የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ በመወያየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

አዲስ አበባ – ኤፍ.ቢ.ሲ || የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ባለፈው አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተከናወኑ የብሔራዊ ደህነንት ስኬታማ ስራዎችን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች የገመገመ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

ኮሚቴው የሀገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎችን በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን ለአብነትም በውጭ ሀገራት የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበረው ሰላምም ጦርነትም ያልሆነ ግንኙነት መስተካከሉ ከለውጡ በኋላ የተገኙ ስኬቶች መሆናቸውን ግምግሟል፡፡

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች መካሄድ መጀመራቸው፤ የደህንነት ተቋም አመራሮች ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዱ እንዲሆኑ የሚያስችል የአመራር ለውጥ መደረጉን በጠንካራ ጎን የገመገመው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመከላከያ ሰራዊት ባለፈው አንድ ዓመት ጠንካራ ሪፎርም ካደረጉ ግንባር ቀደም ተቋማት አንዱ እንደሆነና ከአደረጃጀቱ ጀምሮ አጠቃላይ የመከላከያ መዋቅሩን ለማዘመን የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንም አይቷል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት በአጠቃላይ በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ስራዎች ቢከናወኑም በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆናቸው ኮሚቴው ገምግሟል፡፡

ተግዳሮቶቹ በዋናነት ከጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ወይም ደቦዎች፤ ከህገ-ወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር እንዲሁም ከማህበራዊ ሚድያ ሀሰተኛ ዜናዎች ተጽዕኖ ጋር የተያያዙ መሆናቸውንም ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህነንት ስጋት ምክንያት መሆናቸውንም አስምሮበታል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በዚህም ብሔራዊ ደህንነትን ማረጋገጥንና የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸን አፅንኦት በመስጠት የዜጎችን የሰላም ዋስትና የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ መረባረብ እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፏል።

ለደህንነት ተግዳሮቶች መነሻ ወይም ችግሩን በአጭር ጊዜ እንዳይቀረፍ ከማድረግ አንጻር ዋነኛው ችግር ያለው ከፖለቲካ ስራ ጋር የተተያያዘ እንደሆነ በመለየት የደህንነት ስራው ከፖለቲካ ስራው ጋር ጎን ለጎን ተያይዞ እንዲሰራና በአንዱ የጎደለው በሌላው እየተሞላ አስተማማኝ ሰላም በአጭር ጊዜ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ እንዲከናወን አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከአንዳንድ የአስተዳደር ወሰኖች ጋር በተያያዘ ሲስተዋሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ያሳዩ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሎች ከክልሎች እና ክልሎች ከፌደራል መንግስት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ሃይሎች ቅኝትና አወቃቀር በሚመለከት የሚስተዋሉ ችግሮች በህገ መንግስቱ መሰረት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ለማድረግ የሚያስችል ስራ እንዲሰራ ኮሚቴው ወስኗል።

የጸጥታ ኃይሎች ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ እንዲሁም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ለማስከበር በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የየአካባቢያቸውን ሰላም ለማስከበር እንዲሰሩ ያሳሰበው ኮሚቴው ሰላም ወዳዱ ህዝብ እንደወትሮው ሁሉ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በንቃት እንዲረባረብ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረጉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ሁለንተናዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግም አስምሮበታል፡፡

ኮሚቴው የደህንነት ስጋት ምንጮችን በዝርዝር በመለየት ተግዳሮቶቹን በአጭር ጊዜ በመፍታት የተሟላ ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራት ላይ ተወያይቶ የአፈጻጸም አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY