በሶማሌ ክልል የጄል ኦጋዴን እስር ቤት ኃላፊ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተሰጠ

በሶማሌ ክልል የጄል ኦጋዴን እስር ቤት ኃላፊ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተሰጠ

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው የሶማሌ ክልል ውስጥ 
በርካታ አሰቃቂ ድርጊቶች ሲፈጸምበት እንደቆየ 
የሚነገርለት የጄል ኦጋዴን እስር ቤት ኃላፊ የነበረው
ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ቢቢሲ || የቀድሞው የእስር ቤቱ ኃላፊ ሐሰን ኢስማኤል ኢብራሂም በቅጽል ስሙ “ሐሰን ዴሬ” ሶማሊያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለኢትዮጵያ ተላልፎ በመሰጠቱ ወደ ጅግጅጋ ተወስዷል። ግለሰቡ ክስ ወደ ተመሰረተበት አዲስ አበባ ሊወሰድ እንደሚችልም ተነግሯል።

ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግለሰቡ የተያዘው ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋር በምታዋስነው ጎልደጎብ ተብላ በምትጠራው የድንበር ከተማ ውስጥ ነዋሪዎች ለጸጥታ ኃይሎች በሰጡት ጥቆማ አማካይነት ነው።

ግለሰቡ በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በተለይ ደግሞ ጄል ኦጋዴን ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ ተፈጽመዋል በሚባሉ ሰቆቃዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ዋነኛ ሚና አለው ተብሎ ሲፈለግ ቆይቷል።

ሐሰን ኢስማኤል (ሐሰን ዴሬ) የቀድሞውን የክልሉን ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ኦማርን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ውስጥ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ክስ ከተመሰረተባቸው 40 ያህል ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ተነግሯል።

ግለሰቡ በቀድሞው የሶማሌ ክልል መስተዳደር ውስጥ በከፍተኛ የደኅነትና የጸጥታ ኃላፊነቶች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሰራ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሶማሌ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ፣ የማረሚያ ቤቶች ኃላፊ፣ የጄል ኦጋዴን ኃላፊ እና በክልሉ ልዩ ፖሊስ ውስጥም በኮሎኔልነት አገልግሏል።

በሶማሌ ክልል የሚገኙ እስር ቤቶች በተለይ ደግሞ ጄል ኦጋዴን ውስጥ ተይዘው የነበሩ እስረኞች ላይ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸው እንደነበር የፌደራል መንግሥቱና የክልሉ መንግሥት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በእስር ቤቱ ይገኙ በነበሩ በመቶች በሚቆጠሩ እስረኞች ላይ ይፈጸሙ ከነበሩት ድርጊቶች መካከል ከመሬት በታች ባሉ ጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ማስቀመጥ፣ የተለያዩ ዓይነት ሰቆቃዎች፣ ከአደገኛ የዱር እንስሳት ጋር እስረኞችን ማስቀመጥ፣ አስገድዶ መድፈርና የመሳሰሉ ድርጊቶች እንደነበሩ ተገልጿል።

LEAVE A REPLY