ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ ከሰናይ ሚዲያና ጌት የንግድና የኢንቨስትመንት ማማከር ድርጅት ጋር በመሆን የሰናይ ቲቪ ምስረታ፣ እንዲሁም የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭን በተመለከተ አርብ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት በሂልተን ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተከልክሏል፡፡
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሊሰጥ የነበረው ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሆቴሉ የፀጥታ ሁኔታ ያሰጋኛል የሚል ደብዳቤ ስለፃፈልን ከልክለነዋል በማለት የአዲስ አበባ ፖሊስ መግለጫ አውጥቶ ነበር:: ኢትዮጵያ ሆቴል በበኩሉ ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጠው ምላሽ፣ ፈፅሞ እንደዛ ዓይነት ጥያቄ እንዳላቀረቡ መግለፃቸውንና የሆቴላቸው ስምና የተዋጣለት አገልግሎትም በሌላ ገጽታ የቀረበባቸው መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
የሰናይ ቲቪ ምስረታን በተመለከተ ግንቦት 30 ቀን ከ4 እስከ 6 ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የአዳራሽ ኪራይን በተመለከተ፣ በቀን 27/9/2011 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የጠየቁ ሲሆን ሂልተን ሆቴልም ለቀረበለት ጥያቄ ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም አዎንታዊ ምላሽ በደብዳቤ አሳውቋል:: በዚሁ ዕለት የ12.995 ብር (የአስራ ሁለት ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አምስት ብር) ክፍያ ተፈፅሞ ነበር፡፡ ሆኖም በዛሬው ዕለት እሮብ ግንቦት 30 ቀን የሰናይ መልቲ ሚዲያ መስራቾችና ጋዜጥኞች በቦታው ቢገኙም የታሰበውን ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አልተቻለም፡፡
ሕጋዊ የደብዳቤ ልውውጥ በተካሄደበትና ተገቢው ክፍያ በተፈፀሙበት ሁኔታ እንዴት እንከለከላለን? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የሆቴሉ የሽያጭ ክፍል ረዳት ስራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ሰርጸወልድ “ከሚመለከተው ክፍል ፍቃድ ካላመጡ መግለጫ እንዳይሰጡ ተብሎ፣ ከደህንነት መ/ቤት ተደውሎ ስለተነገረን መስጠት አትችሉም፡፡” ካሉ በኋላ፤ የሆቴሉን ጥበቃዎች ጠርተው የአዳራሹን በር በማዘጋት “ይሄ ከእኔ አቅም በላይ ስለሆነ፣ ግቢውን ለቃችሁ ውጡልኝ” ሲሉ በስፍራው የተገኝው ዘጋቢያችን ታዝቧል፡፡
“ለውጥ አለ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተገንብቷል” እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወቅት፤ ሚዲያ የማቋቋምን ሂደት በተመለከተ የሚደረግ ጋዜጣዊ መግለጫን ያለ አግባብ መገደብ አሳዛኝም፣ አሳፋሪም እንደሆነ እስክንድር ነጋ ተናግሯል:: እስክንድር በወቅቱ መጥተው ለነበሩት በርካታ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እውነታውን በማስረጃ በማስደገፍ ለህዝብ እንዲያቀርቡ ጥሪ አስተላልፏል:: በቀጣይም ሀሳቡ ዕውን እስኪሆንና ነፃ የሕዝብ ሚዲያ ማቋቋም እስኪችል ድረስ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ቢገጥመው ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡