ፖለቲከኞቻችን ጠዋት ጥምጥም፤ ከሰዓት ኩፊ || ያሬድ ተክለማርያም

ፖለቲከኞቻችን ጠዋት ጥምጥም፤ ከሰዓት ኩፊ || ያሬድ ተክለማርያም

ሰሞንኑ ከገዢው ፓርቲ እስከ ተቃዋሚ እና አንዳንድ አክቲቪስቶችም ጭምር ጠዋት የቄስ ጥምጥም፤ ከሰዓት ደግሞ የሼሆቹን ኩፊ አጥልቀው እና የእምነት አልባሳት እየቀያየሩ ሲያደናግሩን የፖለቲካ ድባቡን ቅድመ ምርጫ እንዲሸት አድርገውት ነበር። ምርጫ ሲቃረብ ፖለቲከኞች ቀልባቸውን ይስታሉ። ያልሆኑንት ይሆናል። ያልሰሩትን ይቀባጥራሉ። የማይሰሩትን እንፈጽመዋለን ብለው ቃል ይገባሉ። ይምላሉ፤ ይገዘታሉ።

በየትኛውም አገር የምርጫ መዳረሻ ላይ ፖለቲከኖች ትልቁ ቅዠታቸው ምን ያህል ተከታይ በቀን ውስጥ አተረፍኩ ነው። ለዚህም የማይባጥጡት ተራራ፣ የማይምሱት ጉድጓድ የለም። ከተወዳዳሪዎቻቸው በቀር የሁሉም ወዳጆች ናቸው። ትዝ ብሏቸው የማያውቁትን የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ የሚያስታውሱት በዚህ ወቅት ነው። የህብረተሰቡ መሰረታዊ ችግሮች ጎልተው የሚታያቸው እና የመፍትሔ ሃሳብም የሚፈልቅላቸው በዚህ ወቅት ነው። በሰለጠነው አለም የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የግል እጩ ተወዳዳሪዎች በከፍተኛ ገንዘብ የሚቀጥሯቸው አማካሪዎች እና የቅስቀሳ ስልት የሚነድፉላቸው ባለሙያዎች ቀጥረው ነው የሚንቀሳቀሱት። እነዚህ ባለሙያዎች የሕዝብን ስነ ልቦና በደንብ ያጠኑ፣ የመራጩን ስስ ስሜት በደንብ የሚያውቁ እና ምርጫ እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል እስትራቴጂ ወይም ስልት በመንደፍ የተካኑ፤ እንዲሁም የተቀናቃኙን ቡድን ድክመት እና ጥንካሬ በቅርብ የሚከታተሉ ስለሆኑ ውድድሩ እጅግ ከፍ ያለ እና በዲሞክራሲያው ሥርዓት ውስጥ የሃሳብ ጦርነት ልክ የሚታይበት ነው።

ዶ/ር አብይ በቅርቡ ከኢድ አልፈጥር በዓል ቀደም ብሎ በአንድ ቀን ውስጥ ጠዋት ሲኖዶስ ደጃፍ ደርሰው ከሰዓት ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር የነበራቸውን ጥሩ ቆይታ አይተንና ተደምመን ሳናበቃ በቀጣዮቹ ቀናት ሌሎች የመንግስት ሹሞች፣ ተቃዋሚዎች እና አንዳንድ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠምደው ፎቷቸውን በየድረ ገጹ ሲልኩልን ነገርየው በምርጫ ዋዜማ የሚደረግ የደጋፊ ሽሚያ መሆኑ ገባኝ። በመሰረቱ ይህ አይነቱ አካሄድ በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። ግን የኃይማኖት ተቋማትን ኢላማ ያደረገው የፖለቲከኞች የደጋፊ ሽሚያ እያደር ሌላ ችግር እንዳይፈጥር ብዙዎች ስጋታቸውን መግለጻቸው ግን አግባብ ነው። ላለፉት አስርት አመታት የመከፋፈሉ እና የእርስ በርስ ግጭቱ ሰለባ የነበሩት የኃይማኖት ተቋማት ማገገም ከጀመሩ ከአመት ያልበለጠ እድሜ ነው ያላቸው። የጎጥ ፖለቲካው እነሱንም ሲያሻክር፣ ሲያደባድብ እና ሲያተራምሳቸው ነው የቆየው። ሙሉ በሙሉ ለማገገም እና የበታተኑትን ምዕመን አሰባስበው ጠንካራ ተቋም ለመሆን ገና ጊዜ የሚፈልጉ ይመስለኛል።

በተቃራኒው ፖለቲካችን ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ቅርቃር ውስጥ የገባበት እና መከፋፈሉም ጠንክሮ የሚታይበት ወቅት ላይ ነው ያለነው። እንኳን ተቃዋሚው በውስጥ አንድነቱ ይታወቅ የነበረው ገዢው ፓርቲም በየጎጡ ተከፋፍሎ እርስ በርስ የሚፈራሩ ሰዎች የመሸጉበት ውህደት ሆኖ ነው የሚታየው። ከዲሞክራሲያዊ ባህል፣ ከግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ከሕዝብ ጉዳይ እና ከአገራዊ ዕራይ በብዙ ማይልስ እርቀት ላይ የቆሞቱ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ገዢውን ፖርቲ ጨምሮ የቆዩ በሽታዎቻቸውን እና ክሽፈታቸውን ይዘው በማገገም ላይ ወዳሉት የኃይማኖት ቤቶች መጠጋታቸው በርካታ አደጋዎችን የሚጋብዝ ይመስለኛል። ከብዙ በጥቂቱ፤

+ ካሉን አገራው ተቋማት ውስጥ በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ አድርገው እና አሰባስበው ሊይዙ የሚችሉት እነዚህ የኃይማኖት ተቋማት ናቸው። በአንድ መስጊድ ወይም በአንድ ቤተክርሲያን ውስጥ የተሰባሰቡ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ምዕመናንን ብንመለከት በጽኦታ፣ በጎሳ ወይም ብሔረሰብ ስብጥር እና በእድሜ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የያዙ ናቸው። ወያኔ ሞክሮ በእስልምና እምነት ውስጥ ያልተሳካለት እና በክርስትና እምነቶች ውስጥ ፍሬ አፍርቶ ይታይ የነበርው የዘር መቧደን አሁን እየተወገደ ይመስላል። በመሆኑም በእያንዳንዱ እምነት ውስጥ ሁሉም አይነት ሰው፤ ከሁሉም ብሔር አለ። ሁሉም እምነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ አለች። ኢትዮጵያም ውስጥ ሁሉም እምነቶች አሉ። ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት እነዚህን እምነቶች ማጥፋት የግድ ይላል።

የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ኃይማኖቱን አጥባቂ ስለሆነ እነዚህን እምነቶች ማጥፋት አይቻልም። በእነዚህ እምነቶች ጥንካሬ ውስጥ ኢትዮጵያም አብራ ትጠነክራለች። እነዚህ የእመንት ተቋማት ሲዳከሙ እና የአንባገነኖችና የፖለቲከኞች መፈጫ ሲሆኑ ኢትዮጵያም አብራ ትኮሰምናለች። እስከዛሬም የነበሩ መንግስታት የኃይማኖት ተቋማትን ጨምደው የሚይዙት እና እንዲዳከሙም የሚያደርጓቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት አመቺ ስፍራዎች ስለሆኑ ነው። እነዚህን ተቋማት በሁለት መልኩ ሲጠቀሙባቸው ቆይተዋል። የመጀመሪያው ሕዝቡ ከአምላክም በላይ መንግስትን እንዲፈራ በስብከት መልክ ፍርሃትን እና ከልክ ያለፈ ትዕግስትን በውስጡ ሲያሰርጹበት ቆይተዋል። “ሰማይ አይታረስ፤ መንግስት አይከሰስ” የሚለው የተንሻፈፈ አስተሳሰብ ምንጩም እነዚህ ተቋማት ናቸው። ሁለተኛው ደግሞ ፍርሃት ያሰረጹበት ሕዝብ አብሮ ቆሞና እንጥፍጣፊ ወኔውን ተጠቅሞ መንግስትን እንዳይፈታተን በጎጥ ጭምር እንዲከፋፈል ትልቁን ሚና ተጫውተዋል።

 ኢትዮጵያ ውስጥ ተገልጾ የማያልቅ ግፍ እና በደል በሕዝብ ላይ ሲፈጸም እነዚህ ተቋማት በአርምሞና አንዳንዳም በድርጊት ለግፍ ፈጻሚዎቹ ድጋፍ ሰጥተዋል። ገዳዮችን እየባረኩ ግፉአንን በአደባባይ እረግመዋል፤ አውግዘዋል። የሚደንቀው እነዚህ ተቋማት ህልውናቸው የተመሰረተው በሙዳየ ምጽዋት በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው። ይሁንና ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ ለቤተ እምነቶች መዋጮ የሚያደርገውን ድሃ ምዕመን ክደው ከሚመስሏቸው እና እንዲሁ ከድሃ ሕዝብ በተሰበሰበ ግብር የሚንደላቀቁና የሚሞስኑ ባለስልጣናት ስር መወሸቅን ልማድ አድርገውት ቆይተዋል። ድሃው የአገሬ ሕዝብ በራሱ ገንዘብ ባጠበደላቸው ቀሳውስት፣ ሼኮች እና የመንግስት ሹማምንት ሲበደል ቢኖርም ይህን ሁሉ ለፈጣሪው ትቶና ሁሉንም ይቅር ብሎ ነገን በደስታ ሊኖር ዛሬ ተስፋ ሰንቋል።

 ኢትዮጵያ የጉድ አገር ነች። ከፍተኛ የሞራል ልዕልና አላቸው የሚባሉ የኃይማኖት አባቶቿ እና የመንግስት ተሿሚዎቿ ከዚሁ ከድሃ ሕዝብ በምጽዋት እና በግብር ስም በተነጠቀ ገንዘብ ጥይት በማይበሳቸው እና እጅግ ውድ በሚባሉ የቅንጦት መኪኖች የሚንፈላሰሱባት፤ በተንጣለለ እና ውድ በሆኑ ቅራቅንቦዎች በተሞሉ ቪላዎች ውስጥ አለማቸውን የሚቀጩበት፤ በተቃራኒው ደግሞ ከነዚሁ ሞልቃቆች ደጃፍ የሚላስ የሚቀምስ ያረረባቸው፤ ያደፈ እና የተበጣጠቀ እራፊ እላያቸው ላይ የጣሉ ህጻናት፣ ሴቶች፣ እናቶች እና አዛውንቶች ጸሃይ፣ ዝናብ እና አቧራ እየተፈራረቁባቸው ከሰው ተራ የወጡባት አገር ነች።

 ከሕዝብ በተሰበሰበ ምጽዋት እና ግብር ጥቂቶች የማይገባቸውን ኑሮ ሲኖሩ እና ተርፏቸው ሲደፉ ሚሊዮኖች የመኖር ዋስትና ተነፍገው፣ ከሚኖሩበት ቅዮ እና ቤት በጎሰኝነት እና በሙስና ጭንቅላታቸው በተበላሸ ሰዎች ተገፍተው በየሜዳው የተጣሉበት፣ ከግብር እና ከምጽዋት በተረፈቻቸው ትንሽ ገንዘብ የቀለሷት ጎጆ በእነዚሁ እብሪተኞች በላያቸው ላይ በክረምት ሳይቀር እንዲፈርስ የሚደረግበት ጉደኛ አገር እኮ ነች ኢትዮጵያ።

 በቅርቡ የአዲስ አበባው ጊዜያዊ ከንቲባ ታከለ ኡማ አይኑን በጨው አጥቦ ያለምንም ሃፍረት እና መሸማቀቅ አዲስ አበባ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሕገ ወጥ ቤቶችን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አፈርሳለሁ፤ ፍርድ ቤትም በዚህ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባብን የሚል ዛቻ ሲሰነዝር ሰምተናል። ቤቶቹስ ሕገ ወጥ ይሁኑ። እቤቱ ውስጥ ያሉት ዜጎችስ? እነሱም ሕገ ወጥ ሆነው ተፈጥረው ይሆን ወይስ በአገሪቱ ውስጥ ስር የሰደደው እና ለዘመናት የኖረው የማህበራዊ ፍትሕ እጦት፣ የተዛባ የሃብት ክፍፍል እና የአገር ሃብት ዝርፊያ ያራቆታቸው ወገኖች። የአቶ ታከለ ደሞዝም ሆነ ድሎት ምንጩ የእነዚህ ድሆች መራቆት መሆኑን በቅጡ ያጤኑት አይመስለኝም። የሚነዱት መኪና፣ የሚኖሩበት ቤት እና ከአገር አገር የሚንቀሳቀሱበት ወጪ እና ቢሮዋቸው ጭምር በእነዚህ ድሃ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ የተገኘ መሆኑን ዘንግተውታል። ሕግ ማስከበር፣ ከተማ ማዘመን እና ጽዳት በድሃ ዜጎች መቃብር ላይ መሆን የለበትም። እነሱን ከፍ ለማድረግ እንጂ።

ኢትዮጵያ እንደ አገር፤ ሕዝቧም ከገባበት የድህነት ቅርቃር ውስጥ ሊወጣ የሚችለው የአገሪቱን ሃብት በምጽዋት፣ በግብር እና አገልግሎት በማቅረብ ስም ጠቅለው የሰበሰቡት እና የራሳቸው የምቾት ደሴት የፈጠሩት የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት ሹመኞች እና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የሚገኙት ከበርቴ ነጋዴዎች የሰበሰቡት የግፏን የላብ ውጤት እና የአገር ሃብት መልሰው ለግፉአኑ ድሃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲሰጡ ነው።

አንጀቱን ቋጥሮና ልጆቹን ቆሎና ደረቅ ዳቦ እያበላ እናንተን ጮማ ላስቆረጠ እና ፈትፍቶ ላበላችው ድሃ ሕዝብ በቂ የምግብ ዋስትና አቅርቡለት። ተርቦ ያጠገባችሁን ሕዝብ አጥግቡት። ታርዞ እና ማቅ ለብሶ በወርቅ እንድታጌጡና በውድ ልብስ እንድትደምቁ ያደረጋችውን ድሃ ሕዝብ ከለበሰው ማቅ አላቁት። በባዶ እግሩ እየተጓዘ ውድ ጫማ ላጫማችው እና በውድ መኪና እንድትንፈላሰሱና በአየር እንድትበሩ ላደረጋችው ሕዝብ ቢያንስ በቂ መንገድ እና መጓጓዣ አቅርቡለት። በበበርካታ በሽታዎች እየማቀቀ እና በቂ ሕክምና አጥቶ በተራ በሽታዎች እየሞተ እናንተን ከእነቤተሰቦቻችው አውሮፓና አሜሪካ እየላከ ላስታመማችሁ እና ነፍሳችሁን ለታደጋችሁ ሕዝብ በቂ እና ነጻ ሕክምና አቅርቡለት። የውሃ ጋን በምትባለው ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረና በውሃ ጥም እየተጠበሰ እናንተን ውድ በሆኑ መጠጦች እንድትሳከሩ እና እንድትራጩ ላደረጋችው ሕዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ውኃ እንደልቡ አቅርቡለት።

ቅዱሱ መጽሐፍ ‘የግፏን አፍ ጥልቅ ጉድጓድ ነው’ እንዳለው ከዚህ ጥልቅ ጉድጓድ ጫፍ ቆማችው ግፍ ባማረረው ሕዝብ ላይ የምትዘባበቱ ባለሥልጣናት፣ የኃይማኖት አባቶች እና ፖለቲከኞች ብታስቡበት መልካም ነው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ጉድጓዱ የቀደሙትን ግፈኞች እንደበላው ሁሉ እናትንም ይበላል። ለምትመሩት ሕዝብ ክብር እና እርህራሄ ይኑራችው። በተለይም በድህነት የሚማቅቀውን ሕዝባችውን ለምርጫ ቅስቀሳ ሳይሆን በእርምጃችሁ ሁሉ አስቡት። በየስርቻው ድሃ እያቀፉ ፎቶ ተነስቶ መለጠፍ የእናንተኑ ገጽታ ይገነባ ይሆናል እንጂ ለተገፋው ደሃ ጠብ የሚል ነገር የለውም። ይህን ስል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ አመት ቆይታን የሚያሳየውንም የፎቶ እግዚቢሺን ልብ ይለዋል።

ቅን እያሰብን፣ በጎ እየሰራን በቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY