ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አስችኳይ የመሪዎች ስብሰባ ኢትዮጵያን ጨምሮ 44 ሀገራት የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን የተፈራረሙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ነፃ የንግድ ቀጠናውን ከመፈረም ባሻገር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀድቃ ለአፍሪካ ህብረት በማስረከብ ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ ውሳኔውን መተግበር መጀመሯን ኤፍ.ቢ.ሲ ዘግቧል፡፡
በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ የተደረሰውን ስምምነት ታሪካዊነት ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጋር ያስተሳሰሩት ሲሆን፤ ነፃ የንግድ ቀጠናው ወደ ተግባር መግባቱ በማደግ ላይ ላለው የአህጉሪቷ ምጣኔ ሀብት ጉልህ ሚና እንደሚጫወትም አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር በሪሁን አሰፋ ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውና፤ በስምምነቱ የሚኖረው ሰፊ የገበያ እድል ተጨማሪ ባለሃብቶችን ለመሳብ እንደሚረዳ ሲገልጹ፣ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ (የምጣኔ ሃብት ባለሙያና አማካሪ) ደግሞ፤ በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ሲገቡ፣ በስምምነቱ ያለው ምርትን ከኮታና ቀረጥ ነጻ የማስገባት ሂደት ለባለሃብቶች ከፍ ያለ ጠቀሜታ ያመጣል እምነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡