ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ የሚመራው የባለአደራው ም/ቤት (ባልደራስ) የአዲስ አበባ ነዋሪን የማደራጀት ስራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል፡፡
ም/ቤቱ በቅርቡ የከፈተውን ጽ/ቤት ባስመረቀበት እለት እንደተገለጸው የአዲስ አበባን ሕዝብ የማደራጀት ስራ በክፍለ ከተማ ደረጃ ከዛሬ ሰኔ 1ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መተግበር የተጀመረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስቀድሞ በተያዘው መርሐ ግብር መሰረት በዛሬው ዕለት የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎችን ማደራጀት ጀምሯል:: በአዲስ አበባ ዙሪያ በልዩ ጥቅም ሰበብ ሊተገበሩ የታሰቡ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ከማክሸፍ ጀምሮ አጠቃላይ የከተማዋን ነዋሪ ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅ የሚደረገው ትግል በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል ታውቋል::
ከተለያዩ የአራዳ ክ/ከተማ ወረዳዎች የመጡ በርካታ ወጣቶች ባለአደራው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ ከተማዋ በትክክለኛ መንገድ እና ሕዝብ የመረጠው ከንቲባ እስከምታገኝ ድረስ ትግሉን ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል::
የም/ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ የህዝብ ተቆርቋሪነትን ይዞ የተነሳው ባለአደራው ላይ ግልጽ የሆኑ ጫናዎች እየተደረጉበት ቢገኝም ም/ቤቱ ከሕዝብ የተቀበለውን አደራ ለማሳካት ሁሉንም መስዋዕትነት ይለፍላል ብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና የአራዳ ክ/ከተማ ነዋሪዎችን ዛሬ በጽ/ቤቱ ያደራጀው ባለአደራው ም/ቤት በ1997 ዓ.ም ልክ በዛሬው ቀን ውድ ሕይወታቸውን ላጡና በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች ለተገደሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የጧፍ ማብራትና የሕሊና ጸሎት አካሄዷል፡፡
በተመሳሳይ መ.ኢ.አ.ድ ዛሬ በጽ/ቤቱ ከአስራ አራት ዓመት በፊት ሰኔ 1 ቀን በምርጫ 97 የተገደሉ ንጹሐን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የሚዘክር የመታሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅቷል:: በመታሰቢያ ዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ሊ/መንበር አቶ ማሙሸት አማረ በተጠቀሰው ቀን በጸጥታ ኃይሎች በግፍ የተገደሉት ሰዎች ዛሬ አብረውን በአካል ባይኖሩም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ለከፈሉት መሰዋዕትነት ትውልድ ሁሌም ያስታውሳቸዋል ብለዋል፡፡