ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ብዙዎችን ባሳዘነ መልኩ በቅርቡ በከሚሴ እና አጣዬ አካባቢ የተደራጀ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 50 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በድርጊቱ ተሳትፈዋል በሚል ከተያዙት ግለሰቦች ጋር ሕገ-ወጥ መሳሪዎችም አብረው መያዛቸውን የኮሚሽኑ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ሚዲያ ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ግለሰቦቹ በአካባቢው ከወራት በፊት ተፈፅሞ በነበረው ግጭት የተጠረጠሩ መሆናቸውን አስታውሰው፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የሕግ አካላት ጋር በመሆን ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ፣ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ከአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከሕግ አካላት የተውጣጣ የመርማሪ ቡድን ተዋቅሮ ጉዳዩን በቦታው በመገኘት በጥልቀት ሲያጣራ መቆየቱን የሚያስረዳው ዜና፣ የምርመራ ቡድኑ ባጣራው መሠረት በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች የተደራጀ ወንጀል ሲፈፅሙ እንደቆዩ በማስረጃ መረጋገጡን ለማወቅ ተችሏል። በከሚሴና በአጣዬ አካባቢ በቅርቡ የደረሰው ጥቃትን በተመለከተ ድርጊቱን የፈጸመው የኦነግ ታጣቂ ኃይል ነው የሚሉ በርካታ ዘገባዎች በወቅቱ ከተለያየ አቅጣጫ መሰማታቸው ይታወሳል፡፡