ሜቴክ የወሰደው 11ሄክታር ቦታ ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደረገ

ሜቴክ የወሰደው 11ሄክታር ቦታ ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሕወሓት መራሹ መንግስት ሆን ብሎ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ለማጠንከር ከመሰረታቸው ድርጅቶች መሀል አንዱ የሆነው፣ ሜቴክ ያለአግባብ የወሰዳቸው ቦታዎችን እየተነጠቀ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከወሎ ሰፈር ወደ ጎተራ በሚወስደው መንገድ፣ በተለምዶ መኮድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአምባነኑ በሜቴክ ባለቤትነት ለረዥም ጊዜ ተይዞ ሳይለማ የቆየ 11 ሄክታር መሬት፣ ወደ መንግስት መሬት ባንክ ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ከከንቲባው ጽ/ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ፤ ኢ/ር ታከለ ኡማ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 2 በሚገኘዉ በዚህ ሰፊ ቦታ ላይ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አስቀድሞ ያለ አግባብ የተወሰደውና ሳይለማ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረው ቦታ ከሜቴክ ተነጥቆ ወደ መንግስት መሬት ባንክ እንዲገባ ውሳኔ አስተላልፈዋል፡፡

ከሜቴክ የተነጠቀው ይህ መሬት የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ልማት ላይ ይውላልም ተብሏል፡፡ ሜቴክ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ በአራቱም አቅጣጫ በርካታ ቦታዎችን ነዋሪዎችን ያለ በቂ ካሳ በማፈናቀል፣በማንአለብኝነት አጥሮ ለዓመታት መቀመጡ ይታወሳል፡፡

LEAVE A REPLY