አባ መፍቀሬ ማን ናቸው?

አባ መፍቀሬ ማን ናቸው?

የወሎ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ የደን ቀንን በማስመልከት ባዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ደን ሲነሳ ሁልጊዜ ስማቸው የታይዞ የሚነሳውን፣ በሕዝበ ክርስቲያኑና በሕዝበ ሙስሊሙ የሚወደዱትንና የሚከበሩትን ባህታዌ፣ የብዝሃ ህይወት አባትና የልማት አጋፋሪ ለሆኑትን ለአባ መፍቀሬ ሰብ እውቅና ሰጥቷል።

አባ መፍቀሬ ማን ናቸው?

አባ መፍቀሬ ሰብን በተመለከተ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ ወቅት

“የተሸጡት አባት” በሚል ርዕስ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ላይ አስፍሮት የነበረው ፅሁፍ እነሆ:

በአውሮፓ ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ አንድ የአራተኛው መክዘ ታሪክ አለ፡፡ ድኾችን እጅግ የሚወድ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት ምንም ነገር የማያግደው፤ ከእራሱም አብልጦ ለሌሎችን የሚሞት አንድ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው በበጎ ምግባሩ የተነሣ ስሙ ተረስቶ ‹እኁ ቅዱስ- ቅዱሱ ወንድም› እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ በታሪክ ድርሳናትም የተመዘገበው በዚሁ ስም ነው፡፡ ሠርቶ የሚያገኘውን ምንም ለሌላቸውና ለምነው እንኳን ለማግኘት ዐቅም ላነሣቸው በመስጠት የታወቀ ነበር፡፡

አንድ ጊዜ የሚሰጠው ነገር አጣ፡፡ ብዙ ችግረኞች ደግሞ መልካም ዜናውን ሰምተው ጥቂት ነገር ለማግኘት ወደ እርሱ ዘንድ መጡ፡፡ ምን ይስጣቸው፡፡ የሚያያቸው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ ገንዘቡን ከጨረሰ በኋላ ከሩቅ ሀገር ሳይቀር በመምጣታቸው አዘኑ፡፡ መመለሻ እንኳን የላቸውም ነበር፡፡ በመጨረሻ እኁ ቅዱስ አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹እኔን ሽጡኝና ተካፈሉ› አላቸው፡፡ እነዚያ ችግረኞችም ምን አማራጭ ስላልነበራቸው እርሱን በባርነት ሸጡትና ገንዘቡን ተካፈሉ፡፡

ይህ ታሪክ በታሪክነቱ ሲወሳ የኖረ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን ታሪክ ራሱን ይደግማልና አንድን ታሪክ የሚካፈሉ ሁለት ሰዎች በሺ ዘመናት ልዩነት ውስጥ ሳይቀር ይፈጠራሉ፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም እንደ ‹እኁ ቅዱስ› የተሸጡ ሰው አሉ፡፡ እዚያ ደቡብ – ወሎ ደሴ፡፡

ደሴ የምትታወቀው በፍቅር ከተማነቷ፣ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ዜማዎች አምባ በመሆኗ፣ በንጉሥ ሚካኤል ታሪክና በአይጠየፍ አዳራሽ፣ በዘመናዊው የኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥም በያዘችው ቦታ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ያልተነገረላቸው ፣ በደሴ ተራሮች ላይ የሚያበሩ፣ የሚንቀሳቀሱ፣ የሚተነፍሱና ሕይወት ያላቸው የደሴ ውድ ቅርስም አሉ፡፡

እኒህ ሰው የትውልድ ቦታቸው ወሎ እንዳልሆነ በቅርበት የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ምናልባት ወደ ሰሜን ሸዋ አካባቢ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ እስካሁን ግን የተወለዱበትን ቦታና ዘመን በርግጠኝነት የሚያውቅ የለም፡፡ እርሳቸውም ሃይማኖታቸውንና ምግባራቸውን እንጂ ሰው ትውልዳቸውንና ጎሳቸውን እንዲጠይቃቸውም እንዲያውቅላቸውም አይፈልጉም፡፡ ከጥንት ጀምሮ የሚያውቋቸው የደሴ ከተማ ሽማግሌዎች ግን እርሳቸውን ያወቁበትን ጊዜና በዚያ ጊዜ የስንት ዓመት ሰው ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገመት እድሜያቸውን በሰባና ሰማንያ መካከል ይገምቱታል፡፡ ወደ ጎንደር ለትምህርት ሲሄዱ ደሴ ደረሱ አሉ፡፡ እዚያ የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናትና የተጎዱ ሰዎችን አዩ፡፡ እዚህ በተግባር የሚሠራ ሥራ እያለ እዚያ የቃል ትምህርት ለመማር ምን ወሰደኝ ብለው እዚያው ደሴ ቀሩ አሉ፡፡

እኒህ ሰው የሚታወቁት በሥራና በፍቅር ነው፡፡ በደሴ ከተማ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት በማሳነጽ፣ ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር አሻራ አኑረዋል፡፡ እንዲያውም እርሳቸው ካልገቡበት የሚሳካ አይሆንም ብለው ደሴዎች እስኪገምቱ ድረስም ደርሰዋል፡፡ እርሳቸው ካዘዙ ምደርም ትታዘዛለች እንኳን ሰው ይባላል፡፡ የርሳቸው በጎ ሥራ ግን በዚህ የሚያቆም አይደለም፡፡ የተቸገረና የተጨነቀ ሰው ካገኙ ግንባር ቀደም ደራሽ ናቸው፡፡ ለርሳቸው ዘርና ሃይማኖት ሰውን ለመርዳት መመዘኛዎች አይደሉም፡፡ ሰውነት ብቻ ይበቃቸዋል፡፡ ይህ ርዳታቸው ከመከራ ያወጣቸው፣ ከችግር የታደጋቸውና ሕይወታቸውን ያቀናላቸው ሰዎች ስለ እኒህ አባት ሲያወሩ ከማያቋርጥ ዕንባ ጋር ነው፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ከንግግር ይልቅ እርሳቸውን እያሰቡ ዝም ብለው በማልቀስ ይገልጧቸዋል፡፡

መቼም ለአንዳንዱ አብዝቶ አይደል የሚሰጠው፡፡ እርሳቸው የአካባቢ ጥበቃ አርበኛም ናቸው፡፡ በዚህ የእርግና እድሜያቸው እንኳን መኮትኮቻና መቆፈሪያ፣ አካፋና ባሬላ ይዘው በደሴ ተራሮች ላይ ዛፍ ሲተክሉ ይውላሉ፡፡ ደሴን በአራቱ መዓዝን ስታዩዋት አረንጓዴ ብትሆንባችሁ አትገረሙ፤ እርሳቸው ከአርባ ዓመት በላይ ለፍተውላት ነው፡፡ ለእርሳቸው ዛፍ የሚቆርጥ ቀርቶ ቅጠል የሚበጥስም የማርያም ጠላት ነው፡፡ አይከፈላቸውም፤ አልተመደቡም፤ ደብዳቤ የሰጣቸው የለም፤ እርሳቸው ግን የሀገሬ መራቆት የኔ መራቆት ነው ብለው ደን ሲተክሉና ሲከባከቡ ይኖራሉ፡፡

የእኒህን አባት ስም የሚያውቀው የለም፡፡ ስማቸው ተረስቷል፡፡ ስማቸው የተረሳው ሕዝብ ሌላ የፍቅር ስም ስላወጣላቸው ነው፡፡ ሕዝብ የንቀት ስም፣ የውርደት ስም፣ የሃፍረት ስም ይሰጣል – ለጠላው፡፡ ሕዝብ የፍቅር ስም፣ የክብር ስም፣ የቁልምጫ ስም ይሰጣል – ላፈቀረው፡፡ ለእርሳቸውም ወላጆቻቸው ያወጡላቸውን ስም የሚያስረሳ ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ መፍቀሬ ሰብእ (ሰውን የሚወድድ፣ ሰውም የሚወደው) የሚል ስም፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብእ ይባላሉ፡፡

ድፍን ደሴ ይታዘዛቸዋል፡፡ ንጽሕናቸውንና ሰው ወዳጅ መሆናቸውን ይመሰክርላቸዋል፡፡ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም እኩል ልጃቸው ነው፡፡ የግሼንን መንገድ ሲያሠሩ በደሴ ከተማ የታወቁት የሙስሊም ባለሀብት ‹ሃምሳ ሺ ብር ሰጡኝ› ብለው ነግረውኛል፡፡ ቤታቸው ብትገቡ ትደነቃላችሁ፡፡ ወንበርና አልጋ ነው ያላቸው፡፡ አልጋው ላይ መጻሕፍት በክብር ተደርድረዋል፡፡ ‹‹አልጋ ለንጉሥ ነው፤ ነገሥታቱ ደግሞ መጻሕፍቱ ናቸው፡፡ አልጋው ላይ የሚኖሩት እነርሱ ናቸው›› ይላሉ፡፡ ሰው ለሀገሩና ለወገኑ መልካም ሲሠራ ካዩ የለበሱትንም ካባ ቢሆን አውልቀው ይሸልማሉ፡፡ ስለ እርሳቸው ሲነገር አይወዱም እንጂ ስለ መልካም ሰዎች ተናግረው አይጠግቡም፡፡

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፡፡

የደሴ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተጀመረና ለመጨረስ ገንዘብ አጠረ፡፡ ወዲህ ቢባል ወዲያ ገንዘብ ከየት ይምጣ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ አውጥተው አውርደው አንድ ሃሳብ አመጡ፡፡ አባ መፍቀሬ ሰብእ እንደ እኁ ቅዱስ መሸጥ አለባቸው፡፡ ሄዱና አማከሯቸው፡፡ ‹‹አባ እርስዎን ሸጠን የገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ልንጨርስ ነው›› አሏቸው፡፡ ‹‹እኔ ምን አወጣላችኋለሁ›› አሉ ገርሟቸው፡፡ ‹‹በደንብ ያወጣሉ፡፡ ብቻ ለመሸጥ ይስማሙልን›› አሏቸው፡፡ ‹‹ካወጣሁ እንኳን እንድ ጊዜ ዐሥር ጊዜ ልሸጥ›› አሉ አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡

በእርሳቸው ስም የርሳቸው ፎቶና ስም ያለበት ቶምቦላ ተዘጋጀ፡፡ ድፍን ደሴ – ሙስሊም ከክርስቲያኑ ተሻምቶ ገዛው፡፡ መፍቀሬ ሰብእ አይደሉ፡፡ ያልተሰበሰበውን ጨምሮ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ተሸጡ – አባ መፍቀሬ ሰብእ፡፡ ሌሎቹ የሀገር ሀብት፣ ቅርስና ታሪክ በሚሸጡበት ዘመን አባ መፍቀሬ ራሳቸውን ለሀገርና ለወገን፣ ለእምነታቸውና ለዓላማቸው ሸጡ፡፡ ሌሎች በቤተ እምነቶች ውስጥ ተደብቀው ለጥቅማቸው ሲሉ የምእመናንን ገንዘብ በሚበሉበት ዘመን፤ ለምእመናን ሲሉ አባ መፍቀሬ ሰብእ ተሸጡ፡፡ ሌሎች በጎቻቸውን ለራሳቸው ሲሸጡ፤ አባ መፍቀሬ ግን ለበጎች ሲሉ ራሳቸውን ሸጡ፡፡ እልም ባለ በረሃ ውስጥ የምትገኝ ቀዝቃዛ ምንጭ ተስፋ የቆረጠውን ሁሉ እንድታረካ፤ ታማኝነትና ሕዝብን መውደድ፣ በዓላማ መኖርና ለዓላማ መሠዋት እየጠፋ ባለበት ዘመን፣ እርሳቸውን ማየት እንደዚያ ነው፡፡

via petros Ashenafi

LEAVE A REPLY