ኢትዮጵያ ነገ ዜና || 63 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና በአስፓልት ደረጃ የሚገነባው የሽኩቴ ጩልጤ መንገድ ግባታን አርብ ግንቦት30ቀን 2011 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በይፋ አስጀምረዋል።
ለመንገድ ግንባታው 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን፣ ግማሹ ኮንስትራክሽን ግንባታውን ያከናውናል ተብሏል፡፡ በ3 አመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመንገድ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት የኦሮሚያ ክልል አዲስ የመንገድ ፕሮጀክት የቁጥጥርና የማማከር ስራውን የሚሰሩ ድርጅቶች የመለየት ስራ ገና እየተከናወነ ሲሆን፤ በተያያዘም በ898 ሚሊየን ብር ግንባታው እየተከናወነ ያለው የጊንጭ ሹኩቴ የመንገድ ግንባታ አፈፃፀምም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እየተነገረለት ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከአራቱ የወለጋ ዞኖች ማለትም ከምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች አመራሮች ጋር በሰላም፣ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ላይም በኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያጋጥሙ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት የህግ የበላይነትን ማስከበር ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው፤ የሰላም እጦትን ከመሰረቱ በማድረቅ የህዝብን ደህንነትና ሰላም ማስከበር የመንግስት ግዴታ መሆኑንና ይህን ዕውን ለማድረግ አመራር ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል ሲሉ መናገራቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል፡