በቀላል ትርጓሜው ግብዝነት/ሸፍጠኝነት (hypocrisy) በቅንና እውነተኛ ባህሪያትና ተግባራት የእኛ ያላደረግናቸውን ድንቅ እሴቶች የእኛነት ዋነኛ መገለጫዎች እንደሆኑ አስመስሎ (presence) በማቅረብ እራሳቸንን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም (ህዝብንም) የምናታልልበት ወይም የምናሳስትበት ክፉ ልማድ/ልክፍት ነው ። ግብዝነት አንድ ሰው ወይም ቡድን በመሆንና በማድረግ ሳይሆን በመምሰልና በማስመሰል ገዝፎ የመታየት ክፉ አባዜ መለከፉን የሚገልፅ ሃይለ ቃል ነው ።
ግብዝነትን ለሥጋም ሆነ ለነፍስ መድህን የሆኑ መልእክቶችን (ትምህርቶችን) አጠቃሎ በያዘው በታላቁ መጽሃፍ (መጽሃፍ ቅዱስ) ውስጥም ግዙፍና ጥልቅ ሃይለ ቃል ሆኖ የምናገኝበት ምክንያትም የኸው ነው ።
ችግሩ እናነበንበዋለን ወይም ሲያነበንቡልን ከንፈር እየመጠጥን እንሰመዋለን እንጅ ወደ ውስጠ ህሊናችን ዘልቆና ተዋህዶ የሥጋም ሆነ የነፍስ መዳኛ ሊሆነን በሚያስችል አኳኋን አልተጠቀምንበትም ወይም አንጠቀምበትም ። በዚህም ምክንያት አሁንም ከዚህ ዘመናትን ካስቆጠረው ክፉ አስተሳሰብና አካሄድ ትርጉም ባለው ሁኔታ ፎቀቅ አላልንም ። እውነተኛውንና ዘላቂነት ያለውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ እሴት ግብዝና ጊዜያዊ ከሆነው ለመለየትና የሚበጀውን አድርጎ ለመገኘት ባለመቻላችን (ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ባለመሆናችን) ይኸውና ዛሬም እየተነሱ ተመልሶ ከመውደቅ የታሪክ ድግግሞሽ ሥጋት ውስጥ እንገኛለን ።
የግብዝነት ፖለቲካ በተለይ ለእንደኛ አይነት እኩይና ደንቆሮ ገዥዎች ለዘመናት እያደነቆሩና መከራና ውርደቱን እያለማመዱ ሲገዙት ከቆዩ በኋላ በዚያው መቀጠል እንደማያዋጣቸው ተገንዝበው ስሜቱን የሚኮረኩር ዲስኩር ሲያሰሙትና ለዚህም ይጠቅሙናል ያሚሏቸውን አዎንታዊ እርምጃዎች እዚያም እዚህም ሲያሳዩት መከራው ያለቀለትና ውርደቱ የተራገፈለት ለሚመስለው የዋህ ህዝብ በእጅጉ አሳሳች ወይም አደንዛዥ ነው ።
ለዚህም ነው የዋሁ የአገሬ ህዝብ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የትየለሌ መስዋእትነት የከፈለበትን ቁልፍ ጉዳይ ማለትም ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ሥርዓተ ኢህአዴግ አብቅቶለት እራሱንም የሚጨምር አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመመሥረት ጥያቄ እየተንሸራተተ የግብዝ ፖለቲከኛች የፖለቲካ እስትንፋስ በተለዋወጠ ቁጥር በተስፋ ጭላንጭልና በሥጋት ማእበል ውስጥ ከመዋዠቅ አባዜ ለመውጣት በእጅጉ የተቸገረው ።
“ጥያቄው የኢህአዴግን የተሃድሶ ፍርፋሪ መልቀም ሳይሆን አዲስና እውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ነውና ቀልዳችሁን አቁማችሁ የእውነት ፖለቲካ እንጫወት”ለማለት የሚሽኮረመም ተቀዋሚ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅት ባለበት ፣ ከዚህ ክፉ የፖለቲካና የማህበራዊ አዙሪት ለመውጣትና ነገን ለራሱ የሚመች ለማድረግ የተዘጋጀና የተደራጀ የወጣት ሃይል ባልተፈጠረበት ፣ የምርና ትውልድ አድን የሆነ ምክር የሚለግሥና የተግባር አርአያነት ያለው የሽምግልና ባህል ለማግኘት ብርቅዬ በሆነበት ፣ አብዛኛው ተማርኩና ተመራመርኩ ባይ የኢህአዴግን የእለት ተእለት መዋእለ ዜና እና “የተሃድሶ ስልጠት” ትርክት ከማመንዠክ አባዜ በመውጣት ነቅቶ የማንቃትንና ተደራጅቶ የማደራጀትን ሥራ እንደ ኮረንቲ በርቀት ነው በሚልበት ፣ አብዛኛው የአገሬ ሴቶች የሴቶችን ተሿሚነት ከጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ የሚያልፍና ለሴቶች እውነተኛ እኩልነት ወደ የሚረጋገጥበት መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ የሚያሸጋግር ከመሆኑ አንፃር ሳይሆን “ዓለም አቀፍ አድናቆትን (ዝናን)” ካስገኘው የሃምሳ ፐርሰንት ስታትስቲክስ ስሌት አንፃር ብቻ በማየት “እኩልነታችን ተረጋገጠ” የሚል ፕሮፓጋንዳ ሰለባ በሆኑበት የፖለቲካ አውድ (political arena ) ውስጥ የግብዝነት ፖለቲካ ልክፍትን ማሸነፍ ቀርቶ አደብ ማስገዛትም አይቻልም ።
የግብዝነት አስተሳሰብና ባህሪ ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወትትልቅና ክፉ ጣላት (ጠንቅ) ነው። ግብዝነት/ሸፍጠኝነት አንድ ሰው ወይም ቡድን ስለ እውነት/ስለ ሃቀኝነት፣ ስለ መታመን ፣ ስለ ቅንነት፣ ስለ ነፃነት ፣ ስለ ፍትህ/ስለ የህግ የበላይነት ፣ ስለ እኩልነት ፣ ስለአብሮነት ፣ ስለ ፍቅርና ሰላም ወዘተ አጥብቆ ከሚሰብክበት መድረክ ላይ ሲወርድና ከአደባባይ በስተጀርባ ሲሆን ተቃራኒውን እየሆነና እያደረገ የአገርን (የህዝብን) የእውነተኛ ለውጥ ፍለጋ አቀጣጫና ግሥጋሴ ግራ የሚያጋባ ክፉ የፖለቲካ ባህሪ ነው ። መሪሩን እውነት በመጋፈጥ የተበላሸውን ለማስተካከል የሚጠይቀው የአርበኝነት (አርበኝነት የጦር ሜዳ ድል አድራጊነት ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይባልልኝና) ወኔው እየከዳን ነው እንጅ አሁን ያለንበት የፖለቲካ አውድ (political arena) በግልፅ የሚነግረንና የሚያሳየን ይህንኑ የፖለቲካ ጤና ማጣት ( ill-guided politics ) ነው ።
ይህን ክፉ ባህሪ ከሰብአዊ ፍጡር ጨርሶ ማስወገድ አይቻልም ። የተለየ ተአምር ይፈጠራል ካላልን በስተቀር ሰው እስከሆን ድረስ ከዚህ እንፀየፈዋለን ከምንለው ባህሪያችን ነፃ የመውጣት ጉዳይ አንፃራዊ እንጅ ፍፁማዊ ሊሆን አይችልም ።
የግብዝነት/የሸፍጥ ፖለቲካዊ አስተሳሰብንና ባህሪን እጅግ የከፋና አሳሳቢ የሚያደርገው ከግል ወይም ከተወሰነ የግለሰቦች ስብስብ አልፎ አካባቢን/ማህበረሰብን/አገርን እያሳሳተ ወደ የሚፈለገው እውነተኛ የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት ፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና ሥርዓት የሚደረገውን የትግል ጉዞ ፈሩን (አቅጣጫውን) በማሳት የህዝብን መከራና ውርደት ሲያራዝም ነው ።
ሰሞኑን ኢህአዴግ የሰላም ብሎ የሰየመውና ከግብዝነት የፖለቲካ ጨዋታ (hypocritical political game) ያላለፈ ሚና ያለው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በየክልል የኢህአዴግ አባል ገዥ ፓርቲዎች ተባባሪነት ሚሊዮኖች ከገንዛ አገራቸውና ቀያቸው ለተፈናቀሉበት ፣ ለምድራዊ ሲኦል ለተዳረጉበት እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ዜጎች ህይወት ለተቀጠፈበት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በተጠያቄነት ከጠረጠራቸው ሁለት ሽ በላይ ከሆኑት መካከል አንድ ሽ ሦስት መቶ ያህሉን በህግ ቁጥጥር ሥር ማዋሉንና ሰላምና መረጋጋቱ “እየተሳለጠ” የመሆኑን ዜና አብስሮናል ። ይህንን ዜና እንዲሆን ከምንፈልገው አጠቃላይ እውነታ አንፃር በአበረታችነቱ መቀበል ጨርሶ አያስቸግርም ። ዜናውን እየነገረን ያለው ሥርዓተ ፖለቲካ የትኛው ነው? የሚዘወረውስ በነማን ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ግን ትክክል ወይም ተገቢ ነው ። መሬት ላይ ያለው መሪር ሃቅ እና የፖለቲከኞች የምሥራች ነጋሪነት አልገናኝ የማለቱ ጉዳይ በእጅጉ የሚያሳስበው (የሚያስጨንቀው) ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጋ ይህን ጥያቄ ሳያነሳ (ሳይጠይቅ) ዜናውን በአሜን ባይነት ይቀበለዋል የሚል እምነት የለኝም ።
በፖለቲካ ወለድ ወንጀል እንደተጨማለቀ በተሃድሶ (reform) ስም እራሱን የለውጥ ሃዋርያ አድርጎ በቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ ሥር የሰላም ሚኒስቴር ብሎ በመሰየምና የእርሱን (የእራሱን) ታማኝ አገልጋይ ካድሬዎችን (ባለሥልጣኖችን) በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ስሌት ሾሞ (መድቦ) እውነተኛና ዘላቂ ሰላም አሰፍናለሁ ማለት ከክፉ የፖለቲካ ግብዝነት / ሸፍጥኝነት አያልፍም ። ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ የመከራና የውርደት ቀንበር አሸካሚ ሆኖ የዘለቀው ሥርዓተ ኢህአዴግ የፖለቲካ አውዱን ተቆጣጥሮ በቀጠለበት ሁኔታ የራሱን ትንንሽ ፖለቲከኞች (የበታች አገልጋይ ካድሬዎች) በወንጀል ተጠርጣሪነት በቁጥጥር ሥር አዋልኩ እያለ ፕሮፓጋንዳ አዘል ዜና የማስነገሩ ጉዳይ ከግብዝነት የፖለቲካ ጨዋታነት በስተቀር በሌላ ሊገለፅ አይችልም ።
ኦህዴድ/ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግ እየነገረን ያለው እራሱ ፈጥሮና ተንከባክቦ አሳድጎ ወደ መስክ ካሰማራው እና በህዝብ ህይወት ላይ የተጣበቀ አደገኛ ተባይ (deadly parasite) ሆኖ ዘመናትን ካስቆጠረው የሚሊዮኖች የካድሬ ሠራዊት መካከል የህዝብን ቁጣና ምሬት ለማርገብ ይረዳው ዘንድ አንድ ሽ ወይም ሁለት ሽ በቁጥጥር ሥር አውሎ “እርቀ ሰላሙና መረጋጋቱ በከፍተኛ ፍጥነትና መጠን እየገሠገሠ ነውና ደስ ይበላችሁ” የሚለውን የግብዝነት ፖለቲካ ጨዋታ ነው ። የትኛው ካድሬ (ባለሥልጣን)? መቼና የት ? ለምንና እንዴት ? የሚለውን መረጃ ከህዝብ የመደበቁ (እስካአሁን ያለው ልምድ ይኸው ነውና) ስልት እራሱን የቻለ ችግር ያለበት ነው ። በዚህ ደምሳሳ ሁኔታ ውስጥ የመጨረሻውን ብቻ በትእግሥት እንዲጠብቅ የተፈረደበት የአገሬ ሰው ከኢህአዴግ የቆየ ባህሪና አሁንም ከሚታየው የግብዝነት ፖለቲካ አካሄድ ተነስቶ የራሱን ከእውነት የማይርቅ ግምት ለመስጠት ቢገደድ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ትክክል አይደለህም ለማለት የሞራልም ሆነ የፖለቲካ ብቃት ጨርሶ ሊኖራቸው አይችልም ።
በመራቢያነቱ አደገኛ የሆነውን አካባቢ (environment) መሠረታዊና ዘላቂ በሆነ አቀራረብና ዘዴ ሳያፀዱና ሳያስወግዱ የወባ ትንኝንና የሚያስከትለውን የጤና መታወክና የህይወት ጥፋት ለማስወገድ ከቶ አይቻልም። የኢህአዴግ ፖለቲከኞች እየሄዱበት ያለው መንገድም ይኸው ነው ። በፅእኑ የተመረዘውንና ለማደስ የማይመቸውን ሥርዓተ ፖለቲካ ቅሬተ መርዙን እንዳይተው በሚያደርግ አኳኋን ሳያስወግዱ በውስጡ ካሉት ሚሊዮን ካድሬዎች አንፃር ሲታይ ቁጥራቸው እዚህ ግባ የማይባለውን ካድሬዎችና ባለሥልጣኖች ለህዝብን እሮሮና ቁጣ ማብረጃነት በቁጥጥር ሥር አዋልኳቸው ማለት ከጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ የሚያልፍ አይሆንም ። የኢትዮጵያ ህዝብ የትየለሌ መስዋዕትነት የከፈለበት መሠረታዊ ጥያቄ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን እንጅ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውን ሥርዓተ ኢህአዴግ ጠግኖ ለማስቀጠል አልነበረም ። አሁንም አይደለም ።
ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭ ሆኖ የዘለቀውና አሁንም ትርጉም ባለው (መሠረታዊ በሆነ) አስተሳሰብና አካሄድ ያልተለወጠው ሥርዓተ ኢህአዴግ በቀጠለበት ሁኔታ የህዝብ ቁጣና እሮሮን “ለማስታገስ” ሲባል የእለት ዳቦውን የሚያገኝበት ሥርዓት የፈረሰ በመሰለውና በቃዠ ቁጥር በህዝብ ላይ ወንጀል የሚፈፅመውን የበታች ካድሬ ወይም የአካባቢ ባለሥልጣን እዚያም እዚህም ተቆጣጠርኩ ማለትና የሌለ ሰላምና መረጋጋት ማወጅ እጅግ የከፋና የከረፋ የፖለቲካ ግብዝነት ነው ።
እያልኩ ያለሁት የንፁሃንን ህይወት ያስቀጠፉና ምስቅልቅሉን ያወጡ የኢህአዴግ ካድሬዎች በህግ አግባብ ተገቢው እርምጃ አይወሰድባቸው አይደለም ። ጤናማ አእምሮ ያለውና የወገን መከራና ውርደት ከምር የሚያሳስበው ዜጋ እንዲህ አይነት እጅግ ደምሳሳና የዘቀጠ ሃሳብ ይሰነዝራል የሚል እንኳን እምነት ጥርጣሬ የለኝም።
እያልኩ ያለሁት እኩይ የፖለቲካ አጀንዳውን በህገ መንግሥት ደረጃ ቀርፆና ተግባር ላይ አውሎ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ የዘለቀው የህወሃት/ኢህአዴግ ታሪክ የሚነግረን እንደ ግንባርና እንደ ሥርዓት ለመቀጠል ሥጋት ውስጥ በገባ ቁጠር ትልልቁ አሳ ትንንሹን አሳ እንደሚውጠው ሁሉ የእራሱን ካድሬዎች እየዋጠ (እርካሽ መስዋዕትነት እያስከፈለ) እዚህ የደረሰ መሆኑን ልብ ያሻል ነው ። አዎ ! እያልኩ ያለሁት ይህ ክፉ ታሪክ ዛሬም እራሱን እየደገመ መሆኑን በመሬት ላይ ካለው እውነት ጋር እያነፃፀርን ካላየነው የግብዝነት (የሸፍጥ) ፖለቲካ ሰለባዎች እንሆናለን ነው ።
የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ሁሉ ይፈለጡና ይቆረጡ የሚል ደምሳሳና ደንቆሮ አመለካከት የለኝም። እያልኩ ያለሁት ከፖለቲካ ወለድ ወንጀል ነፃ ያልሆኑ “ትልልቅ” ፖለቲከኞችን እየሸለመና እየሾመ አቅፎና ደግፎ የያዘው ሥርዓተ ኢህአዴግበቀጠለበት የፖለቲካ አውድ (political arena) ውስጥ የበታች ፈፃሚና አስፈፃሚ ካድሬዎቹን እዚያም እዚህም በቁጥጥር ሥር በማዋል “በህግ የበላይነት እንደማልደራደር እወቁልኝ” የሚለው እወጃ ጨርሶ ወንዝ አያሻግርም ነው።ከወንዙ ማዶ ወደ አለውና ወደ የምንፈልገው ሥርዓተ ፖለቲካ በእንዲህ አይነት የኢህአዴግ የግብዝነት (የሸፍጥ) ፖለቲካ መሻገር ከቶ አይቻለንም ነው ።
በወቅቱ የትሮይ ፈረሶች (ብአዴን፣ኦህዴድና ደህዴን) አዛዥ (ጌታ) የነበሩት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት “ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው ” ብለው ነበር ። በሰውየው እጅግ እኩይ የፖለቲካ ሰብእና ምክንያት በወቅቱ አባባላቸውን ብዙም ከምር ያንሰላሰለው ሰው የነበረ አይመስለኝም ።ይኸውና አሁን እውነት ሆኖ ኦህዴድ/ኦዴፓ የትሮይ ፈረሶቹን እንዳሻው እየጋለበ የመከራና የውርደት ዶፍን ሲያከፋፍል የኖረውን ህወሃትን ተክቶ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ትርጉም ባለው አኳኋን ባልተለወጠበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ በተራው ሁለቱን (ብአዴንና ደህዴንን) በትሮይ ፈረስነት ለመጠቀም የሚያስችሉ ቁልፍ (ስትራቴጅክ) የፌደራል ተብየ ቦታዎችን በእጁ አስገብቷል ።
ኦህዴድ/ኦዴፓ መራሹ ኢህአዴግም የህዝብ የሰቆቃ እሮሮ በግብዝነት (በሸፍጥ) ፖለቲካ የተለወሰ ተሃድሶውን ሥጋት ላይ የሚጥል ሆኖ በተሰማው ቁጥር ኮትኩቶና አሰልጥኖ ያሰማራቸውን የበታች ወይም የመስክ ፈረሶቹን ለመስወዕትነት እያቀረበ “ሰላምንና መረጋጋትን እያሳለጥኩት ነውና አታስቡ” ይለናል ።ታዲያ ይህ አይነቱ ትእይንተ ፖለቲካ በመከረኛው የአገሬ ህዝብ ላይ እንደ መሳለቅ ካልሆነ በስተቀር በሌላ እንዴት ሊገለፅ ይችላል ?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦህዴድ/ኦዴፓና የኢህዴግ ሊቀ መንበር እና የኦህዴድ /ኢህአዴግ መራሹ የሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል (executive branch of government) የበላይ አለቃ ናቸው ። እናም እየተካሄደ ያለው የግብዝነት (የሸፍጥ) ፖለቲካ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በእጅጉ ስለሚመለከታቸው እንኳን ከደሙ ንፁህ ነኝ ለማለት ድክመቴ ተጋኖብኛል ብሎ ለማሳመን የሚችሉ አይመስለኝም ።
በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ለማነኛውም ጤናማ አእምሮ ላለውና የአገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል ለሚል ዜጋ ሁሉ እጅግ ግልፅ የሆነውን መሪር ሃቅ ለፖለቲካ ፍጆታሲባል ለማሳነስ መሞከር ወይም ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ልፍስፍስ ሰበብ (clumsy execuse) መደርደር የገብዝነት ፖለቲካ መገለጫ እንጅ ወደ እውነተኛ መፍትሄ የሚወስድ የፖለቲካ ባህሪ አይደለም ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ኦህዴድ/ ኦዴፓ በሚገዛው ክልል ባለሥልጣናትና በጎሳ/በዘር ፖለቲካ ንግድ ልክፍተኞች አነሳሽነትና አስተባባሪነት ለበርካታ ወራት በተካሄደ ኢሰብአዊ ዘመቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ከቀያቸው የተፈናቀሉበትን ፣ ለምድራዊ ሲኦል የተጋለጡበትን እና በርካቶችም አካላቸው የጎደለበትንና ህይወታቸው የተቀጠፈበትን አሰቃቂ ሁኔታ በደምሳሳው ፀረ ለውጥ የሚሏቸው ሃይሎች ፣ ሚዲያው እና በበጎ አድራጎት ስም የሚነግዱ ድርጅቶች የሚያጋንኑት እንደሆነ አድርቀው ለማቅረብ የሄዱበት እርቀት የያዙትን ሥልጣንና ተግባር ጨርሶ አይመጥንም ። ከዚህ የባሰ የፖለቲካ ግብዝነትም የለም ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አፈ ቀላጤም ( የፕሬስ ሃላፊ) በደምሳሳው ከግጭት እናተርፋለን የሚሉ ሃይሎች የሚሏቸውንና የተሳሳተ መረጃ ያራግባል የሚሉትን ሚዲያ ተጠያቂ ባደረጉበትና በድል አድራጊነት ፕሮፓጋንዳ አገላለፅ ስሜት ከኢሳት ጋር ባደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ የነገሩን የዚህኑ የግብዝነት ፖለቲካ ግልባጭ ነው ።
እነዚህ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ይህን ሁሉ ሲነግሩን ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭና አከፋፋይ ሆኖ በዘለቀውና አሁንም እንደ ሥርዓተ በቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ ውስጥ ተዋናይ እንደነበሩና እንደሆኑ ሆነው ሳይሆን በዴሞክራሲ ተወልደውና አድገው የኢትዮጵያን ህዝብ ዴሞክራሲን ለማቀዳጀት ትግል እንደጀመሩ አይነት ሆነው ነው። ከዚህ የባሰ ክፉ የፖለቲካ ግብዝነት ልክፍት የለም። “ስለተአምራዊው” የለውጥ አራማጅነታቸው አብዝተው ከሚተርኩበትና ከሚጫወቱበት አውደ ፖለቲካ ወጥተው የገሃዱን ዓለም መሪር እውነት ግልፅነትን በተላበሰ ወኔ በመጋፈጥና ለራሳቸው ሳይሆን ለአገር (ለህዝብ) የሚበጀውን ሁሉ በአርበኝነት ወኔ ለመቀበል የሚያስችል የፖለቲካ ባህሪም ሆነ የተሞክሮው ማጣፊያ በእጅጉ ያጥራቸዋል ። ለዚህም ነው ከግብዝነት የፖለቲካ ጨዋታ ባሻገር አልፈው ለመሄድ ያልፈለጉት (ያልሆነላቸው) ።
የዋሁ የአገሬ ሰው አሁን የሚያያትን የለውጥ ጭላንጭል የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ የኢህአዴግ ሥርዓተ ፖለቲካ አሸክሞት ከኖረው የመከራና የውርደት ቀንበር ጋር እያነፃፀረና የይሆናል ተስፋ እየሰነቀ በየሄዱበት አካባቢና በየስብሰባ አዳራሹ ስሜትን ኮርኳሪ ዲስኩር ሲደሰኩሩለት በሚለግሳቸው ሞቅ ያለ ጭብጨባ ሞቅ እያላቸው የተቸገሩም ይመስለኛል። የዚህ አይነት በጭብጨባ የመጋል (ከልክ በላይ የመሞቅ) ስሜት በራስ ከመተማመን ቀውስ (self confidence crisis) ሊመጣ እንደሚችልም መረዳት ጥሩ ነው። ለምን የለውጥ አራማጆች በራሳቸው አይተማመኑም? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ ። በአንድ በኩል በፅዕኑ የተለከፉበትን የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍት ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል ፖለቲካዊና ማህበራዊ መሠረት የመጣል የአርበኝነት ወኔ ጨርሶ የማጣታቸው ጉዳይ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዜግነት (የኢትዮጵያዊነት) ፖለቲካ የሚያራምደውን የህበረተሰብ ክፍልና የፖለቲካ ጎራ ወደ እነሱው የጥበትና የወራዳነት (የዘር አጥንት ቆጠራ) ፖለቲካ ለመሳብ ያለመቻላቸው ፈተና የመረበሽና በራስ ያለመተማመን ቀውስ ( serious frustration and self-confidence crisis) ውስጥ እንደዘፈቃቸው ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የጀመሩት የጥገና ለውጥቢደናቀፍና ከሁሉም ሳይሆኑ ቢቀሩ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የተዘፈቁበትን የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተሸክሞ ማን ምን ያመጣብኝ ይሆን እያሉ እረፍት አጥቶ መኖር እራሱን የቻለ ከባድ ፈተና ነው ።
ለዚህ ነው ከግብዝነት (ከሸፍጥ) ፖለቲካ ጨዋታ ወጥቶ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲከኛውን እና በአንድነት ስም ሁሉንም ልጨፍልቅ የሚለውን ፖለቲከኛ አደብ አስገዝቶ የጎሳ/የብሄረሰብ እራስን የማስተዳደር፣ ባህልን የመንከባከብና የመጠበቅ እና ቋንቋን የመጠቀም መብት የሚከበርበት የዜግነት ፖለቲካ ሥርዓትን በተቀበለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖኖር በሚያስችል የፖለቲካ ሥራ ላይ መረባረብ የግድ አሁን መጀመር ያለበት ። ይህ ግን ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በበላይነት በሚመራው አካሄድ ሳይሆን የአገራችን ጉዳይና የፖለቲካ ህመማችን ከምር ያሳስበናል የሚሉ ድርጅቶችና ዜጎች ከሂደቱ እስከ ውጤቱ ሙሉና ንቁ ተሳትፎ በሚያደርጉበት አግባብ መካሄድ ይኖርበታል ። የኢህአዴግ ፖለቲከኞችም የግብዝነት (የሸፍጥ)ፖለቲካ ጨዋታቸውን አቁመው ለዚሁ የወደቀ የጋራ ቤትን በጋራ የማንሳት ርብርብ እራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይኖርባቸዋል ። በመደናቆርና በመናቆር ለውድቀት የዳረጉትን የጋራ ቤት በጋራ ከማንሳትና ከመገንባት የበለጠ አርበኝነት የለም ።