የዛሬ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. አዲስ አበባ መስተዳድር ዜጎች ህገ ወጥ ቤቶቻቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እንዲያፈርሱ 2 ሳምንት ቀነ ገደብ ሰጥቷል- ሲል ዘግቧል አዲስ ስታንዳርድ፡፡ አስተዳደሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህገ ወጥ የመሬር ወረራና የህገ ወጥ ቤቶች ግንባታ አሳሳቢ እንደሆነበት ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በዚሁ ጉዳይ አፈጻጸም ላይ ከክፍለ ከተማ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ጋር ተመካክረዋል፡፡ ካልሆነ አስተዳደሩ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እርምጃ ይወስዳል፡፡ በህገ ወጥ ግንባታው ተሳታፊ ሆኖ የተገኘ የመንግስት አመራር በህግ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ሕገ ቤቶች የሚፈርሱባቸው ክፍለ ከተሞች ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊ፣ ንፋስ ስልክ፣ ላፍቶ፣ ጉለሌና የካ ናቸው፡፡

2. የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ-ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) 21 የስራ አስፈጻሚ አባላትን መምረጡን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ በመንግስት ትይዩ በተዋቀረው ስራ አስፈጻሚ ውስጥ የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋና ምክትል መሪው አንዷለም አራጌን ጨምሮ 7 ሰዎች በአባልነት ተካተዋል፡፡ የፓርቲውን የዕለት ተዕለት በሚከታተለው ስራ አስፈጻሚ ውስጥ ደሞ የፓርቲው ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ፣ ምክትላቸው ጫኔ ከበደ፣ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊው ዋሲሁን ተስፋዬን ጨምሮ 14 የፓርቲው አባላት ተመርጠዋል፡፡

3. ገቢዎች ሚንስቴር ከውጭ ለሚገቡ ያገለገሉ እቃዎችና ተሽከርካሪዎች ይሰጥ የነበረውን የቀረጥ ቅናሽ ማንሳቱን ዋዜማ ተረድታለች፡፡ ከዚህ በኋላ መንግሥት ከተሽከርካሪዎች ዋና ዋጋ ላይ ብቻ ቀረጡን እያሰላ ይጥላል፡፡ እስካሁን ባለው አሰራር ከውጭ የሚገቡ ያገከገኩ ተሽከርካሪዎች ዋና ዋጋ ላይ የአገልግሎት ዋጋ ተብሎ እስከ 30 በመቶ ከቀረጣቸው ላይ ተሰልቶ ይቀነስላቸው ነበር፡፡ አዲሱ መመሪያ የሀገር ውስጥ የመኪና ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሬ ያመጣል ተብሎ ተገምቷል፡፡

4. በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ ሰልፈኞቹ “የአማራ ድምጽ ይከበር” የሚል መፈክር አሰምተዋል- ብሏል የDW ዘገባ፡፡ “መፈናቀልና ወከባ ይቁም”፣ “ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ይቁም”፤ “ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር” የሚሉ መፈክሮችንም አስተጋብተዋል፡፡ የፌደራልና የክልሉ መንግሥት ለችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡም ጠይቀዋል፡፡ ሰልፉን ያዘጋጁት የሸዋ አማራ ተወላጆች አስተባባሪዎች ናቸው ተብሏል፡፡

5. ቦይንግ ኩባንያ አብራሪዎችን ይሰጡት የነበረውን ጥቆማ ትኩረት ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋን ማስቀረት ይቻል እንደነበር ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ በተለይ የአሜሪካ አየር መንገድ አብራሪዎች ለኩባንያው በርካታ የማሻሻያ ሃሳቦችን አቅርበው ኩባንያው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏቸዋል፡፡ ኩባንያው ችግሩን በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ አብራሪዎች ለማላከክ መሞከሩ ደሞ ይቅር የማይባል ነው፤ የፈጸመው ተግባርም አሳፋሪ ነው- ሲል ወቅሷል የአሜሪካ አውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር። ባለሙያዎች አውሮፕላኑ መሠረታዊ የንድፍ ስህተት እንዳለበት ያምናሉ፡፡

6. የኢትዮጵያ፣ ኬንያና ኡጋንዳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጋራ ድንበሮች አርብቶ አደሮች ትጥቅ እንዲፈቱ ጥሩ ማድረጋቸውን ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ መሪዎቹ ከቀናት በፊት በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ኬንያ ውስጥ ተገናኝተው መክረዋል፡፡ መንግሥታቱ በተመሳሳይ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ እንዲጀምሩም ጥሪ አድርገዋል፡፡ በሦስቱ ሀገሮች የጋራ ድንበሮች 8 ሚሊዮን ያህል ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች እንዳሉ ይገመታል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ዳሰነችና የኬንያ ቱርካና ጎሳዎች የሚያካሂዱት ከብት ዘረፋ ብዙ ሕይወት የሚጠፋበት ሆኗል፡፡ በአካባቢው አንድ ክላሽንኮቭ ከ200-300 ዶላር ይሸጣል፡፡

LEAVE A REPLY