ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአምራች ድርጅቶቻቸው አድራሻና ምንጫቸው የማይታወቁ፣ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ የምግብ ምርቶች ገበያ ላይ እንዳሉ በተደረገው የገበያ ቅኝት ማግኘቱን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታዉቋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ድርጅቶች ተመርተው ወደ ገበያ በተሰራጩ ምርቶች ላይ በተደረገ የገበያ ቅኝት፤ በብሔራዊ ደረጃ የተቀመጠውን መስፈርት ያላሟሉ፤ ምንም ዓይነት ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸው፤ የአምራች አድራሻ እና መለያ ቁጥር ያልሰፈረባቸው የአቼቶ ምርቶች ገበያ ላይ በተደረገው የቁጥጥር ስራ የተገኙ ሲሆን፣ በህገ ወጥ ምርቶቹ ላይም አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ግልጿል፡፡
Real Aceto (ሪል አቼቶ)፣ Munit Aceto (ሙኒት አቼቶ)፤ Herme Aceto (ሐርሚ አቼቶ)፣(ሳሚ አቼቶ)፤ Sname Trading Aceto (ሰናሚ አቼቶ)እና Saron Aceto (ሳሮን አቼቶ) የተሰኙት ጥራታቸው ያልተሟላ አቼቶዎች ላይ ተቋሙ እርምጃ ወስዷል::
ህብረተሰቡ እነዚህን የአቼቶ ምርቶችን እንዳይጠቀም አሳስቧል:: ተመሳሳይ ምርቶች በሌሎች አካባቢና የመገበያያ ስፍራዎች ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ለሚገኝ የጤና ተቆጣጣሪ፤ ለፖሊስ አካላት ወይም በፌደራል ደረጃ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በነጻ ስልክ መስመር 8482 በመጠቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡