የሀኪሞች ነገር || ብርሃኑ ተክለያሬድ

የሀኪሞች ነገር || ብርሃኑ ተክለያሬድ

ሀኪሞች እየጠየቁ ካሉት ጥያቄና እያካሄዱ ካሉት አድማ ጋር ተያይዞ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ ገመድ ጉተታ እየታየ ነው። በወዲህ በኩል ሁሉን ማዳፈንና ማድበስበስን ስራዬ ያለው “ለውጠኛ” “ሀኪሙ ዝም ብሎ አንገቱን ደፍቶ ችግሩን መቻል አለበት ምንም ጥያቄዎች የሉትም ካሉትም የልብ አውቃ የሆኑ መሪዎች በሂደት ይመልሱለታል” አይነት አስተያየት ሲሰነዝር፣ በወዲያ በኩልም ሀኪሞቹ የጠየቁትን ጥያቄ “ምን ለውጥ አለና” ለማስባል መጠቀም የፈለጉ ወገኖች “ሀኪሞች በእርግጥም ተበድላችኋል በሉ እናንተ በዚያ ግፉ እኛም በዚህ እንገፋለን” አይነት የሀኪሞቹን ጥያቄ ፖለቲካዊ የማድረግና ለፈለጉት አላማ ለማዋል የመፈለግ አዝማሚያ ይታያል። የወደቀው ጋኔን ሕወሓት ጭፍሮች የሆኑ የአየር አጋንንቶቹ እነ ዳንኤል ብርሀኔ ተቃውሞውን ለማጦዝ ሀኪሞቹን ተቀላቅሎ ፎቶ እስከመነሳት ደርሰዋል፣ የሆነ ሆኖ የሀኪሞቹ ጥያቄ በወዲህም ሆነ በወዲያ በኩል ከሚደረገው ጉተታ ወጣ ብሎ መታየት አለበት ባይ ነኝ።

ሀኪምነት የተከበረ ሙያ ነው። በቃልኪዳን የታሰረ ዘር ቀለምና ሀይማኖት የሌሉት የሰውን ልጅ ህይወት በማትረፍ እርካታን የሚጎናፀፉበት፣ የሰው ዘር ወደ ምድር እንዲመጣ ምክንያት በመሆን ከወላጆች ጋር አብረው የሚፈነድቁበት፣ ህይወት ሲያልፍም ጥርስን ነክሰው በውስጥ እያዘኑ ቆፍጠን ብሎ ስራን የሚያከናውኑበት ክቡር ሙያ በሀገራችን በዚህ ሙያ ውስጥ ያለፉ ወገኖች ከፍተኛ ችግርና ስቃይ እያስተናገዱ ወገኖቻቸውን ሲያገለግሉ ኖረዋል፣ ዛሬም ሀኪሙ ዘመናትን የተሻገሩ ችግሮችን ተሸክሞ በሙያው ላይ ነው እናም ጥያቄዎቹን ለምን ለመንግስት አቀረበ መባሉ ነውርም ሃጢአትም ነው።

በእርግጥ የሀኪሞች ጥያቄዎች ብዙ ናቸው። እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎችም አሁን ሀገራችን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ በጥቂት ጊዜ ሊመለሱ የሚችሉ አይደሉም፣ ነገር ግን በአርሲ የሀኪሞች መደብደብ እርሱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀኪሞች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በውይይቱ እንዲገኙ የተደረጉ ሰዎች የተመረጡበት መንገድና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ የተናገሯቸው መረን የለቀቁ ንግግሮች እንደ መንስኤ ሆነው ሀኪሙ አሁን ለደረበት ሁኔታ አብቅቶታል እናም ገመድ ጉተታው አብቅቶ ወደ መፍትሄዎቹ መኬድ አለበት ባይ ነኝ።

መንግስት ማስፈራራቱን ማቆም አለበት፣ ሁሉንም ባይሆንም አስቸኳይና መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን መመለስ አለበት ግላቭ፣ ጄኔሬተር፣ የደም መለኪያ ወ.ዘ.ተ. የሌለበት ሆስፒታል የሚሰራ ሀኪም ስራ ማቆም አድማ ባያደርግም ስራ ቆሟል ስለ መሰረታዊ ችግሮቹ የሚያሰላስል ሀኪም ተረጋግቶ የሰው ህይወት ማትረፍ አይችልም ጥቃቅን ነገሮችን ዛሬ በመመለስ ቀጣዩን በሂደት በመመለስ ላይ ተግባብቶ የህመምተኛ ህይወት መቀጠል አለበት።

በሀኪሞችም በኩል በዚህ የተከበረ ሙያ ውስጥ በእጆቻቸው ለመፈወስ ከፈጣሪያቸው በመቀጠል ተስፋ አድርገው ለወራት ወረፋ ይዘው የሚጠባበቁ ወገኖቻቸውን በመመልከት ከስሜት በፀዳና ሀገራቸውንና ወገናቸውን ሊጠቅም በሚችል ጥያቄ የማቅረቢያና የተቃውሞ መንገድን በመቀየስ ጥያቄዎቻቸው እስኪመለሱ ድረስ መታገል አለባቸው።

የህክምና ባለሙያነት የተከበረ ሙያ መሆኑን ያልተረዱ አክቲቪስቶችም ነገሩን የሚያዩበት መንገድ ሀኪሙን በማስቆጣት ወዳልተፈለገ መንገድ ሊወስዱ ከሚችሉ አስተያየቶች ሊቆጠቡ ይገባል በተነሱ ህዝባዊ እምቢተኝነቶች ውስጥ ክፉዎች በጥይት ሲያነጥፉት የነበሩትን ወገን በድፍረት እንዳላከሙልን ሁሉ በአጣሪ ኮሚሽኖች ሀኪሞች በድፍረት ምስክርነት እንዳልሰጡ ሁሉ (መለስን ያንቀጠቀጠውን የነዳኛ ፍሬህይወትን አጣሪ ኮሚሽን ሪፖርትን ልብ ይሏል) ላለፉት27 አመታት የት ነበራችሁ ብሎ ማንጓጠጥ የድፍረት ድፍረት ነው። የሀኪሞች ጥያቄ ፖለቲካዊ አይደለም በሁሉም ሞያ ስነ ምግባር የሌላቸው ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ በሀኪሞችም ዘንድ እንዳሉ መታወቅ አለበት በጅምላ ሙያውን ለማራከስ መሞከር ራስን ጭምር ማዋረድ ነው።

አንዲት ሀገር አለችን ሀገራችን እንደ ሀገር እንድትኖር በየዘርፉ ያሉ ሙያተኞች ያስፈልጓታል ይልቁኑም ሀኪሞች!!!

እናም ሰከን እንበል

LEAVE A REPLY