ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ቅዱስ ሲኖዶስ ሰሞኑን ባካሔደው ጉባኤው የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን በኦርቶዶክስ ስም በጉባኤ ተወግዘው የተለዩትን፣ “ቅብዐት እና ጸጋ” በማጫፈር፣ ‘ኦርቶዶክስ ቅብዐት’ እና ‘ኦርቶዶክስ ጸጋ’ የሚል የምዝገባ ቅጽ ማካተቱን ተቃውሟል::
“ቅብዐት” እና “ጸጋ” ለተባሉ መናፍቃን፣ በዘዴ ዕውቅና መስጠት አንዲቷን ቤተ ክርስቲያን የሚከፋፍል ነው ብሏል ሲኖዶሱ፡፡ ድርጊቱ በሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር በመኾኑ ቅጹ በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል፡፡” ሲልም ማሳሰቢ ሰጥቷል፡፡
“ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ተቋም የሚጠራበት ፍጹምና አጠቃላይ መጠሪያ ስም እንጂ ቅጽልም አይደለም፡፡ “ቅብዐት” እና “ጸጋ” ለዘመናት ሲያፋጁን ኖረው ለመጨረሻ ጊዜ፣ በአኩስም እና በቦሩ ሜዳ ጉባኤያት፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንት ተረተው የተዳከሙና የጠፉ ኑፋቄዎች ናቸው ብሏል ሲኖዶሱ::
በሌላ በኩል ባህላዊውን ዋቄፈና እንደ ሃይማኖት፣ ከኦርቶዶክሳዊነት ጋራ በታሪክና በይዘት ተነጻጻሪ፣ ብሎም ተገዳዳሪ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን ማሸማቀቅና ይዞታዋን መቀራመት ሊቆም እንደሚገባ አስጠንቅቋል:: ከመንበረ ፓትርያርክ ጀምሮ በየአህጉረ ስብከቱ ስለ ቆጠራው አስፈላጊነት፣ በውጤቱ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች ዙሪያ ለካህናት እና ለምእመናን በቂ ትምህርትና ቅስቀሳ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ጉዳዩ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ አፈጻጸሙን የሚከታተል ከሰበካ ጉባኤ ማደራጃ፣ ከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲሁም ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያዎች የተውጣጣ አካል በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለመሰየም ተወስኗል:: ይህ አካል በቆጠራው ላይ የቤተክርስቲያን ስጋቶች ናቸው በሚባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግስት አካል ጋር በመነጋገር ነገሮችን በጥልቀት ይከታተላል ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና በቅዱስ ሲኖዶስ ትናንት ግንቦት 30 ቀን የከሰዓት በኋላ ባካሄደው ስብሰባ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡
በሕጉ መሠረት ቅዱስ ፓትርያርኩ የብፁዕ ዋና ጸሐፊውን መሠየም በደብዳቤ በመግለጽ አዲስ የተመረጡትን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ በፊርማቸው ይሾሟቸዋል፡፡ በዚህ መሰረት ብፁዕ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዮሴፍ፣ የሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅትንም በቦርድ ሰብሳቢነት ይመራሉ:: ተሰናባቾቹ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በምልአተ ጉባኤው አባላት ሽልማትና ከፍተኛ ምስጋና ተችሯቸው በክብር ተሸኝተዋል፡፡