ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አምስተኛው የኢትዮጵያ ድንገተኛ ቀዶህክምና ሙያተኞች ማህበር ዓመታዊ ጉባዔ በአ/አ ተካሄደ:: በጉባኤው ላይ የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ ከጤና ማህበራት የተጋበዙ ተሳታፊዎች እና የማህበሩ አባላት ተገኝተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ህክምና ሙያተኞች በሀገሪቱ ሆስፒታሎች ላለፉት ስምንት አመታት መተግበር ከጀመረ ወዲህ የተገኙ ውጤቶች አመርቂ መሆናቸውን አስታውሰዋል:: በዚህ ውጤታማ የጤና መርሃ ግብር የእናቶችና ጨቅላ ህጻናት ሞት መቀነስ፣ ብሎም ጥራቱን የጠበቀ የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
በሀገሪቱ ከ830 በላይ በዘርፉ የሰለጠኑ ሙያተኞች መኖራቸውን የጠቀሱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ መለሰ ታከለ በኩላቸው፣ በተለያዩ የክልል አካባቢዎች በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ሁኔታ ውስጥም ለህብረተሰቡ የድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡