ እና የሕግ የበላይነትን በማስፈኑ እረገድ ያሳየው ዳተኝነት ነው። ሁለተኛው እና አሳሳቢው ጉዳይ ደግሞ አክራሪ ብሔረተኞችን የሚጠየፍ እና በአደባባይ የሚያወግዝ ማህበረሰብ ገና አለመፈጠሩ እና በተቃራኒው አክራሪ ብሔረተኞች ባዘጋጁለት የብሔር ወጥመድ ውስጥ የሚገባው ሰው ቁጥር እለት ከዕለት እየጨመረ መምጣቱ ነው። አክራሪ ብሔረተኞች ብቻቸውን መቆም ስለማይችሉ የመጀመሪያው ስልታቸው ሁሉንም ብሔረተኛ ማድረግ ነው። ሁሉም በየብሔሩ ከተሸጎጠ አገራዊ አስተሳሰብ ይከስማል። ያኔ አገርን ለማፍረስም ሆነ ብሔረተኞች በቀደዱት ቦይ ለመንጎድ መንገዱ ቀና ነው።
አሁን ካለንበት አደጋ ልንወጣ እና አገሪቱም የአክራሪ ብሔረተኞች መፈንጫ እንዳትሆን ማድረግ የሚቻለው፤
+ መንግስት በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ግጭቶችን እና ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ሲኖረው፤
+ ሕብረተሰቡ አክራሪ ብሔረተኞች ያጠመዱለት ወጥመድ ውስጥ ገብቶ አገሩ እንዳያጣ ተገቢውን ጥንቃቄ ሲያደርግ፤
+ ጥቃት በማንም ኢትዮጵያዊ ላይ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሲደርስ በእኩል ድምጽ እና በወገንተኝነት ስሜት ማውገዝ ስንችል፤
+ የአጥፊዎችን እና የተጎጂዎችን የብሔር ማንነት መሰረት ያደረጉ ድጋፍም ሆነ ነቀፌታዎች ከሰውነት ደረጃ ሰለሚያወርዱን መጥፎን ድርጊት ማንም ይፈጽመው ማን በመጥፎነቱ ማውገዝ እና ማንኛውም ሰው ላይ ጥቃት ሲደርስ ማውገዝ እና ከግፏን ጎን መቆም ስንችል፤
+ በብሔር የተደራጃችው እና የብሔር ፖለቲካን የምታራምዱ ወገኖችም ኢትዮጵያ ለአንዱ ብሔር ገነት ለሌላው ብሔር ሲኦል ልትሆን እንደማትችል ተረድታችው ብሔር ተኮር ጥቃትን ለማስቆም መታገል ስትጀምሩ፤
ያኔ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትሆናለች። በግፉአን ደም መቆታቸቱ ይብቃ!
ቸር እንሰንብት!