ሚስጢራዊው የኢሳት ቦርድና ውዝግቡ || ክንፉ አሰፋ

ሚስጢራዊው የኢሳት ቦርድና ውዝግቡ || ክንፉ አሰፋ

“የኢሳት ቦርድ ማን ነው?” የሚለው “የሚሊዮን ብር” ጥያቄ በህዝብ ዘንድ ውዥንብር መፍጠሩ እንግዳ ሊሆን አይችልም። ምላሹን የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ እንኳ ሊያውቀው ካልቻለ፣ በስሙ የሚነገድበት ሰፊው ህዝብ እንዴት ሊያውቀው ይችላል? አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ስራውን እንጂ ጀርባውን ሳይመለከቱ ስለገቡበት፣ ከመጋረጃ ጀርባ የሚዶለተውን ሴራ ሁሉ ላያውቁ ይችሉ ይሆናል።

በጋዜጠኝነት ስም ኢሳት ላይ ለተቀመጡ የግንቦት ሰባት ካድሬዎች ግን ይህ ጉዳይ ምስጢር አይደለም። ገለልተኞቹም ቢሆኑ “ኢሳት የግንቦት ሰባት ነው።” የሚለውን ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ሳያውቁ ነው የገቡበት ለማለት ይከብዳል። “ኢሳት የህዝብ ነው” እያሉ የህዝቡን ኪስ ሲያጥቡ ከርመው መጨረሻ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አደባባይ ወጥተው፣ በኬኛ ጨዋታ ጥሬ ሃቁን ተፉት። የግንቦት ሰባት የአስር አመታቱ ድል እና ገድል ሲሰላ በቀሪ ሂሳብ የሚገኘው ኢሳት ብቻ እንደሆነ ጸጉራቸውን አከክ ሳያደርጉ፣ አይናቸውንም ሳያሻሹ ገልጸዋል።

“የህዝብ አይን እና ጆሮ ነው” ሲባል የነበረው ተቋም ችግሩ የገንዘብ ቢሆን ኖሮ እዳው ገብስ ነበር። እስካሁን ይረዳ የነበረው ዲያስፖራ አሁንም እጁን የሚያጥፍበት ምክንያትም አይኖርም። የገንዘብ ችግርን ለመፍታት አንድ ሺህ መንገዶች አሉ። ምክንያቱ ገንዘብ ከሆነ ስራው በሙሉ ቀጥ ይላል እንጂ በተቀናሽ ሰበብ የቂም ሂሳብ አይወራረድም። ጉዳዩ “ቦርድ” በሚል ማደናበርያ ከሽኖ አጎብዳጆችን የማቆየት እቅድ ስለመሆኑ የተቋሙን የውስጥ ታሪክ የኋሊት መመልከቱ ይጠቅማል።

ጋዜጠኞቹ አዲስ አበባ ገብተው በሜዲያ “ኢሳት የግንቦት ሰባት አይደለም” ብለው የሞገቱበት አመክንዮ ገና ከህዝቡ ጆሮ ገብቶ ሳይዋሃድ፣ ከከሰመው ግንቦት ሰባት እንደ መብረቅ ዱብ ያለው መግለጫ በራሱ ድርጅቱ በነሱ ላይ ያለውን የንቀት ደረጃ ያመላክታል። በዚሁ ድራማ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ የተመለከትነው ገቢር ደግሞ የትእይንቱን ዘውግ ከትራጀዲ ወደ ኮሜዲ ወስዶታል። ሕዝብ ሆነው ኢሳትን ከግንቦት ሰባት የተረከቡት የራሱ የግንቦት ሰባት ጸሃፊ የነበሩት ናቸው። ድርጊቱ ሰዎቻችን የሕዝብን አስተሳሰብ ምን ያህል ዝቅ አድርገው እንደሚመለከቱት ይጠቁመናል።

ዲሲ ላይ የተነሳው የቅነሳ በትር እና ገመድ ጉተታ እርግጥ እንደተባለው “በገንዘብ ችግር ነው?” ወይንስ “ድብቅ የፖለቲካ ሴራ አለበት?” ለሚለው ጥያቄ በተቀዳሚ አስረጂ የሚሆነው የአቶ ኤፍሬም ማዴቦ ቃለ­ምልልስ ይሆናል። የፓርቲው አመራር የነበሩት ኤፍሬም ማዴቦ፤ ኤል፣ ቲ፣ ቪ፣ ላይ ቀርበው ጋዜጠኞቹ “እውቀት አልባ፣ ዘርን ከዘር የሚያፋጁ፣ ከነባራዊ ሃቅ የራቁ.. ወዘተ ” እያሉ ሲወርፉ ከጠረጴዛው ስር አንዳች ነገር እየተጎነጎነች እንደነበር የምትጠቁም አብሪ ጥይት ናት። ወትሮም “ትግላችን ስልጣን ለመያዝ አይደለም” እያሉ በነጭ ውሸት እዚህ የደረሱ ሰዎች፣ ጋዜጠኞቹን በኢህአዴግኛ ቋንቋ መወንጀል እና የመወረፍ ሞራሉ ሊኖራቸው አይችልም። ለሙግቴ ሁለተኛው ማሳያ ደግሞ ከዚህ በታች የምጽፍላችሁ ታሪክ ነው። ይህንን አጭር ታሪክ ስታነብቡት የኢሳት ቦርድ ማን እንደሆነም ታውቁታለችሁ።

ከወዲህ እና ወዲያ እያንጓለለ ያለው ነፋስ አስፋልቱ ላይ ያለውን አዋራ በመጠኑም ቢሆን ማንሳት ጀመረ እንጂ ትብያውን ጠርጎ አላጠፋውም። ነፋስ ሳይሆን አውሎነፋስ ሲነሳ ግን አዋራውን ጠራርጎ አየሩን ያጠራዋል የሚል እምነት አለኝ። በበርካታ ጋዜጠኞች ጥያቄ መሰረት፣ ይህችን አጭር መልዕክት የምለቅቀው በመጽሃፍ መልክ በስፋት ካሰፈርኩት ማስታወሻ ላይ ጨልፌ ነው።

“መጨረሻው ጅማሬውን የሳየናል።” ይላል ማኪያቬሊ፣ ዘ­ፕሪንስ በሚለው መድብሉ። ሩቅ ተመልካች የሆነ ጅማሬ ግማሽ መንገድ ላይ አይቆምም። መሰረቱ ከጸና ግንብ ሳይሆን አሸዋ የተሰራ ቤት እና መርህ አልባ ተቆም ደግሞ አንድ ናቸው። “በአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ጅብ ሲጮህ ይፈርሳል!” እንዲሉ የሁለቱም ግዜ ጠብቀው በጩኸት ይጠፋሉ።

ይህን ጽሁፍ ሳሰጋጅ የሙያ ሃላፊነት እና የሞራል ግዴታ ብቻ ይዞኝ አይደለም። ማን ይመስክር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ በጥንስሱ ላይ አሻራችንን ያሳረፍን ዜጎች፣ ጅማሮውን መመስከሩ ለግንዛቤ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። የምጽፈውን ሁሉ በማስረጃ እደግፈዋለሁ። አላማዬ ሰዎችን ወይንም ድርጅትን ለመውቀስ ሳይሆን የምሰጠው ምስክርነት ለሌላው ትምህርት ይሆን ዘንድ በሚል እሳቤ ነው። ነገርን ከስሩ ለመመልከት አንዳንድ የሚጎረብጡ ነገሮች ማንሳት ግን ግድ ይላል። “በሙያ ነፃነት ላይ አልደራደርም” ማለቴ ያስከፈለኝ ዋጋ ቢኖርም ቂም ግን አልቋጠርኩም። በዚህ ላይ አንዳች ስህተት አለ ብሎ የሚያሳብ ወገን ካለም ፊት ለፊት ለመሞገት ዝግጁ ነኝ። መረጃን በማስረጃ ፣ ሃሳብን ደግሞ በሃሳብ

ማሸነፍ የሚሳናቸው ድኩማኖች ማንነታቸውን ደብቀው በሚተፉት ቅርሻት የኖረንበት እና የለመድነው ጉዳይ ስለሆነ አያሳስበኝም። ድርጅቱ እንደ አንድ የትግል ስትራቲጂ የነደፈው የወፍ ዘራሾች ስድብ እና ዘለፋ ግን መሬት ላይ ያለ እውነታን ፈጽሞ አይቀይረውም።

በስደት የምንገኝ ጋዜጠኞች፣ ሕዝብን በመረጃ ሃይል በማስታጠቅ፣ በሃሳብ ልዕልና የሚያምን ትውልድ ለመገንባት ያቀድነው አላማ ነበር። ህወሃት የሚባል አንድ ቡድን ብቻ ተይዞ የሚቀለድበት የመረጃ ሞኖፖንሊ ለመስበር ነበር እቅዳችን። ይህንን እቅድ ወደ ተግባር ቀይሮ እውን ለማድረግ ይህ ነው የማይባል መስዋዕትነት ቢከፈልበትም፣ ውሎ ሲያድር ግን በሴራ ፖለቲካ የመጠለፍ እጣ ገጥሞታል። ይህን መራራ ሃቅ ወደኋላ እመለስበታለሁ። ከዚያ በፊት ግን ስለ ግንቦት ሰባቱ ኢሳት አፈና እና አፋኝ ገጽታ አንድ አስረጂ ክስተት ላንሳ።

ርዕዮት አለሙ ከቴዎድሮስ ጸጋዬ ጋር ያደረገችው ቃለ መጠይቅ መታገዱ የአፈናውን ጭንብል ገለጥ አደረገው እንጂ እንዲህ አይነቱ ጸያፍ ተግባር የጀመረው አሁን አይደለም። ሃምሌ ወር 2014 ቨርጂያ የሚገኘው ኢሳት ስቱዲዮ እንድገኝ ሲሳይ አጌና በተደጋጋሚ ደወለልኝ። “የሃገር ልጅ” የሚል ፕሮግራም ላይ ከደረጀ ደስታ ጋር እንድንወያይ ቀጠሮ ይዘን ነበር። ከደረጀ ደስታ ጋር ስቱዲዮ ገብተን ለሁለት ሰዓታት ያህል ተወያየን። በውይይታችን በጦር የተደራጁ ተቃዋሚ ሃይሎች ላይ ያለውን ድክመት እና በተለይ ደግሞ በኤርትራ በኩል የተጀመረው ትግል ላይ እምነት እንደሌለኝ መናገሬን አስታውሳለሁ። አምስተርዳም ከተመለስኩ በኋላ ፕሮግራሙ እንዳይተላለፍ መታገዱን ሰማሁ። ምክንያቱን አልተገለጸም። ደረጀ ደስታ እንዲህ አይነቱ ነገር ሲደጋገምበት ኢሳትን በገዛ ፍቃዱ መሰናበቱ ተሰማ። ነጻ እና ገለልተኛ የነበረው ጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ ከዲሲ ስቱዲዮ ሲሰናበት እነሱ ደስተኞች እንደነበሩ ግልጽ ነው። በአፈናው ላይ የሲሳይ አጌና ዝምታ ግን ሳይገርመን አልቀረም።

የትግል አማራጩ ሕዝባዊ አመጽ ነው ብሎ መናገር የግንቦት ሰባትን እቅድ ይጸረር ይሆናል። በሃሳብ ደረጃ የአንድ ሰውን አመለካከት መቋቋም አለመቻል በራሱ ማንነታቸውን ይነግረናል። በኤርትራ የተጀመረው ትግል የውሸት ነበር የሚለውን ጥሬ ሃቅ ዛሬ ጀነራል ከማል ገልቹ እና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አረጋግጠውልናል። ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን አልነበረም ማለት የድርጅቱን አቋም አያንጸባርቅም ማለት እንዳልሆነም ድርጅቱን የሚተቹ ወገኖችን በማፈን አሳይቶናል።

በዚያ እቅፍ ውስጥ ተቀምጦ፣ የመብት ጠበቃ ሆኖ ለመቅረብ የሚሰራው ድራማ ግን ያሳዝን ነበር። ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ከኢቲቪ ጋዜጠኛ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንዳይተላለፍ ተደረገ የሚለውን ዜና ለመስበር ሲጣደፍ፣ ራሱ አፋኝ ሆኖ ስለ አፋኞች የመናገርን ሞራሉን ከየት እንዳመጣው ጠያቂ እንኳ አልነበረም።

እናም ኢሳት “የህዝብ አይን እና ጆሮ ነው” ብለን ለፈጠርነው እንኳ ያልራራልን፣ ሌላውን ሞጋች እና ተቺ ያስተናግዳል ማለት ዘበት ባይሆን ይገርማል። እንዲህ እያልኩ በርካታ አፈናዎችን እጠቅሳለሁ።…ወደፊት በስፋት። አሁን ግን በኢሳት ምስረታ፣ ቃል የተገባውን እና በተግባር የተደረገውን ለመቃኘት ዘጠኝ አመት ወደ ኋላ ልመልሳችሁ።

እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 2010 ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአሜሪካ ስልክ ደውሎ ስለሜዲያ አስፈላጊነት እና ተግባራዊ ስለማድረጉ እቅድ አወራኝ። በነገሩ ላይ በተደጋጋሚ ከተነጋገርንበት በኋላ አንድ ያልተጻፈ ስምምነት ላይ ደረስን። ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ የአዲስ ድምጹ አበበ በለው ጋዜጠኞችን ጠርቶ በአማራጭ ሜዲያ ዙርያ ያወያይ ነበር። በሆላንድ የምንገኝ ጋዜጠኞች የህወሃትን የሜዲያ ሞኖፖሊ ለመስበር ነጻ እና ገለልታኛ ሆኖ የሚሰራ ሳተላይት ቴሌቭዥን ለማቋቋም ደፋ ቀና የምንልበት ወቅት ነበር። ከወዳጆቼ ጋር ሆነን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደተራመድን መግለጼንም አስታውሳለሁ።

በሆላንድ መንግስት የተመዘገበ የሜዲያ ፈቃድ ከማውጣት ባለፈ፣ በአውሮፓ ህብረት በኩል ለስራው የሚሆን በጀት ተጠይቋል። በፕሮጀክት ነደፋው ፕ/ር አል ማርያም እና አንጋፋው ጋዜጠኛ ከፋለ ማሞ ተሳትፈዋል። ሚስ አና ጎሜዝ በአውሮፓ ፓርላማን ባደረገችው ከፍተኛ ውትወታ የአውሮፓ ፓርላማው “ለኢትዮጵያ አማራጭ ሜዲያ ያስፈልጋል” የሚል ውሳኔ አስተላልፎ ስለነበር በህብረቱ ትልቅ ተስፋ ነበረን። በሚስጥር ተይዞ የነበረው ይህ ጉዳይ በ”ኢንድያን ኦሽን ኒውስ ሌተር” በተዛባ መንገድ ወጣና ነገሩን አወሳሰበው። ይህን የተገነዘበው ህወሃት ዲ.ኤል.ኤ ፓይፐርስ የተሰኘውን የህግ ተቋም በሚሊዮኖች ቀጥሮ ወደ አውሮፓ አመጣ። በመጨረሻ በአውሮፓ ህብረት በኩል የነበረው ተስፋ ጨልሞ እጃችንን አጥጥፈን በተቀመጥንበት ወቅት ነበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሃሳቡን ያካፈለን።

ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በነበረው ስምምነት መሰረት፣ ተቋሙ ነጻ ሆኖ ተቃዋሚዎችንም ጭምር እንዲተች፣ ህወሃትን ሳይቀር አቅርቦ በሃሳብ መሞገት እንዲችል፣ የዕለት ስራው በጋዜጠኞች ኢዲቶርያል ቦርድ እንዲተዳደር፣ ገለልተኛ አማካሪ ቦርድ እንዲኖረው የሚል ይገኝበታል። የፋይናንሱን ችግር በተመለከተም ኢሳት ራሱን ችሎ በእግሩ እስኪቆም ድረስ ድርጅቱ ግዚያዊ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገባ። ኢሳት የሚለውን ስያሜ እና ከሶማሌዎች ያገኘውን የሳተላይት ልምድ ይዞ ከለንደን ብቅ ያለው የአባይ ሜድያው ግሩም ይልማ ነው።

ቢሮ ለማደራጀት አበበ ቦጋለ ከቤልጅየም እየተመላለሰ ብዙ ለፍቷል። መስፍን አማን ከሆላንድ፣ ከስዊዘርላንድ ለዚሁ ስራ የመጣው ጋዜጠኛ እያደር አዲስ፣ ኤፍሬም ደመቀ፣ ዳናኤል ነጋሽ፣ ዳኛቸው መኮንን…እና ጆኒ ሲሚንቶ እየለበሱ ስቱዲዮ ገነቡ። መሰረቱ ተጥሎ አቧራው ሲጠረግ አሁን ከፊት ቀደም ቀደም እያሉ ከሚታዩዋቸው አንዳቸውም አልነበሩም። ሁሉም በመጨረው ሰዓት እጅ ታጠበው ወደ ማዕድ የቀረቡ ናቸው። ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋላኞች ደግሞ ፊተኞች ይሆኑ ዘንድ ግን ይህ ሆነ። እነ ሲሳይ አጌና በአዲስ አበበ ሚለኒየም አዳራሽ ተገኝተው፤ ጠጠር እንኳ ያላቀበሉትን የፓርቲ ሰዎች ስም እየጠሩ ሲያመሰግኑ፣ የመሰረት ድንጋይ የጣሉትን ግን እንዳልነበሩ መቁጠራቸው ሳያስተዛዘብ አይቀርም። ሌሎችን እያሳነሱ ከመግዘፍ ይልቅ እያገዘፉ መግዘፍ ትልቅነት መሆኑን ከመጋቢ ዮናታን አክሊሉ መማሩ መልካም ነው።

በተባለውም መሰረት ስራው ከመጀመሩ አስቀድሞ በእነ ፕ/ር አል ማርያም የተሰየመ አለማቀፍ አማካሪ ቦርድ ተቋቋመ። ቦርዱ በወ/ት ሜሮን አሃዱ፣ አቶ አበበ በለው፣ አቶ ግደይ ዘርዓጺዮን፣ አቶ ሙሳ እና ሼክስፒር ፈይሳን ያካትታል።

መስፍን አማን አስተዳደር ክፍል ሃላፊ፣ ፋሲል የኔአለም ደግሞ የኢዲቶርያል ሃላፊ ሆነው ስራው በጥድፊያ ተጀመረ። አማካሪ ቦርዱ ለስራው ጥራት እና ቅልጥፍና እጅግ ተግቶ ቢሰራም ረጂም አልተጓዘም።

ኢሳት በመላው ኢትዮጵያ በስፋት መታየት እና ተጽእኖ መፍጠር ሲጀምር ውስጥ ያሉ ነገሮች መለዋወጥ ጀመሩ። የተባለው የቲም ስራ ቀረና ኢዲቶርያል ቦርዱን አንድ ግለሰብ ብቻ እንዲይዘው ተደረገ። ቀጥታ ግንኙነቱ እና ትዕዛዝ የሚቀበለው ከዶ/ር ገድሉ ኪዳኔ ሆነ። ዶ/ር ገድሉ የግንቦት ሰባት አመራር አባል እና የዶ/ር ብርሃኑ ቀኝ እጅ ነው። በትክክለኛ ስሙ አናውቀውም ነበር። በአካልም እስካሁን አይተነው አናውቅም።

ለኢሳት መልካም ስም ያሰጠው አለምአቀፉ የአማካሪ ቦርድ እንዲፈርስ የሄዱበት መንገድ አሁን ስመጥር ጋዜጠኞችን ካባረሩበት መንገድ ጋር ይመሳሰላል። ግንቦት ሰባትን ከመሰረቱት አራት ሰዎች መካከል አንደኛው መስፍን አማን ከጀርባ ምን እየተቦካ እንደሆነ ያውቃል። የእ ፕ/ር አል ማርያም እና አበበ በለው ከፊት መታየት በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮ ነበር። ይሁንና እነሱን አታስፈልጉም ብሎ ማባረሩ ችግር ስላለው ሌላ የዲፕሎማሲ ቋንቋ ተመርጦ “ካሁን በኋላ በአመት ሁለቴ ብቻ ነው የምታስፈልጉት” ተባሉ። አማካሪ ቦርዱ ከዚያች ቅጽበት ወዲህ አልተገኘም።

በጎን ደግሞ መስራች ቦርድ የሚል ህጋዊ አካል እንዲፈጠር በዶ/ር ብርሃኑ በኩል ተጠየቅኩ። ቀጥሎም የአራት ሰዎች ስም ተላከልኝ። ዶ/ር አዲሱ መሸሻ ከዲሲ(ዶ/ር ገድሉ ኪዳኔ)፣ ዶ/ር ሙሉአለም አዳም ከኦስሎ፣ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ከሆላንድ፣ ዶ/ር አዚዝ መሃመድ ከዳላስ እና አቶ መላኩ አድነው ከለንደን።

በህጉ መሰረት የኢሳትን እጣ ፈንታ የሚወስኑት እኔን ጨምሮ እነዚህ አምስት ሰዎች ናቸው ማለት ነው። እነዚህን ወንድሞች ሳስመዘግብ ከጀርባው አንዳች የተደበቀ ነገር ይዟል የሚል ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አልነበረኝም። ለመርህ የቆሙ ናቸው ብዬ የምከራከርላቸው፣ ለፍትህ ይሞታሉ ብዬ የምምልላቸው ሰዎች በምንም አግባብ ልጠርጥራቸው አልችልም። ከእኔ በስተቀር ሁሉም የግንቦት ሰባት አባላት መሆናቸውን ያወቅኩት ግን ትንሽ ዘግይቼ ነበር።

በመላው አለም የሚገኙ ጋዜጠኞች የሚወከሉበት የኢዲቶርያል ቦርድ እንዲቋቋም ያቀረብኩት ጥናት እና ፕሮፖዛል በቦርዱ ውድቅ ሲሆን ነበር መባነን የጀመርኩት።… አሁን ኢድቶርያል ቦርድ የለም። አማካሪ ቲም የለም። ቦርዱ እና ቦርዱን የሚያዘው አንድ ሰው የሚመራው ተቋም ሆኖ ቀረ። ቀጣዩ እርምጃ ለግንቦት ሰባት የማይመቹ ጋዜጠኞችን በበጀት ምክንያት መቀነስ ነበር። ስዊዘርላንድ ከሚኖርበት መጠለያ ተጠርቶ የመጣው ጋዜጠኛ እያደር አዲስ ጉዳይ ለሰሚው ያምማል። እያደር አዲ በሆላንድ የጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ በህመም እንዲሰቃይ ተፈርዶበት ነበር። ይህንን ጉዳይ ወደፊት በስፋት እንሄድበታለን።

ከ 20 ዓመት በላይ የሬዲዮ መምርያ ሃላፊ የነበሩ አቶ ከፋለ በበጀት ሰበብ መቀነስ ግን ከፍተኛ አዋራ ስላስነሳ በዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የሚመራ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደረገ። የአጣሪ ኮሚቴው ረጂም ግዜ ወስዶ ችግሩን አጣርቶ የሰጠው ውሳኔ ግን በውስጥ ታፍኖ ቀረ። ከአመታት በኋላ ደረጀ ሃብተወልድ የእያደር አዲስን ጉዳይ ይዞ ላስታረቅ ብሎ ገባና በዚያው ኢሳት ውስጥ ተቀጠረ። ኢሳት ስራ ሲጀምር ደረጀ ለምን እንዳልተቀጠረ ሃላፊው ሲጠየቅ ­ የሱን ቋንቋ ላለመጠቀም “እምሮው የተረጋጋ አይደለም” አይነት ምላሽ ነበር የተሰጠው።

በርካታ ምስጢር የያዘው የአጣሪ ኮሚቴው መረጃ አሁንም በእጄ አለ። እንዳስፈላጊነቱ ለህዝብ ይፋ ይሆናል።

የሚሊዮኑን ብር ጥያቄ ለመመለስ ­ በህግ ተመዝግቦ የሚገኘው ቦርድ ከላይ የተጠቀሰው ቢሆንም፣ በቦርዱ ስም ውሳኔ የሚያስተላልፈው ግን አንድ ግለሰብ ነው። አንዳንዴም ነአምን ዘለቀ ብቅ ይልና የቦርዱን ሃሳብ (በግል እያለ) ያስተላልፍልናል።

ይቀጥላል….

LEAVE A REPLY