ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለኮሌራ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ክትባት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል። የኢንስቲትዩቱ ም/ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ፤ ከአለም የጤና ድርጅት በተገኘ ድጋፍ የኮሌራ በሽታ ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ለኤፍ.ቢ.ሲ ገልጸዋል፡፡
ክትባቱን በቅድሚያ ለበሽታው በጣም ተጋላጭ ወደ ሆኑ ቦታዎች ለማሰራጨት የቅድመ ሁኔታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤አሁን ወደ ሀገር ውስጥ በገባው ክትባት ሁሉንም አካባቢዎች በፍጥነት ማዳረስ የማይቻል በመሆኑ፣ በቀጣይ ተጨማሪ የክትባት ግብዓት ከድርጅቱ ለመጠየቅ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የኮሌራ በሽታ ከግል ንጽህና ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በሰፊው ስለሚተላለፍ፤ ህብረተሰቡ የግል ንፅህናውን በመጠበቅና አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች መቆጠብ እንዳለበት የተናገሩት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የበሽታው ምልክት ሲታይም ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ህይወቱን ሊታደግ እንደሚገባ አሳስበው፤ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ 356 የኮሌራ ህሙማን የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከህሙማኑ መካከል 197 በአማራ፣ 122 በኦሮሚያ፣ 33 በሶማሌ፣ 8 በትግራይ ክልሎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ 6 ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ በሶማሌ ክልልም የአተት በሽታ የታየ ሲሆን፣ እስካሁን በሽታው ኮሌራ መሆኑ ግን እንዳልተረጋገጠም ገልጸዋል፡፡