በዱላ መቀጣቀጥ ብትችልም
መደባደብ፣ ማባረር፣ መግደልም
መፍትሔ ሆኖ ላያኖርህ ላያቆይህ
ጥፋት ነው ለጥፋት ማቆብቆብህ
በጣጥሰህ ሸንሽነህ ካልከፋፈልካት
ሰላም አውለህ ሰላም ካሳደርካት
አገርህ እንደኹ ለሁልኽም በቂህ ናት
አንባጓሮህን አሽቀንጥረህ ወርውረህ
የዘር ቁርሾ ቀለምህን ከግንባርህ ፍቀህ
ተመካክረህ ተግባብተህ እደር ከወንድምህ
አንተስ፣ እሱስ፣ እሷስ ካለኢትዮጵያ ማን አላችሁ
አንድ እኮ ናት! የጋራ መኖርያ ቤታችሁ
ዛሬ ቀንቶህ የወጣልህን የነፃነት ፀሐይ
የዴሞክራሲና የአንድነት አዋይ
እንዳትጋርደው ደም ባጠቆረው ከፋይ
በነገር ሠሪዎች የማያቋርጥ ትብትብ
በአዋካቢ ተዋክበህ ሕሊናህ እንዳይሰለብ
እጅህ ለጭካኔ እንዳይዘረጋ ሰብስብ
ምላስህን ከክፉ ወሬ ፍሰት ገድብ
ሹማምንትም ሹመታችሁ …
ለሕዝብ መሆኑን አውቃችሁ
እየተሰማ ካለው የመከፋፈል የቁም ኩነኔ
እየታየ ካለው ዓይን ያወጣ ጭካኔ
ወገኖች አገራችሁን ለማዳን ተነሱ
አደራ መረከባችሁን አትርሱ
ለውጡን በመጠበቅ ሕግን በማስከበር
ሥርዓት እንዲይዝ ዳር እስከ ዳር አገር
እናንተ ላይ ወድቋል ትልቅ ኃላፊነት
በቀና ልቦና ሕዝባችሁን ምሩት
ሠራዊቱም የማንንም ወገን ሳትይዝ
የሕዝብ ሰላም እንዳይጠፋ እንዳይመረዝ
የኃላፊነት ድርሻህን በአግባቡ በመወጣት
እናት አገርህን ከሞት እልቂት አድናት
አባቶችም ከፈጣሪ በጸሎታችሁ
ከሕዝብም በመንፈሳዊ ትምህርታችሁ
በመገናኘት የሰላም ሐዋርያ ሆናችሁ
በጥንካሬ በትጋት መቆም አለባችሁ
ጸሐፍትም እንዳያጠፋን፤ የመጨካከን መዘዙ
ብዕራችሁን ለአንድነትና ለፍቅር ምዘዙ
ፖለቲከኛም ሆንክ አክቲቪስቱ
ኢንቨስተሩ ባለሀብቱ
የውጪውም የአገር ቤቱ
ፖለቲካው የሚቃናው
ሀብትህ ፍሬ የሚያፈራው
አገር ስትኖር ስትቆም ነው
ዘር ጥላቻ መከፋፈል
እንዳይሰፋ አብረህ ታገል
አለበለዚያ ግን፤ ማንም ሆንኽ ማንም
የትም ቦታ ነዋሪ ብትሆን የትም
ተከባብረህ መኖር ካልቻልክ በሰላም
ተገዳድለህ መፍትሔ ማምጣት አትችልም