“የለውጥ ሂደቱ ባለቤትነትና አሸናፊነት የህዝብ ነው!” ስንል ምን እያልን ነው? || ጠገናው...

“የለውጥ ሂደቱ ባለቤትነትና አሸናፊነት የህዝብ ነው!” ስንል ምን እያልን ነው? || ጠገናው ጎሹ

ከ1960/70ዎቹ ፣ ከ1980ዎቹና ከ1990ዎቹ ሁለተኛ  አጋማሽ   የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ፍለጋ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ውድቀትና ካስከተሉት አስከፊ ውጤት ከምር ተምረን ተገቢውን ባለማድረጋችን እጅግ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ያስከፈሉንና አሁንም እያስከፈሉን ያሉ ጉዳዮች በርካታ ናቸው።   ከነዚህ መካከል ግን “ህዝብ የለውጥ ሂደትና የድሉም ባለቤት ነው” የሚለውን አጠቃላይ እውነት (general truth) መሬት ላይ አውርደን አጠቃላይ እውነት ብቻ ሳይሆን እንደየ አገሩ (እንደ ተጨባጭ ሁኔታው)  በተግባር ሊተረጎም (ሊፈተሽ) የሚችል እውነታ መሆኑን ለማስመስከር ያለመቻላችን ጉዳይ ትልቁ ፈተና ነው ።  የለውጥ ሂደት ላይ ነን በምንልበት በዚህ ወቅትም በፈተናው ከባድነትና ውስብስብነት ብቻ ሳይሆን በእኛው በራሳችን የአስተሳሰብ፣ የሞራልና የተቀናጀ አሠራር ድህነት ምክንያት ትርጉም ባለው አኳኋን ከአዙሪቱ ለመውጣት  አልቻልንም ።

የተሳትፎው ስፋትና ጥልቀት እንደ የአገሩ (እንደየ ማህበረሰቡ) የእድገትና ሥልጣኔ ደረጃ (ህሊናዊና ተጨባጭ ሁኔታዎች ) ሊለያይ መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና  ምሥረታ ሂደት  እውን መሆን  የሚወሰነው  በህዝብ የባለቤትነት  ስሜትና ንቁ ተሳትፎ ሲታጀብ ብቻ ነው ።

በእውነት ከተነጋገርን በዚህ ትክክለኛ የለውጥ አካሄድ የተቃኘና እውን የሆነ የፖለቲካ ተሞክሮ ኖሮንም አያውቅም፤ አሁንም ትርጉም ባለው ሁኔታ የለም። ቢኖረንማ ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት አዙሪት ለመውጣት የዚያው ክፉ አዙሪት ፈብራኪና አከፋፋይ ሆኖ የዘለቀውና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ኢህአዴግ “የእውነተኛ ዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ መድህን እኔ ነኝ” ሲለን “ከሰማዬ ሰማያት ኋጢአትህ የተሠረየልህ ነህና ቤት ለእንቦሳ” ብለን ባልተቀበልን ነበር ። አማራጭ ህዝባዊ የፖለቲካ ሃይል (አካል) ስለ አላዘጋጀን አሜን ከማለት አልፎ እጥፍና ዘርጋ ብለን ከመቀበል ውጭ አማራጭ አልነበረንም። ከምንቆጥረው ረጅም የአገርነት ታሪክና  ከአስተሳሰብና የሞራል ድህነታችን  አንፃር ሲታይ  እንዲህ አይነቱ  የተሸናፊነት ፖለቲካ ሥነ ልቦና ቢያሳዝን እንጅ አይገርምም ።

 “ህዝብ የለውጥ ባለቤትና አሸናፊ!” ነው የሚለው መፈክር  ወደ መሬት ወርዶ የለውጥ ህሊናዊና ማቴሪያላዊ ሃይል እንዲሆን ያለማስቻል የፖለቲካ ውድቀት ውጤቱ ከዚህ የተሻለ ከቶ ሊሆን አይችልም ።

“ የለውጥ ሂደት ባለቤትነት ፣አሸናፊነትና  የውጤቱም ተጠቃሚነት የህዝብ ነው” በሚለው አጠቃላይ የፖለቲካ እምነት (አመለካከት) እውነትነትና መሠረታዊ መርህነት ላይ የማይስማማ ካለ በድንቁርና  ሥር የሚኖር ወይም ጭራቃዊ በሆነ የግል ወይም የቡድን ፍላጎት ጨርሶ ህሊናው የታወረ መሆን አለበት ።

እጅግ ፈታኝ ጥያቄ የሚያጋጥመን ግን  ይህን አጠቃላይ እውነትና መሠረታዊ መርህ ወደ የገሃዱ ዓለም የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ እውነታ አውርደን ስንፈትሸው ነው። ባለፈው ግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን አይወድቁ ውድቀት እየወደቅን እዚህ የደረስንበት ዋናው  ምክንያት ይህንኑ ጥያቄ በቅንነትና በትክክል ለመመለስ ከመቻል ወይም ካለመቻል ጋር በጥብቅ  የተቆራኘ ስለሆነ ነው ።

ተነሳን ስንል ይበልጥ በከፋ ሁኔታ ተመልሰን እየወደቅን ከመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ከምንገኝበት የፖለቲካ አዙሪት መውጣት የምንችለው  “ህዝብ ወሳኝና አሸናፊ ነው!”  የሚለው  አጠቃላይ እውነት  ከትርክታችን ማድመቂያነት የዘለለ ለማድረግ አለመቻላችን  መሆኑን በቅንነትና በደፋርነት ተቀብለን ተገቢውን ያደረግን እለት ብቻ ነው ። ምክንያቱም  ወደ መሬት ወርዶ ህሊናዊና ቁሳዊ ሃይልበመሆን የመከራና የውርደት እድሜን ማሳጠር በማይችል የፖለቲካ መነባንብ  እውነተኛ የሥርዓት ለውጥን  እውን ማድረግ  አልተቻለንም።  የሚቻለንም አይሆንም ።

የህዝብ የተሳትፎና የወሳኝነት ትርክትን ወይም ንድፈ ሃሳብን ወደ መሬት አውርዶ የለውጥ ትግል ሂደቱን ከግቡ የሚያደርስ  ንቃተ ህሊና (የግንዛቤ ብቃት) እና የድርጅት ሃይል የመፍጠርና በጥራትም ሆነ በተደራሽነት ብቁ አድርጎ የመገኘት የአርበኝነት ወኔው  እጅግ ደካማ በሆነበት አውደ ፖለቲካ ሥር “ህዝብ ያሸንፋል!  ህዝብ አምርሯል ! “ ወዘተ የሚለው ከፉካሬ ቃልነት  አያልፍም ።   ለዚህ እውነትነት ደግሞ ከመጣንበት የግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን ተሞክሮ በላይ የሚነግረን ሌላ አስረጅ የለም ።

በእጅጉ ልብ የሚሰብረው ደግሞ  ህዝብ በገዥዎች እየተወሰነበትና ደጋግሞ እየተሸነፈ  “ህዝብ ይወስናልና ያሸንፋል!” እያልን ከመጣንበት እጅግ አስከፊ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት አዙሪት ለመውጣት ትርጉም ባለው ሁኔታ ላይ አለመገኘታችን ነው ። ዛሬም ለምን? በምን ሁኔታ ? እንዴት? በነማን ከየት ወደ የት?  ወዘተ የሚሉ የተጨባጭነት (የተግባራዊነት) ጥያቄዎችን እየሸሸን እና በደምሳሳው  “የህዝብ ይወስናልና ያሸንፋል!” መፈክርን በዘልማድ እያስተጋባን  ጨርሶ የትም አንደርስም ።ይልቁንም  የተፈራረቁበት ገዥዎች ሁሉ የእውቀትና የማቴሪያል መናጢ ደሃ አድርገው  ሲገዙት የኖሩትን የአገሬ ህዝብ ለባዶ ተስፋ ሰለባነት እያዘጋጀነው መሆኑን አውቀን ሳይመሽ ትክክለኛ የሆነውንና ዘላቂነት ያለውን የሥርዓት ለውጥ ፍኖት (መንገድ) መፈለግና መከተል ይኖርብናል ።

በአንድ በኩል “የለውጥ አራማጅ በምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ላይ የምር ጥያቄ በቀረበና ጠንከር ያለ ትችት በተሰነዘረ ቁጥር የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞችንና የኢህአዴግ ጥቅመኞችን አስቆጥቶ አገርን እንደ ሸክላ ፍርክስክሱን ያወጣል“ የሚል አይነት የዘቀጠ ትርክት እየተረኩ  በሌላ ደግሞ  “ህዝብ ይወስናልና ያሸንፋል !” የሚል ባዶ መፈክር ማጮህ  ጨርሶ ስሜት አይሰጥም ።

ይህን እጅግ ግዙፍና ጥልቅ ትርጉም የተሸከመ የፖለቲካ ፅንሰ ሃሳብ  አዘውትረን  የቃል ንግግሮቻችንና የፅሁፎቻችን መንደርደሪያ ፣ ማጠናከሪያና ማሳረጊያ ማድረግ ከጀመርን ግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን ሆነን ።  “መንግሥት ማለት ህዝብ ማለት ነውና የህዝብን እሮሮ እያዳመጠ መፍትሄ ይውለድ”  የሚለው የቆየ እጅግ የዋህ  ፣ ያልዘመነና  ለገዥዎች ግን ትልቅ  ማታለያ  (ማደንዘዣ) ሆኖ የቆየው  የፖለቲካ ትርክት ጊዜው አልፎበት  በለመደው አኳኋን መቀጠል ሲያቅተው ነበር አዳዲስና ብሶት ወለድ የሆኑ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን የሚያንፃባርቁ (የተሸከሙ) ፅንሰ ሃሳቦች በአንፃራዊነት ጎልተው የወጡትና በጥቂት ጊዜ ውስጥ የህዝብን ቀልብ በእጅጉ እያሳቡ የመጡት ። በተለይ ከ1960ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ።

“ፍፁማዊው የአፄ አገዛዝ ወይ በራሱ ፈቃድ ዘመኑን በሚመጥን አይነትና መጠን ሥርዓቱን  ያሻሽል ፤ ካልሆነ ይወገድ !   ህዝብ ያሸንፋል (አሸናፊ ነው) ! ድል የህዝብ ነው! ህዝብ ለነፃነትና ለፍትህ ባለቤትነቱ ቆርጦ ተነስቷልና የሚበግረው ምድራዊ ኅይል የለም! የጊዜ ጉዳይ እንጅ የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ወደ የታሪክ መዘክርነት ይለወጣል!  የነፃነትና የፍትህ ትግል በመጠን የማይተመን ዋጋ ያስከፍላል! ህዝባዊ መንግሥት ይቋቋም!  ወዘተ” የሚሉ የፖለቲካ ሃይለ ቃሎች መዘውተር ከጀመሩ ብዙ ዓመታት ተቆጠሩ። ከ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ጀምረን ስናሰላው ማለት ነው።ይህን ሁሉ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ጥያቄና ጩኸት ወደ መሬት አውርዶ የሚሸከምና ወደ ታለመለት ግብ የሚያደርስ ህሊናዊና ድርጅታዊ ሃይል ባለመኖሩ ነገሮች ሁሉ እንደማይሆን ሆኖ ።

” የዚያን ትውልድ ሙከራና ውድቀት በአገሩ ውስጥ ከእርሱ የቀደመና በተሞክሮነት የሚማርበት የዘመናዊ  የፖለቲካ አጋጣሚ  ስለአልነበረ ፣ በወቅቱ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ጥሩ አማራጭ ሆኖ ያገኘው የሶሽያሊዝም ርእዮተ ዓለም በመሆኑ እና ይህ ግን የአገሩን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ ተሳሳተ ከሚል አንፃር ማየትም ይቻላል ።

ከዚያ ወዲህ  ለምን ከስህተት አልተማራችሁም ? አሁንስ የት ናችሁ?” ተብለን ብንጠየቅ ልንመልሰው የምንችለው ምላሽ እንኳን ሊያሳምን (ሊያረካ) አሳፋሪና ለመስማትም የሰለቸ ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ የተለየ እውቀት ጨርሶ አይጠይቅም።  ምክንያቱም ፈጥቶና ገጦ የሚታይ መሪር ሃቅ ነውና ።

ካሳለፍናቸው የሁለት መንግሥታት ለውጥ አብዮቶች (1966, 1983) እና ከ1997ቱ ህወሃት/ኢህአዴግን በምርጫ ሳጥን ለማሰናበት የተደረገው እጅግ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት እንቅስቃሴ ውድቀት የሚነግረን የህዝብ ወሳኝነትና አሸናፊነት መፈክራችን እና የተግባር ማንነታችን በአሳዛኝ ሁኔታ ተለያይተው መውደቃቸውን ነው ። አሁንም በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ በመሽከረከር ላይ ነው የምንገኘው።

ህዝብን የዘመናት መከራና ውርደት አሸክመውት የኖሩትን አገዛዞች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወግድ በሚያስችለው ንቃተ ህሊና (awareness/consciousness) እና የአደረጃጀት ሰንሰለት (organizational networking) እንዲያያዝ አላገዝነውም (አላስቻልነውም) ።በሌላ አገላለፅ አይበገሬነትና ዘላቂነት ባለው የአስተሳሰብ ልእልና እና የአደረጃጀት መሠረት ላይ እንዲቆም አላስቻልነውም (አላገዝነውም) ። መፈክሩን ግን ከመቸውም ጊዜና ሁኔታ በላይ ከፍ አድርገንና እየደጋገምን እናስጮኸዋለን ።

ለዚህም ነው  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ (በአገር)  ላይ  የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ ከነበረውና አሁንም ሥልጣን ላይ ካለው ኢህአዴግ የወጡ ፖለቲከኞች “አማራጭ የማይገኝልን  የለውጥ ሂደቱ መንገድ መሪዎች እኛ ነን”ሲሉን  አማራጩ ከሰማይ  እርቆብን ስለተቸገርን “አዎ! የእናንተን ተአምራዊ የለውጥ መሪነት ከመደገፍ ሌላ አማራጭ የለንም” እያልን የራሳችንን ከልክ ያለፈ ውድቀት ያረጋገጥንላቸው ።

እያልኩ ያለሁት የኢህዴግ ተሃድሶ (reform) ፖለቲከኞች ለለውጥ ተዘጋጅተናል ሲሉን በደምሳሳው አትችሉምና አታስፈልጉም እንበላቸው አይደለም። ይህን ማድረግ ከእነሱ የባሰ የፖለቲካ ደንቆሮነት ነውና ። አዎ! እያልኩ ያለሁት በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ውሏችን ሲሆን ከእነርሱ በእጅጉ ልቆ በመገኘት ቢያንስ ግን የእነሱን የፖለቲካ ጨዋታ በሚመጥን የፖለቲካ አውድ ውስጥ እራሳችንን ማግኘት አለመቻላችንን በቅንነት ተረድተን ወደ ትክክለኛው የፖለቲካ መስመር እንግባ ነው። አዎ! እያልኩ ያለሁት የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ የከፋና የከረፋ አገዛዛቸው በኋላም የኢትዮጵያን ህዝብ እጅግ እራስን አዋራጅ (self-dehumanizing) በሚያደርግ አኳኋን የተሃድሶ ፍርፋሪያቸው ተመፅዕዋች (ሰለባ) እንዲያደርጉት ጨርሶ መፍቀድ የለብንም ነው።አዎ! እያልኩ ያለሁት  በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀው እና ከሞት አፋፍ ተመልሶ እንደ ሥርዓት የቀጠለው  ኢህአዴግ የበላይ አለቆቹን (ህወሃት/ኢህአዴግን በኦዴፓ/ኢህአዴግ) እየቀያየረ “ዴሞክራሲያዊነት ማለት ይኸው ነው” ሲለን  “ደጋፊህን እንደአሸን ያፍላልህ ፣ ነቃፊህን ወይም ተቀናቃኝክን ደግሞ ሲሆን አደብ ያስገዛልህ ካለሆነም በጠንካራው ዴሞክራሲያዊ ክንድህ ድባቅ እንድትመታው የአንተው ውቃቢ ይርዳህ”  የሚል የተቀዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ ነኝ ባይና ወደ ሥልጣን ከመጣው ፖለቲከኛ ጋር የሚገለባበጥ አድር ባይ ባለሥልጣንና ምሁር (ልሂቅ ነኝ ባይ) በሚተረማመስበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ የህዝብ ወሳኝነትና አሸናፊነት እንዲረጋገጥ ማድረግ አይቻልም ነው።

አዎ! እንደ ዜጋ በየትኛውም የአገሪቱ አቅጣጫና ክፍል በነፃነት ተዘዋውሮ ለማወቅና ለማሳወቅ ፣ የጋራ አገራዊ ራዕይንና ግብ በማይናውጥ የጋራ መርህ ላይ ለማቆም፣ የተቀናጀና ውጤት ተኮር የሆነ ስትራቴጅና እቅድ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በጠንካራና ዘላቂ  መሠረት ላይ የሚቆም ድርጅታዊ ቁመናን እውን ለማድረግ  ሲቻል ብቻ ነው “ህዝብ የለውጥ ሂደት ባለቤትና አሸናፊ ነው!”የሚለው ወርቃማ መፈክር  ስሜት ከመስጠት አልፎ የተሟላ የለውጥ ሞተር የሚሆነው ። እየታዘብን ያለነው እውነታ ግን ይህን የሚያሳይ አይደለም ።

አሁን አሁንማ ተስፋ የተጣለባቸው እጅግ ውሱን ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችም የኢህአዴግን የተሃድሶ ፍርፋሪ (ምፅዋዕት) አምነው ስለተቀበሉ ጭንቀታቸውና ፀሎታቸው ሁሉ  አንድ ሰው (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) እክል እንዳያጋጥመው ሆኗል ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚኒስትርነቱ ብቻ ሳይሆን   እንደሰው ጎጅ የሆነ እክል እንዲገጥመው ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው የአገሬ ሰው የሚመኝ አይመስለኝም ።

እንደ አሸን ከተፈለፈለውና እየተፈለፈለ ካለው   ድርጅት ተብየ መካከል “ጠቅላይ ሚኒስትሩ  እክል ቢገጥመው ጊዜያዊ መንገጫገጭ ካልሆነ በስተቀር እኛ እያለን (ድርጅታችን እያለ) አገር አትፈርስም” የሚል መጥፋቱን የታዘብ የአገሬ ሰው “ምነው አገሬ ይህን ያህል የሰው  መናጢ  ድሃ ሆንሽ ?” በሚል ምርር ብሎ ሲያዝን ማየት ህመሙ ከባድ ነው ። ቅን አሳቢና የእውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሁን ካለበት መሪር ሃቅ ጋር ለማነፃፀርና ለመረዳት ሲሞክር በእጅጉ የተደበላለቀ ስሜት ህሊናውን (የማሰቢያና የማመዛዘኛ ነፍሱን) በእጅጉ ቢያስጨንቀው  ከቶ የሚገርም አይሆንም ።

እንደ ዓለም የጤና ድርጅ የ1918 (እ ኤ አ) ሪፖርት የአገራችን በአማካይ በህይወት የመቆየት እድሜ ስሌት 65.5 እንደሆነ ያሳያል ። እናም በአንድ ትውልድ አማካይ እድሜ ውስጥ (ከ1960ዎቹ ጀምሮ) ስናስተጋባው የነበረውን የህዝብ አሸናፊነትበመሬት ላይ አውርደን ያልተገበርነውና ከመከራና ውርደት ያልተላቀቅነው ለምንና እንዴት ይሆን? ይህን የገንዛ ህሊናን ከመኮስኮስ አልፎ በእጅጉ የሚያቆስል የፖለቲካ እንቆቅልሽ  ትርጉም ባለው አኳኋን ለመረዳትና መፍትሄውን ለማበጀት ሳንችል እንዴት ይህን ያህል ዘመን ዘለቅን ? አሁንስ ከዚህ እጅግ ክፉ የፖለቲካ አዙሪት (political vicious cycle) ለመውጣት ትርጉም ያለው ሥራ ባለቤቶች ለመሆን ለምንና እንዴት አልሳካልን አለ? የሚሉትና ተያያዥ ጥያቄዎች  ዛሬም በአግባቡ ያላስተናገድናቸው ፈተናዎቻችን ናቸው ።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል !”  በሚለው ምትክ “የእኔ ወይም የእኛ ጎሳ/ዘውግያሸንፋል! ካልሆነ ግን የቀረው ይቀራል !” የሚል የለየለትና  መድሃኔቱንም ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ወደ ሆነ እብደት ውስጥ ገብተናል ። በእንዲህ አይነት እጅግ የተሳከሩና  የዘቀጡ የፖለቲካ ማንነት ከረጢቶች ውስጥ ገብተን የየራሳችን አንጡራ ነፍስ ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመኖር ያልተቸገሩትን መቶ ሚሊዮን ነፍሶች ምስቅልቅላቸውን በማውጣት ላይ እንገኛለን ። ታዲያ እንዲህ እየሆንና እያደረግን የለውጥ ባለቤትና ተጠቃሚ ህዝብን ነው! የሚለውን እድሜ ጠገብ ትርክት ማነብነቡ እንዴትና   በምን ተአምር ነው የስኬታማነታችን ማሳያ ሊሆን የሚችለው ?   በፍፁም!

በእውነት ከተነጋገርን በዚህ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ካለፈው ልክ የሌለው ውድቀታችን ተምረን የተሻለን ሆነንና አድርገን ለመገኘት አለመቻላችን የውድቀቶች ሁሉ ውድቀት ነው። እንዲያውም ይባስ ብለን ለዘመናት አስተሳስሮን የኖረውን የአብሮነት ክር (historical, social, moral and cultural fabric) እየበጣጠስን ተያይዘን ወደ ምድራዊው እንጦሮጦስ (ሲኦል) የመውረድ የፖለቲካ እብደት ውስጥ ነው የምንገኘው።

በህወሃት የበላይነት እየተመራ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ  የመከራና የውርደት ዶፍ  በህዝብ ላይ ያወርድ በነበረው  የፖለቲካ ሥርዓት እና በህዝብ አልገዛም ባይነት መካከል የነበረው ቅራኔ በነበረበት  መቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በአንፃራዊነት ይበል የሚያሰኙ ኩነቶችን (እርምጃዎችን ) መስማትና  ማየት ከጀመርን ሁለተኛውን ዓመት ያዝን ።  የእርምጃዎቹ  አዎንታዊነት  ወይም አበረታችነት  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው የመከራና የውርደት አገዛዝ  አንፃር  እንጅ ከእውነተኛ የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ሂደትና ግብ ጋር ጨርሶ የሚነፃፀሩ አይደሉም ። የመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርን ስኬታማ አድርጎ ወደ አዲስ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለመግባት የሚያስችሉ ሁኔታዎች በሌሉበት የኢህአዴግን የተሃድሶ “ትሩፋት” ዲስኩሮችና እርምጃዎች ከእውነተኛው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትይዩ ማነፃፀር የፖለቲካ ደደብነትን ካልሆነ በስተቀር ሌላ የሚነግረን የለም።

የኢህአዴግ የተሃድሶ  ፖለቲከኞች ወደ ሥልጣን ከወጡ ወዲህ የተወሰዱ እርምጃዎች እጅግ እኩይ የሆነውን የህወሃት የበላይነት ከማስወገድ ጋር ተከትለው የመጡ በመሆናቸው አዎንታዊና አበረታች ስሜት (ተስፋ) ቢያሳድሩ ተገቢና ትክክል ነው።  ዋናው ጥያቄ ግን የህወሃት የበላይነት የማስወገደ ብቻ አይደለም ።ሊሆንም አይችልም። የህወሃት እኩይና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ በእውን (በመሠረቱ) ተለውጧል ወይ የሚለውን እርግጠኛ በሆነ አወንታዊ መልስ ለመመለስ መሞከር ግልፅና ግልፅ የሆነውን እውነት ሸምጥጦ መካድ ነው የሚሆነው ። ይህ ደግሞ የለየለት የውድቀት ቁልቁለት ነው። ምክንያቱም መሪሩን እውነት ተቀብሎ ወደ ትክክለኛው የሥርዓት ለውጥ የሚወስደውን መንገድ ለመከተል ካለመፈለግ (ካለመቻል)  የበለጠ የለውጥ ሂደት ጠላት የለም።  እዚያና እዚህ ስሜትን ኮርኳሪ ዲስኩሮች በተደሰኮሩና “የተሃድሶ” እርምጃዎች በታዩ ቁጥር የትየለሌ መስዋእትነት ከተከፈለበት የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ  መንገድ በመውጣት የለውጥ አራማጅ የምንላቸውን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “የለውጥ ድል ነጋሪት” እየተቀባበልን መጎሰም “ወሳኝና አሸናፊ ነው!” እያልን በምንፎክርለት የዋህ ህዝብ መሳለቅ ነው የሚሆነው ።

ለዚህ ነው በዘለማድ የምናስተጋባውን ግዙፍና ጥልቅ ፅንሰ ሃሳብ (ህዝብ ወሳኝና አሸናፊ ነው!) ከምር ቆም ብለን ምን እያልን እንደሆነ የየራሳችን ውስጠ ህሊና መጠየቅ የሚኖርብን ።

አጥብቀንና በእጅጉ ደጋግመን የምንሰብከውን የህዝብ የለውጥ ባለቤትነትና አሸናፊነት ፖለቲካ እውነተኛነትና  ዘላቄነትነት ባለው አኳኋን ስናስኬደው ነበር ወይአሁንስ እያስኬድነው ነው ወይብለን መጠየቅ ይኖርብናል ። መልሳችን “እንዴታ/ አዎን!” የሚል ከሆነ  በምን አይነት አንቅቶ የማንቃትና ተደራጅቶ የማደራጀት ይዘት በየትኛው የአስተሳሰብና የሞራል ልዕልና ? የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ነው ለዘመናት የኖረበት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ታሪክ  ፍፃሜ እንዲያገኝ በሚያስችለው አኳኋን ያነሳሳነውና እንዲደራጅ የረዳነው የትኛውን የህብረተሰብ ክፍል ነው የሚፈልገውን የለውጥ ሂደትና ግብ ከኢህአዴ ፖለቲከኞች የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ ነፃ በሆነ የዜግነት  ማንነትና  ምንነት እንዲወስን ያገዝነው ?  የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን እየሸሹ ስለህዝብ ወሳኝነትና አሸናፊነት ሌት ተቀን ማነብነብ የውድቀት እንጅ የስኬት ማሳያ ሊሆን አይችልም።

መቸም መሪሩን የውደቀት እውነት ተቀብሎ የሚሻለውን የማድረግ ወኔው እየከዳን ተቸግረን ነው እንጅ በመሬት ላይ ያለው ፖለቲካዊ እኛነታችን እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በአዎንታዊነት መመለስ የምንችል መሆናችንን አያሳይም ወይም አይናገርም  ።

በፖለቲካ ወለድ ወንጀል በበሰበሰና በከረፋ ሥርዓት ሥር መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጨርሶ እውን ሊሆን አይችልም።አንዳንድ ወገኖች ይህን አይነት አስተያየት (የመከራከሪያ ሃሳብ) ፅንፍ የረገጠ፣ ጨለምተኝነት፣ ተስፋ ቢስነት፣ ፀረ-የለውጥ አራማጅ ፣ ወዘተ ሲሉ ማድመጥ ወይም ማንበብ የተለመደ ሆኗል ። እንደ አጠቃላይ  መርህና እንደ አጠቃላይ እውነት እንደዚህ አይነት አስተያየቶችን በደምሳሳው ማጣጣል ወይም መካድ ትክክል አይሆንም ።

አንድ እውነታ ግን ግልፅና ግልፅ መሆን አለበት ። አፍጥቶና አግጥጦ የሚታየው የሩብ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ሥርዓት አሁንም አራጊና ፈጣሪ በሆነበት የፖለቲካ አውድ ሥር ኢህአዴግ የአጋንንታዊ  መንፈሱን  አውልቆ የመልአክታንን መንፈስ የተላበሰ የለውጥ ሃይል አድርጎ በመቁጠር  እርሱን መተቸት ወይም መቃወም ፅንፈኝነትና ጨለምተኝነት ነው ብሎ መከራከር ጨርሶ ውሃ አይቋጥርም።  ለህልውናው ሲል “በንስሃ መታጠቤንና  አወንታዊ እርምጃዎችን መውሰዴን እንደ ታሪካዊ የለውጥ ገድል ተቀብላችሁ ተከተሉኝ”  ሲል “አሜን!” በሉ የሚል የፖለቲካ አመለካከት ወይ የድንቁርና ነው ወይም ደግሞ የፍርፋሪ ምፅዕዋት ምን አነሰኝ የሚል እጅግ የወረደ የፖለቲካ ሰብእና ነው ።

ትርጉም ያለው የህግ (ህገ መንግሥት) ፣ የፖለቲካ መዋቅርና አሠራር (የሦስቱም የመንግስት አካላት) ፣ የገዥው ፓርቲ (የግንባሩ) አደረጃጀትና አሠራር የለውጥ ሂደት በሌለበት ፣ አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ ልክፍተኞች እብደት በጦዘበት ፣ ተቃዋሚ የሚባሉት ወገኖች ካለመኖር የተሻሉ ባልሆኑበት  ፣ ልክ የሌለው የአድርባይነት ልክፍተኛው በሚተራመስበት ፣ ወዘተ የፖለቲካ አውድ ሥር “ህዝብ የለውጥ ሂደት ባለቤትና አሸናፊ ነው!” የሚለው የፖለቲካ መፈክር ከንግግር ማድመቂያነት አያልፍም ።

“ዶ /ር አብይ አህመድን የመሰለ የለውጥ መሪ ይደገፋል እንጅ እንዴት ይተቻል ?”የሚል ጨርሶ የዘቀጠ መከራከሪያ ማድመጥም (ማንበብም) የተለመደ ሆኗል ።የነበረውና  አሁንም ያለው አጠቃላይ የፖለቲካ ውድቀት እንደተጠበቀ ሆኖ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአደገኛ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ የፖለቲካ ማንነት በእጅጉ የተመረዘውንና የተወሳሰበውን የፖለቲካ አውድ ለመለወጥ የሚደረገውንና መደረግ ያለበትን ጉዳይ ከአንድ ወይም በጣት ከሚቆጠሩና ኢህአዴግ ጥርሳቸውን ነቅሎ ካሳደጋቸውና ካጎለመሳቸው ፖለቲከኞች ጥንካሬና ድክመት ጋር በወሳኝነት ማያያዝ ደግም  እጅግ የሚከረፋ የፖለቲካ  ድንቁርና ነው። እዚህ ላይ ነው “ህዝብ ወሳኝና አሸናፊ ነው!” የሚለው መፈክራችን  ባዶ ጩኸት ወይም የዘልማድ ፖለቲካዊ ቋንቋ የሚሆነው ።

እንኳን በኢህአዴግ ሥር ጥርሱን ነቅሎ ያደገ ፖለቲከኛ  ከደሙ ፍፁም ንፁህ ነው (የመላእክትነት ባህሪ አለው የሚባል- ከተገኘ )  ፖለቲከኛ  በዚያው በበሰሰበሰና በከረፋ ሥርዓት ይሁንታ (blessing ) መንበረ ሥልጣኑ ላይ ቢቀመጥ ከኢህአዴግ “የተሃድሶ” ፍርፋሪ ያለፈ የሚያመጣው ለውጥ  የለም። ምክንያቱም  ስለ እውነተኛ ለውጥ እያወራ ከሆነ ጥያቄው (ጉዳዩ)  መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ስንል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓትን በተሃድሶ (reform) ስም ማስቀጥል ማለት አይደለም።

 በነቃ (በእውቀት ላይ በተመሠረተ) እና በጋራ አገራዊ ራዕይና መርህ ላይ በቆመ ድርጅታዊ ሃይል ዙሪያ አለመሰለፍ ያስከተለውን መከራ፣ ውርደትና  ግዙፍ መስዋእትነት በቅጡ ተገንዝቦ ኢህአዴ በተሃድሶ ስም የሚያራምደውን የሸፍጥ ፖለቲካ ቁማር አቁሞ ወደ ትክክለኛው የመፍትሄ መንገድ በመግባት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀውን ታሪኩን እንዲያድስ ከማድረግ ይልቅ “ዶ/ር አብይ አህመድ አንድ ነገር ቢሆን የኢትዮጵያ ፍፃሜ ይሆናል” የሚል ተቀዋሚ ፖለቲከኛና ምሁር መስማት በእጅጉ ህሊና ያቆስላል። እንደ ግለሰብ ዜጋ እና እንደ ህዝብም በብርቱ ያሳፍራል ። ይህ በእጅጉ የዘቀጠ ትንታኔ አይሉት ያልተቀደሰ ሽርክናን ፍለጋ የፖለቲካ ትርክት የለውጥ ፍለጋው ሂደት ገና በእጡ ፎቀቅ ሳይል ክፉ የፖለቲካ አባዜ ሆኖብናል ። ምክንያቱም የህዝብን ወሳኝነትና አሸናፊነት ፖለቲካዊ ትርክት (political naration) ወደ መሬት አውርደንና በህሊናዊ ልእልና እና በአደረጃጀት ብቃት የእውነተኛ ለውጥ አማራጭ ሃይል ለመፍጠር ያለመቻል አሳዝኝ ውደቀት ነው።

የዴሞክራሲ ደምና አጥንት ተላብሶ ለሚቆም  የዜግነትና የአብሮነት የፖለቲካ ሥርዓት ለመታገል እስከ በረሃ ወርደው ከነበሩት እና በቅንነት የአገር ጉዳይ ያሳስበናል ከሚሉ ኢትዮጵያውያን  አድናቆትንና  ድጋፍ ከተቸራቸው (ኢዜማ በሚል ተዋህደናል ከሚሉት) ፖለቲከኞች “ዶ/ር አብይ አህመድ ካለቀለት አገር አለቀላት” የሚል የቅድመ ሞት ሙሾ ሲያወርዱ መስማት/ማየት በእጅጉ ህሊናን ያቆስላል ። ቅንና እውነተኛ ህሊና ላለው ።

የእነዚህ ፖለቲከኞች እያደር መዝቀጥን የሚያሳየን ይህ ብቻ አይደለም ።”በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ከገንዛ አገራቸውና ቀያቸው ክፋትን ከማያውቁ ህፃናት ልጆቻቸው ጋር ለመግለፅ ለሚያስቸግር ምድራዊ ሲኦል ሲዳረጉ “ምነው ድምፅችሁ አልተሰማ ?” ሲባሉ ” ለዶ/ር አብይ አህመድ (ኦዴፓ/ኢህአዴግ) ከመጋረጃው በስተጀርባ ነግረናል ። ከዚህ ባለፈ እዚያም እዚህም  ጩኸት ስለመጣ/ስለተሰማ መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አላገኘነውም ወይም ችግሩን ማባባስ ነው”ሲሉ መስማት በእጅጉ አንገት ያስደፋል ። አዙሮ የሚያይ አንገት ላለው የአገሬ ሰው ። እያደር እየዘቀጠ የመጣው የፖለቲካ ሰብእናቸው በዚህም አልቆመም ። በብዙሃን መገናኛ (ኢሳት) እና “አዲስ አበባ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ኦዴፓን ጨምሮ በጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍት ያበዱ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች የመጫወቻ ሜዳ ልትሆን አይገባም!” የሚል መሠረታዊ የመብት ጥያቄ ያነሱ ንፁሃን ዜጎችን የተቹበት መንገድና ሁኔታ “ምን ነካን ወገኖቼ ?” የሚል እጅግ መሪር ጥያቄ ይጭራል። “ወጣ ወጣና እንደሸንበቆ (እንደ መቃ) ፣ ተንከባለለ እንደ መውቀጫ” ማለት ይኸ ነው ። (የሰሞኑን የአርበኞች ግንቦት ሰባት በተለይ የአቶ ኤፍሬም ማዴቦንና የዶ/ር ብርሃኑን የቲቪ መስኮት ቃለ ምልልሶች ልብ ይሏል ) ።  

 

የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በሚቆጣጠረው የፖለቲካ አውድ ሥር ጨርሶ ፍፃሜ እንደማያገኝ  አስረግጦ ለመናገር ወይም ለመከራከር   የሚሽኮረመሙና የኢህአዴግን “የተሃድሶ ትሩፋት” ሃሳብና አካሄድ መቃወምን ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አንድ ሁለት እያልን እስኪሰለቸን ስማቸውን የምንጠቅሳቸውን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች እንደመቃወም የሚቆጥሩ የተቀዋሞ መንጋዎች (ክለቦች) በተሞላ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ  “ህዝብ የለውጥ ባለቤትና አሸናፊ ነው!” የሚለው ዘመናትን ያስቆጠረ መፈክር ባዶ ፉከራ ነው ። ይህ አይነት  ከውስጠ ህሊናችን ሳይሆን ከምላሳችን ላይ የሚባርቅ ሃይለ ቃል ፈፅሞ የትም አያደርሰንም ።  “የኢህአዴግ ጥገናዊ (ማስተካካያ) “ትሩፋቶች” ለእኛ ምን አነሱን?” ወደ እሚልና ከሰብአዊ ፍጡር በታች ወደ እሚያውለን ደረጃ እራሳችንን  ካላወረድነው በስተቀር መሪሩ ሃቅ ይኸው ነው ።

የኢህአዴግን የሸፍጥ ንሳሃ በመስማት እና  ለራሱም ህልውና  ሲል  የሚወስዳቸውን አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎች  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከፈፀመው   እጅግ የከፋና የከረፋ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጋር በማነፃፀር እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር  እየተካሄደ  እንደሆነ የሚተረከው  ትርክት እጅግ ስሜት የማይሰጥ ፖለቲካዊ ድንቁርና ነው ። እንደ ግለሰብ ዜጋም ይሁን እንደ ህዝብ  ለዘመናት ከኖሩበት መከራና ውርደት በእውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ነፃ ከመውጣት ይልቅ  የተሻለ መከራና ውርደት ያለ ይመስል የዛሬው ከትናንቱ ይሻላል የሚል አይነት አስተሳሰብ  ሰለባ ከመሆን የከፋ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የሰብእናም  ውድቀት የለም።

በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቁት የኢህአዴግ ፖለቲከኞችና ግብረ በላዎቻቸው ይህን አይነት እጅግ የወረደና የተዋረደ አስተሳሰብ በመከረኛው ህዝብ ሥነ ልቦና ውስጥ ለማስረፅ ቢሞክሩ ከቶ የሚገርም አይደለም 

በእጅጉ የሚገርመውና ህሊናን የሚያቆስለው ተደራጀሁ የሚለው የአገሬ ፖለቲከኛ እና ተመራመርኩና እየተመራመርኩ ነው የሚለው የህብረተሰብ ክፍል  የዚሁ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ሰለባ ሲሆን ነው። በዚህ አይነት እጅግ የዘቀጠ የአስተሳሰብ (የአመለካከት)  የፖለቲካ አውድ  ዙሪያ የሚሽከረከር የድርጅት አይነት እየፈለፈልን “ህዝብ የለውጥ ባለቤትና አሸናፊ ነው!” የሚለውን መፈክር  ማጮህና ማስጮህ ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም ። በዚህ አይነት የፖለቲካ አውድ ዙሪያ መሽከርከር  ለራሱ የሚበጀውን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ገና ከፍተኛና እልህ አስጨራሽ ትግል የሚጠብቀውን ትውልድ የጭንጋፍ ፖለቲካ አስተሳሰብ ሰለባ ማድረግ ነው ።የአገሬ ወጣት ትውልድ  እራሱን በበሰለ አስተሳሰብ ፣ በሞራል ልእልና እና በአገራዊ የአደረጃጅት ሰንሰለት በተያያዘ ሁኔታ ውስጥ ማግኘት ባለመቻሉ  መንበረ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ፖለቲከኞች ሁሉ በትሮይ ፈረስነት  የሚጠቀሙበት አስከፊው የፖለቲካ ምንነትና ማንነት ማብቃት አለበት ።

ይህ ወጣት ትውልድ በአካል (existence) የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፣ በፖለቲካ አስተሳሰብና መንፈስ ግን በጥንታዊው (primitive) ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደረገውን ምክንያት መመርመርና መዋጋት ይኖርበታል ። ቅን፣  የጋራ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ለሆነ ወጣት ምክንያቱም ሆነ መፍትሄው ብዙ ምርምር የሚጠይቅ አይደለም ።  የዚህ የፖለቲካ ህመም ምክንያት እንደ አሸን የፈሉና አሁንም መፍላታቸውን የቀጠሉ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ የፖለቲካ ማንነት ልክፍተኛ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው እና እንዲሁም የዚሁ  ልክፍት ሰለባ የሆኑ አክቲቪስት ነን ባዮች ናቸው ። እነዚህ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ተብየዎች “የኢትዮጵያዊነትም ሆነ የጎሳ/የብሄረሰብ ማንነት አስጠቅቶሃልና የመጀመሪያ ምርጫህና ተጋድሎህ ለጎሳህ/ለብሄረሰብህ ልኡአላዊነት ይሁን” ይሉታል ።  ይቀጥሉና “ኢትዮጵያዊነት የሚለውን እንደአስፈላጊነቱ (እንደ አመችነቱ) እያየህ እንደሚሆን ታደርገዋለህ “ብለው የዜግነቱን ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊና ሚዛናዊ የመሆን ሰብእናውን በእጅጉ ያመሰቃቅሉበታል ።  እናም እዚህ ላይ ነው ይህ ትውልድ አሁን ላለበትና ለሚመጠው ዘመን በሚመጥን አስተሳሰብና ቁመና ላይ ለመገኘት በአርበኝነት ወኔና በተጨባጭ ድርጅታዊ ብቃት ዝግጁ መሆን የግድ የሚለው ።

ይህን እጅግ የተቀደሰ ሥራ በተመለከተ ለጎሳ/ለዘር አጥንት ቆጠራ የፖለቲካ ማንነት ነጋዴዎች የሚከተለውን ግልፅና ቀጥተኛ የአቋም ማሳወቂያ መልእክት በማስተላለፍ መጀመር  አለበት ። “በልኡላዊና ዴሞክራሲያዊ  ኢትዮጵያዊነት ሥር መኖርና ሌላው ማንነቴ በጭራሽ አይጣሉብኝም ። ለምን ? ቢባል መሠረታዊው ችግር በእኩልነት ፣በመከባበር፣ በአብሮነትና በጋራ ብልፅግና የሚያኖር እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማስፈን እንጅ እናንተ እንደምትሉት የሁለት ተቃርኖ ማንነት ጉዳይ አይደለም።  ስለሆነም ወደ እንስሳነት ወደ እሚጠጋው የፖለቲካ ማንነት እየጎተታችሁ ወርቃማውን እድሜየንና ዘመኔን እንድታበላሹብኝ ጨርሶ አልፈቅድላችሁም ” በሚል የአርበኝነት መንፈስ መሞገትና መታገል ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ ።

ለዚህ ነው “ህዝብ የለውጥ ሂደት ባለቤትና አሸናፊ ነው!” የሚለው ዘመን ጠገብ የፖለቲዳ ፉከራ ወደ መሬት ወርዶ እውነተኛ ወይም ማንም ፖለቲከኛ ከዙፋን በወረደ እና በወጣ ቁጥር የማይዘውረው  የለውጥ ሞተር ሆኖ ማገልገል አለበት የሚለው በጣም ትክክል የሚሆነው።

ከጎሳ/ከዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ማንነት እናተርፋለን በሚል ክፉ ልክፍት የተለከፉ ፖለተኛና አክቲቢስት ነን ባዮች የተበላሸ የፖለካ ሥርዓትና የአስተዳር በደል በሚወልደው የነፃነትና እጦትና የኑሮ ቀውስ  የሚያሳድርበት ግራ የመጋባት (ተስፋ የመጣት)ስሜት ተጠቅመው ወደ እነሱ ወጥመድ ውስጥ በማስገባት ከጎሳየ/ከመንደሬ ውጭ ያለው ገድል ይግባ የሚል እጅግ አስከፊ ወደ ሆነ የአንድ አገር ልጆች የመጠፋፋት እብደት እንዳይከቱት የማድረግ ሃላፊነት አለበት ። መጭው ዘመን የእርሱ የሆነው ወጣት ትውልድ ።በተለይም ፊደል የቆጠረውና በመቁጠር ላይ ያለው።

እንደ ኢህአዴግ ዓይነት  እጅግ ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበከተ የአገዛዝ ቡድን አሁንም እንደ ሥርዓት በቀጠለበት ሁኔታ አንዳንድ ለራሱም ህልውና የሚጠቅሙ አወንታዊ እርምጃዎችን መውሰዱን ከትናንቱ ጭራቃዊ ተፈጥሮው ፣ባህሪውና ተግባሩ ጋር  እያነፃፀሩ “ለውጡ በህዝብ ባለቤትነትና ወሳኝነት እየተሳለጠ ነው”  ብሎ ከመቀበል የበለጠ እራስን ለሽንፈት (ለውድቀት) የማዘጋጀት አባዜ የለም።

የዚህ አይነት አደገኛ የፖለቲካ ትርክት የመጀመሪያው ሰለባ (ተጠቂ) ደግሞ ከአገሪቱ ህዝብ ከፍተኛውን ፐርሰንት የያዘውና የመጭው ጊዜ እጣ ፈንታ የተሳካ ወይም የተበላሸ መሆን በቀጥታ የሚመለከተው (የሚያሳስበው) ወጣቱ ትውልድ ነው ።

ለዚህ ነው “ህዝብ የለውጥ ሂደት ድል ባለቤት ነው!” የሚለውን ምላስ ላይ የተንጠለጠለና ወረቀት ላይ የተቀለመ ፖለቲካዊ መፈክር ወደ መሬት አውርዶ የእውነተኛ ሥርዓት ለውጥ ሞተር ማድረግ ግድ የሚለው።

ባለመታደል ሳይሆን ስለህዝብ የዴሞክራሲያዊ  ለውጥ ባለቤትነት፣ አሸናፊነትና ተጠቃሚነት አጥብቀንና አዘውትረን የምደሰኩረውን ፖለቲካዊ ዲስኩር  ወደ መሬት አውርደን  እውን ለማድረግ የሚያስችል የንቃት (የአስተሳሰብ)፣ የአድረጃጀትና የተግባር ሥራ   ላይ ባለማዋላችን  ይኸውና ተነሳን ስንል ተመልሰን ከመውደቅ ሥጋት ላይ ወድቀናል።

የበላይ አለቃ ከመቀየርና ለእራሱም ህልውና ሲል አንዳንድ ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ የሰቆቃ አገዛዙ በአንፃራዊነት የተሻሉ  የሚያስመስሉ እርምጃዎችን ከማሳየት በቀር   መሠረታዊ የፖለቲካ ተፈጥሮውን፣ ባህሪውንና አካሄዱን ያልቀየረው ሥርዓተ  ኢህአዴግ ከሞት አፋፍ ተመልሶ በተሃድሶ ስም  የለውጥ ሃዋርያነቱን ማንም አይወስድብኝም እያለን ነው ።  ታዲያ ይህ ትውልድ ከእነዚህ እና መሰሎቻቸው የፖለቲካ ጨዋታ አድማቂነት ወጥቶ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ መከባበር ፣ መተጋገዝና የጋራ ብልፅግና የሚረገገጥባትን ኢትዮጵያ መፍጠር ይኖርበታል ። ግልብ ስሜቱን ለእራሳቸው ግብስብስ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ለማድረግ የሚውረገረጉ  ፖለቲከኞችን (መሪዎችን ጨምሮ) መራቅ ብቻ ሳይሆን  በቀጥታና በግልፅ ሊፀየፋቸውና ሊታገላቸው ይገባል።

 የዚህን እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ጋግርት (ክፉ ጠንቅ) አስወግዶ ትክክለኛውን መንገድ የሚያመቻችና ተፈላጊውን ግብ እውን ለማድረግ የሚያስችል ህሊናዊና ድርጅታዊ ዝግጁነትና ብቃት በእጅጉ ከጎደለን ስለ ምን አይነት “የህዝብ የለውጥ ባለቤትነትና አሸናፊነት” እንደምናወራም አናውቅም።  

አንዳንዶቻችን  ይህን እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ በነቃ ፣ በማይናወጥ መርህ ላይ በተመሠረተ እና በተደራጀ/በተቀናጀ የትግል ሥልት መክተን ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ የጎሳ ፖለቲካ ቡድኖችን (ክለቦችን) አጠናክረን እንደ  አሸን በማራባቱ  ሥራ ላይ  ተጠምደናል። ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት ከየድርጅቶቻችን ስያሜ ጀምሮ ከፖለቲካ ቋንቋችን መዝገበ ቃላት ጠፍቶ በየጎሳችን/በየዘራችን/በየመንደራችን ስያሜ ተተክቷል ።

ሌላው ቀርቶ በኢህአዴግ እኩይ የፖለቲካ ባህሪና አጀንዳ  እና በሌሎች የጎሳ ፖለቲካ እብዶች ምክንያት ለቁም ሰቆቃና ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉትንና የሚዳረጉትን ንፁሃን ወገኖቻችንን በኢትዮጵያዊነት መጥራት ወኔው ከድቶናል ወይም ልክ የሌለው የዜግነት ማንነት ቀውስ ውስጥ ገብተናል ። በቁሙ የሰውን እርዳታ የሚማፀነውን እና የሞተን ወገን በኢትዮጵያዊነት ለመጥራት ከመፍራት ወይም ከመፀየፍ የከፋ ምን አይነት የምንነትና የማንነት ቀውስ ወይም ውድቀት ሊኖር ይችላል ? ፈፅሞ አይኖርም ።ለዚህ ነው የዚህን ትውልድ ተልእኮና ተግባር አሁን ከምናየው የእብደትና የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ በእጅጉ የተለየ መሆኑን ልብ ማለት የሚያስፈልገው።

ሌሎቻችን ደግሞ በተፎካካሪነት አውደ ፖለቲካ ስም የኢህአዴግ “የለውጥ ሃዋርያትን” እድሜና ጤና እየለመንና በመጭዎቹ ምርጫዎች የተወሰኑ መቀመጫዎችንና የሥልጣን ቦታዎችን  የሚያስገኝልንን ሁኔታ ከኢህአዴግ ጋር “እያመቻቸን” ታሪክ ሰሪዎች ሆነን የመታየት  ቅዠት ውስጥ እንገኛለን ።

ለመሆኑ ከአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ሰማንያ ፐርሰንት የሚሆነውንና  ከእጅ ወደ አፍ ለሆነ ኖሮ በማትበቃ  መሬት ላይ የመንግሥት (የወስላታ/ባለጌ ባለሥልጣናት ) ጭሰኝነት ሥር  የሚኖረውን መከረኛ ኢትዮጵያዊ  እንኳን ማንቃትና ማደራጀት በቅጡስ ጎብኝተነው እናውቃለን እንዴ ?  በነገራችን ላይ እንኳን ወደ ገጠሬው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአገሪቱ ዋና ከተማ ወጭ እንኳን እንደ ፖለቲከኛ እንደ አንድ አገር ዜጋ መዘዋወር በተቸገርንበት ሁኔታ ስለምን አይነት የህዝብ የለውጥ ባለቤትነትና አሸናፊነት ነው የምናወራው ?

ኢህአዴግ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ የመሬት ባለቤትነቱን ነጥቆ የእኩይ ፖለቲካው ታጋች  (hostage) አድርጎት የኖረው ይህኑ መከረኛ የህዝብ ክፍል ነው። ይኸውና ከሰሞኑ ደግሞ የለውጥ አራማጅ ተብየዎቹ ቁልፉ ያለው ህገ መንግሥት ተብየው ውስጥ እንደሆነ እያወቁ የመሬት ይዞታ ማሻሻያ አዋጅ የሚል በጣም እርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ጀምረዋል ። የዚህ አስቀያሚ ፖለቲካ አካሄድ ግልፅና ግልፅ ነው ።ያንን ከቁራሽ መሬቱ ጋር መሠረታዊ የዜግነት መብቱን የተገፈፈውን መከረኛ  ህዝብ በተሃድሷቸው ፍርፋሪ በመሸንገል “በል እንግዴህ የምርጫዋን ሳጠን እንዳትረሳ ። ድሮም ሆነ አሁን የምንተማመነው በአንተ ነው ። ከእኛ ቀጥሎ ደግሞ አጋሮቻችን የሆኑትን  የየጎሳህን/የየመንደርክን ፖለቲከኞች አትርሳ” ለማለት እንደሆነ ብዙ ማሰብ ጨርሶ አይጠይቅም ።ግን በእጅጉ ልብ ይሰብራል ።

ኧረ ለመሆኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ (በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ) ጉልህ ሚና የነበራቸው የመምህራን ማህበር ፣የሠራተኞች ማህበር ፣ የተማሪዎች ማህበር እና ሌሎች በርካታ የሙያና ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ማህበራት አሉ እንዴ? ካሉስ ምን እያደረጉ ነውተቀዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲ ተብየዎችስ የእንደዚህ አይነት ልዩ ልዩ አካላትን ፍላጎትና ጥቅም በቅርብ እያጠኑና እየተከታተሉ የሚበጀውን ካላደረጉ “የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር የሚለው” እጅግ ደምሳሳ የፖለቲካ ዲስኩር እንዴት ስሜት ሊሰጥ ይችላል ?

  • ታዲያ “ ህዝብ የለውጥ ሂደት ባለቤትና አሸናፊም ነው!” ስንል ምን እያልን ነው?
  • የህዝብ የለውጥ ሄደት ባለቤትነትና አሸናፊነት የት ላይ ቆሞ ነው እውን የሚሆነው ?
  • ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የምንደሰኩረው ይህ ሁሉ የማንቃትና የማደራጀት ግዙፍና ጥልቅ ክፍተት (ባዶነት) ባለበት ነው እንዴ?

ፈተናችን ዘርፈ ብዙና ከባድም ነው ። የድክመታችን (የውድቀታችን) ስፉትና ጥልቀትም እንዲሁ ። ይህን መሪር እውነት በደፋርነት አምነንና ተቀብለን በጊዜና ትርጉም ባለው አኳኋን ከገሰገስን አዎህዝብ ያሸንፋል! ከአሸናፊነቱ በረከትም በጋራ ይሳተፋል! ከዚህ በተቃራኒ ያለው የሚያስከትለው ውጤት ግልፅ ስለሆነ ማብራሪያ አያስፈልገውም።

 የመጀመሪያው ይሆን ዘንድ እየተመኘሁ አበቃሁ !

LEAVE A REPLY