ኢትዮጵያ ነገ ዜና || 9ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽ ሽልማት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተካሄደ:: በሰነ ሥርዓቱ 194 ተመራማሪዎችና ኢኖቬተሮች እውቅናና ሽልማት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተቀብለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 38 ወርቅ፣ 81 ብር፣ 66 ነሃስ፣ 4 የፈጠራ ስራ የምርምር ፣ 5ልዩ ተሸላሚ ይገኙበታል፡፡ ከጅብራና ጥቁር አፈር ሰልፈሪክ አሲድ በማዘጋጀት (የመኪና ባትሪ ለመሙላት የሚያስችል) የአቶ አቦሃይ ውብሸት የምርምር ስራ፤ የሲግናል ዋይፋይ የተማሪ ሃምዛ የፈጠራ ውጤት፤ ከፕላስቲክ እና ቆሻሻ ነዳጅ ማምረት የሚያስችለው የአቶ ሀባሻ ዳርጌ ድንቅ ስራዎች የወርቅ ተሸላሚ ከሆኑት ውስጥ ይገኙበታል፡፡
በብር ደረጃ ከተሸለሙት ተጠቃሾች ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ዳልጋ የሰሩት የአሜሪካ መጤ ተምች ማጥፊያ፣ የባቡር ሃዲድና ባቡር እግር መፋጨትን ከወዳደቁ ጎማዎች ማስቀረት የሚያስችል ምርምር ውጥታቸውን ያበርከቱት አቶ ዘውዴ ሞገስ በብር ደረጃ ከተሸለሙት መሀከል ይገኛሉ፡፡
ሽልማቱን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የጀመሩትን የፈጠራ ስራ ጨርሰው ማህበረሰቡን እንዲጠቅሙ በማድረግ ረገድ የጀግንነት ስራ እንዲሰሩ የፈጠራና የምርምር ባለሙያ ለሆኑ ሰዎች ጥሪ ያቀረቡ አቅርበዋል:: እናውቃለን ብለው ሰዎችን የሚያጋጩ ሰዎች ከእነዚህ ወጣቶች በቂ ትምህርት መውሰድ ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ (ዶ/ር ኢንጂ) ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው የፈጠራና የምርምር ስራዎችን ከመሸለም ባለፈ ወደ ምርት እና አገልግሎት ገብተው የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ለማድረግ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡