ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍቶ የቆየው ሙስና እና የሀብት ብክነት በመንግሥት መፍትሄ ባላገኘበትና ኢኮኖሚውን በህግና በፖሊሲ መምራት ባልተቻለበት ሁኔታ ግዙፎቹ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ባለሀብት መዘዋወር እንደሌለባቸው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታውቋል።
የፓርቲው የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሱ ኃይሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ከመዛወራቸው በፊት ገዢው ፓርቲ ሀገር የሚመራበትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንደሚገባው ተናግረዋል:: መንግስት ለውድድር ክፍትና ጠንካራ ተፎካካሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መገንባት እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል፡፡
መንግስት ጠንካራ የማስተዳደር አቅምን መፍጠር ሳይችልና ተንሰራፍቶ የቆየውን ብልሹ አሰራር በቅጡ ሳያርም እንደ መብራት ኃይልና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ታላላቅ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፍ ማዘዋወር ዋጋ እንደሚያስከፍል አቶ ካሱ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡