የዛሬ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. የለገጣፎ ተፈናቃዮች አቤቱታቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ማቅረባቸውን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ 183 ያህሉ ተፈናቃዮች ያቀረቡት አቤቱታ ኦሮሚያ ክልል የሊዝ አዋጁን መሠረት አድርጎ ያወጣቸው ደንቦችና መመርያዎች መኖሪያ ቤታችን ስላፈረሰ የእኩልነትና ሰብዓዊ መብታችን ተነክቷል፤ እናም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ይሰጥልን የሚል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 37 ፍትሕ የማግኘት መብት በሰጠበት ሁኔታ በፌዴራል የሊዝ አዋጁ ለባለንብረቶቹ ምንም ዓይነት ካሳ ሳይከፈል የማስለቀቅ ሥልጣኑን ለአስፈጻሚ አካል ብቻ መስጠቱ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል ይላል- ሰነዱ፡፡ 6 ነጥቦችን የያዘው አቤቱታ ለጉባኤው የቀረበው ግንቦት 2 ነው፡፡ በለገጣፎ ያለ ፕላን የተሠሩ ተብለው ከወራት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች መፍረሳቸው ይታወሳል፡፡ ተፈናቃዮቹ የ70 ሚሊዮን ብር ጉዳት ካሳ ክስ ሊመሰርቱ መሆኑም ታውቋል፡፡

2. የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኢትዮጵያ መድሃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የቀድሞ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን ዋዜማ ዘግባለች፡፡
ኃይለ ሥላሴ ቢሆን (የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር)፣
የማነብርሃን ታደሰ (ም/ዋና ዳይሬክተር)፣ ሙከሚል አብደላ (የግዥ ዳይሬክተር) እንዲሁም በተለያዩ የግዥ ሃላፊነቶች የነበሩት ኢንጅነር አሸናፊ ሁሴን፣ ያሬድ ይገዙ፣ አንዳርጋቸው ሞግሪያ እና ያለው ሞላ በመጀመሪያው የዋና ወንጀል አድራጊነት መዝገብ ተካተዋል፡፡ ተከሳሾቹ የግዥ መመሪያዎችንና አዋጁን በመተላለፍ ለመከላከያ ሚንስቴር ያለጨረታ በ13 ሚሊዮን ብር መድሃኒት እንዲገዛ አድርገዋል- የሚል ነው አንደኛው ክስ፡፡ ኢንጅነር አሸናፊና አንዳርጋቸው ገና በቁጥጥር ስር አልዋሉም፡፡ ችሎቱ ለተከሳሾቹ ዋስትና መብት ከልክሎ፣ የክስ መቃወሚያቸውን ለግንቦት 19 እንዲያቀርቡ አዟል፡፡

3. የኢትዮጲስ ጋዜጣ ዘጋቢ ምስጋን ጌታቸው ዛሬ ሥራ ላይ እንዳለ በፖሊስ ተደብድቦ መታሰሩን የአዲስ አበባ ባልደራስ ጽ/ቤት ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ስንታየሁ ቸኮል በባልደራሱ ፌስቡክ ገጽ አስታውቋል፡፡ ጋዜጠኛው ዛሬ ጠዋት 4 ኪሎ አካባቢ ቤታቸው ሲፈርስባቸው የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ቅሬታ ለመዘገብ ሲሄድ ነው ከቢሮ እንደወጣ ፖሊሶች የደበደቡትና ያሰሩት፡፡ ካሜራውንና ሌሎች እቃዎችንም ቀምተው ወደ ጣቢያ ወስደውታል ብሏል፡፡ ለዐይን እማኝነት አራዳ ፖሊስ ማዠዣ ጣቢያ የገቡ ሰዎች ከግቢው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ኢትዮጲስ የባልደራሱ ሰብሳቢ በሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤትነት የምትታተም ሳምንታዊ ጋዜጣ ናት፡፡

4. ከሐምሌ 2010 ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ሥዩም መኮንን ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ትናንት ለሠራተኞቹ ገልጸዋል፡፡ ከሃላፊነት የለቀቁበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግን አላሳወቁም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለድርጅታቸው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ከኢቢሲ ከሃላፊነታቸው ለመልቀቅ ሲጠይቁ ነበር- ብሏል ሪፖርተር

5. ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሥራ ፍቃድ ሥራ መስራት አይችሉም- ብሏል የኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ፡፡. ሸገር አንድ የመስሪያ ቤቱን ሃላፊ ጠቅሶ እንደዘገበው ኤርትራዊያኑ በዘፈቀደ እየገቡ ቢሆንም በቅርቡ ግን መንግስት እንደማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ እንዲስተናገዱ የሚያስችል ሕግ ለማዘጋጀት ሃሳብ አለ፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኤርትራ መንግስት ጋር ገና ንግግር ላይ ነን ብለዋል፡፡

6. ዐለም ዐቀፉ የአስትሮኖሚ ኀብረት አዲስ ለተገኘ ግዙፍ የህዋ አካል ኢትዮጵያ ስም እንድታወጣለት ዕድል እንደሰጣት የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ ዕድሉ ለኢትዮጵያ የተሰጠው በዘርፉ እያሳየች ያለችውን ለውጥ ከግምት በማስገባት ነው ብሏል አክሎ፡፡ አዲስ የተገኘው ግኝት ኮኮብና ኮኮቧን የምትዞር አንዲት ፕላኔት የያዘ የፕላኔት ስርዓት ነው ተብሏል፡፡ ዜጎች ለህዋው አካል በ920 ነጻ የስልክ መስመር አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ስም በማውጣት እንዲሳተፉም ጽ/ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

LEAVE A REPLY