የትምህርትን ህይወት ‹ሀ› ብዬ ስጀምር ያበረታታኸኝ፤ 1ኛ ስወጣ ያጨበጨብክልኝ፤ የወደፊት ምኞቴ ሀኪም መሆን ነው ስል ይቅናሽ ብለህ የመረቅከኝ ለዚህ እንድበቃ ከጎኔ ያልተለየኸኝ ወገኔ ወዴት አለህ?
እውነት ሀኪም ሆና ጨከናብሃለች፤ አንተ ልትሞት ስታጣጥር እሷ ብር ፍለጋ እየሮጠች ነው፤ ስላንተ አትጨነቅም ያሉህን አመንካቸው?
እንዴት ይቻለኛል? እንደው እነሱ እንዳሉት ያጎረስከኝን ረስቼ፤ አርሰህ ያበላኸኝን ወጪት ሰብሬ ምን ላገኝ? ምንስ ቢሆን እኔ አኮ ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡
ደምህን የምጋራ፤ ካጥንትህ የምካፈል፤ ቋንቋህን የምናገር ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡ ክፉና ግድየለሽ አድርገው ላንተ እንደነገሩህ ልሁን ብልስ ከየት አምጥቼው፡፡ አንተ ያስተማርከኝ ከወገን አልፎ ለጎረቤት መሞት እንጂ መች ወገኔን መግደል ሆነና? እውነት ይህን ጭካኔ ከየት ታመጣዋለች ብለህ አመንካቸው?
ዛሬ በነጩ ጋውን ስታይ ሌላ ፍጡር ተደርጌ የተሳለኩት ፤ እንደ ጠላት የተቆጠርኩት፤ የትላንቷ ሚሚ የዛሬዋ ዶክተር፤ የኢዛና፤ የአጼ ቴዎድሮስ፤ የአብዲሳ አጋ ደም ያለብኝ፤ የነ ካዎ ጦና ጥበብን የተማርኩ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራዬን ያነገትኩ ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡
እውነት ስራዋን አቁማ ብር ጨምሩ አለች፤ ስራው ግን አልተበደለም ሲሉ ‹ምን አይነት ራስ ወዳድ ናት አስባሉህ?› እውነት እኔ ያንተን ደህንነት ሳላመቻች፤ ድንገተኛ ክፋልን ሳላሸፍን፤ ምጥ ላይ ያለች እናት፤ ባለተስፋ ህጻን ትቼ ምክድህ ይመስልሃል? እንዴት አድርጌ? እኔ እኮ ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡
ወገኔ የጤናው ዘርፍ ይሻሻልለት፤ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ይይጥ ፤ የሚለውን ጥያቄ ደብቀው ‹‹ብር ብቻ›› ትላለች ብለው ካነተ ያጣሉኝን ታሪከ አይምራቸውም፡፡
ሰራ ማቆም መፍትሄ ነው ብላለች ሲሉህ አትመናቸው፡፡ አንዳንዴ እነሱ በሚሰሙት ቋንቋ ለመናገር እንጂ አንተን መቼም አሳልፌ አልሰጥም፡፡ ይህ ደግሞ ቃሌ ነው፡፡ ‹‹ቃል የእምነት እዳ ነው›› ብለህ ያስተመርከኝን የማልረሳ ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡
እመነኝ አላማዬ የተሻለ የጤና አገግሎት እንድታገኝ፤ እኔ እያለሁልህ ህክምና ፍለጋ ከሀገር እንዳትወጣ፤ ሙያዬን በስንፍናውና በግድየለሽነቱ ሚያሰድበውን በስመ ሀኪም ያለውን አጋልጬ ላወጣ፤ የህክምና ትምህርቱ ጥራት እንዲኖረውና ብቁ ሀኪም ለሀገሬ ለሀገርህ እንዲፈጠር ነው፡፡
ወገኔ ሆይ ስማኝ በጣም ባስፈለከኝ ጊዜ አትራቀኝ መቼም ማልከዳህ ኩሩ ኢትዮጲያዊ ያንተው ዘር ነኝ፡፡