ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዳግም በተከሰተ የቆሻሻ መደርመስ አደጋ እስካሁን የአንድ ሰው አስክሬን መገኝቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት እና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ረጲ አካባቢ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በዛሬው ዕለት ሰኔ 3 ቀን በደረሰ የቆሻሻ መደርመስ እስካሁን ድረስ የደረሰው ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ተጣርቶ አልተገለጸም:: አደጋውን ተከትሎ በአካባቢው በተደረገ ቁፋሮ አንድ የ70 ዓመት አዛውንት በህይወት ማውጣት ቢቻልም፣ አለርት ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
አደጋው የደረሰው ቆሻሻ ከተጠራቀመበት አካባቢ ላይ ከተሰሩ የፕላስቲክ ቤቶች፣ እንዲሁም መንገድ ዳር ከመሆኑ አኳያ እስካሁን ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር ማወቅ አልተቻለም። አሁን ላይም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ቆሻሻው በተደረመሰበት አካባቢ የሰው ህይወት ለማዳን በኤክስካቫተር የታገዘ ቁፋሮ እያካሄዱ መሆናቸውን ለመታዘብ ችለናል፡፡
በአ/አ ኮልፌ ቀራንዮ ረጲ አካባቢ፣ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው በዚህ ስፍራ ከሁለት ዓመት በፊት በደረሰ ተመሳሳይ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል። በአካባቢው ያለውን አደገኛ የቆሻሻ ክምችት ተከትሎ በአካባቢው የሰፈሩ ዜጎችን ጉዳይ በተመለከተ የከተማዋ መስተዳድር በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያበጅ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ወገኖች ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡