የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ዐርብ ዐበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. ፌደራል ፖሊስ ፍርድ ቤት የሰጠኝን የመጥሪያ ትዕዛዝ ለተከሳሽ ጌታቸው አሠፋ ለማድረስ ጊዜ አጥሮኛል ብሏል- ክሱን ለሚያየው ችሎት። እንደ ኢቢሲ ዘገባ ትዕዛዙ ግንቦት 8 ተሰጥቶ፣ መጥሪያው ከፍርድ ቤቱ የወጣው ግን ግንቦት 14 መሆኑን ጠቅሶ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ችሎቱም ለሰኔ 3 ቀጥሯል፡፡ የሲዲ የምስክርነት ማስረጃዎችን ግን ካንዱ በስተቀር ለተከሳሾች ማድረሱን አስረድቷል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ምስክሮቹ ማንነታቸው ሳይገለጽ ምስክርነት እንዲሰጡ ጠይቆ፣ በጉዳዩ ላይ ሰኔ 3 ውሳኔ እሰጥበታለሁ- ብሎታል ችሎቱ፡፡ ከጌታቸው ጋር ተከሰው ችሎት የቀረቡ ሌሎች ተከሳሾች ደመወዛቸው ተቋርጦ መቸገራቸውን አስረድተው ነበር፤ ችሎቱ ግን በጉዳዩ ላይ ሥልጣን እንደሌለው ገልጾ ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንዲያመለክቱ መክሯቸዋል፡፡

2. ዛሬ ችሎት በመቅረብ ላይ በነበሩት የፖሊስ ኮማንደር አለማየሁ ኃይሉ ላይ ደብደባ ተፈጽሞባቸዋል- ብሏል የኢቢሲ ዘገባ፡፡ የተወሰኑ የቂሊንጦ እስረኞች ከተከሳሾቹ ፖሊሶች ጋር ወደ ችሎት ሲቀርቡ መንገድ ላይ በመገናኘታቸው ነበር የቂሊንጦዎቹ ታራሚዎች በኮማንደር አለማየሁ ላይ አካላዊ ጥቃት ያደረሱት፡፡ ችሎቱም ድርጊቱ እንደተነገረው በተከሳሽ ፖሊሶች ላይ ሊሰማ ይዞት የነበረውን ቀጠሮ ወደ ሐምሌ 1 አስተላልፏል፡፡ እነ ኮማንደር አለማየሁ የደህንነት ስጋት አለብን በማለታቸው ከቂሊንጦ ወደ ቃሊቲ እንዲዛወሩ ተደርጎ ነበር፡፡ 10 የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የተከሰሱት ከ2005-2010 ባለው ጊዜ በተጠርጣሪዎች ምርመራ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ ተጠርጥረው ነው፡፡

3. የኢትዮጵያ ዜግነት ማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የመሠረቱት ፓርቲዎች ራሳቸውን ስለማክሰማቸው እንደማያውቅ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተናግሯል፡፡ ኢዜማም ለቦርዱ ቀርቦ ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ አልተመዘገበም- ብለዋል የቦርዱ የኮምኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ዘመን ሲናገሩ፡፡ የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ ሊያዘን አይችልም፤ ፓርቲዎቹ በመተዳደሪያ ደንባቸው በጉባዔ ወስነው አዲሱን ፓርቲ መስርተዋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አርበኞች ግንቦት 7፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲና የጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ ተዋህደን ኢዜማን መስረተናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

4. ፖሊስ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት አባል ሽመልስ ለገሠን ዛሬ እንዳሰራቸው የባላዳራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ለኢትዮ-ታይምስ ተናግሯል፡፡ ታሳሪውን ለመጠየቅ ወደ አራዳ ፖሊስ ጣቢያ የሄደው ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ስንታየሁ ቸኮልም ላጭር ጊዜ ታስሮ ተለቋል፡፡ ሽመልስ የታሰረው የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕገ ወጥ ቤቶችን አፈርሳለሁ ማለቱን ተከትሎ ካቀረበው የአደባባይ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

5. ከፍተኛ የጦር ሠራዊቱ አዛዦች ዛሬ ብሄራዊ ቤተ መንግሥቱን ጎብኝተዋል፡፡ በቤተ መንግሥቱ ቅጽር ግቢ የሚካሄዱትን የተለያዩ ፕሮጀክቶችንም ጎብኝተዋል ብሏል- የጠቅላይ ሚንስቴር ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ዜና፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም በአካል ተገኝተው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት ለከተማዋ ስላለው ጠቀሜታ ለሠራዊቱ አዛዦች ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

6. ኤርትራ ነጻነቷን ከኢትዮጵያ ያገኘችበትን 28ኛ የነጻነት በዐል ዛሬ ስታከብር ውላለች፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትናነት የ“እንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ የትግራይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልም በትግራይ ቴሌቪዥን ዛሬ ባሰተላለፉት መልዕክት የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት የኤርትራን ነጻነት ቀናዒ መሆኑን መግለጻቸውን DW ዘግቧል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ባለፈው ዐመት ሰላም ስምምነት ከደረሱ ወዲህ ኤርትራ የነጻነት በዐሏን ስታከብር ያሁኑ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ በቅርቡ ከኤርትራ በኩል መልሶ የተዘጋው ሁለቱ ሀገሮች ድንበር እስከዛሬው ዕለት አልተከፈተም፡፡

7. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክልሉ ሚሊሽያና የቀበሌ ታጣቂዎች መሳሪያ ይዘው እንዳይንቀሳቀሱ መከልከኩን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡ በክልሉ በሞላ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ይዞ መንቀሳቀስም ታግዷል፡፡ ከመከላከያ ሠራዊቱና ፌደራል ፖሊስ ውጭ በወሰን አካባቢ የክልሉ ፖኪስና ልዩ ሃይልም በ5 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ጦር መሳሪያ ይዘው መግባት አይችሉም፡፡

8. ምርጫ ቦርድ በመጭው ሰኞ ለጋዜጠኞች መግለጫ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ መገናኛ ብዙሃንም ተገኝተው እንዲዘግቡ ጥሪ አድርጓል፡፡ መግለጫው በቦርዱ አዲስ አወቃቀር፣ በአዳዲስ ቦርድ አባላት አሰያየም፣ በምርጫ በጀት፣ በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጥያቄና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መራዘምና ተፈናቃዮች በምርጫው ላይ ስለሚፈጥሩት ተጽዕኖ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል- ይላል የአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ፡፡

LEAVE A REPLY