ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ታላቁና አወዛጋቢው ደራሲ አውግቸው ተረፈ በሦስት የተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ ንጉሤ ሚናስ፣ ኅሩይ ሚናስ እና አውግቸው ተረፈ በተሰኙ ስሞች፡፡ ንጉሤ ወላጆቹ ያወጡለት ሥም ነው፡፡ አጎቱ ኅሩይ ብለው ሰየሙት፡፡ “አውግቸው” መርካቶ መጻሕፍ ሲነግድ ራሱ ለራሱ እንደቀልድ ያወጣው ሥም ነው፡፡ በኋላም “አውግቸው ተረፈ”ን እንደ ብዕር ስም በመጠቀም በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡
አውግቸው ተረፈ የተወለደው በ1943 ዓ.ም በጎጃም ክ/ሀገር በቢቸና አውራጃ ነው፡፡ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በጎጃም ታላላቅ አብያተ-ቅኔያት ሲሆን፤ በ1960ዎቹ ጎጃምን ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በወር ሦስት ብር እየተከፈለው ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቅኔ ትምህርት ቤት እንደገባ በአንድ ወቅት በራሱ አንደበት እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር
“… ቀጨኔ መድኃኔዓለም ገባሁና አልስማማኝ ሲል ወደ ቅድስት ማርያም ሄድኩ፡፡ እዚያ አንድ ጓደኛዬን ስላገኘሁት ቅድስት ማርያም ዝም ብዬ ተቀመጥኩ፡፡ ቅድስት ማርያም ለአንድ ዓመት ያህል ተቀመጥን፡፡ የተማሪዎች ማደሪያ ነበር፡፡ ቅዳሴ እንማራለን ብለን ተመልሰን ገባን፡፡ እየተማርንም እያቋረጥንም ቁጭ አልን፡፡ ከዚያ ከቅድስት ማርያም አባረሩንና ለ6 ወር በረንዳ እያደርን ቁራሽ እየለመን እናድር ነበር፡፡
ከዚያ እኔ ወደ ጡረታ ሰፈር መጣሁና ከአንድ ዓይነ ስውር ጋር እሱን እየመራሁ ለሁለት ዓመት ተቀመጥኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ከሌላ ዓይነ ስውር ጋር አለቃ ነቢየ ልዑል እሚባሉ ዘንድ በወር 12 ብር ቀጠሩኝና እሳቸውን እየመራሁ ቢሮ ስለነበራቸው መጻሕፍ ቅዱስ … ያስተምሩም ስለነበር መጻሕፍ ቅዱስ እያነበብኩላቸው፣ እየጻፍኩላቸው፣ እየመራኋቸው ለአንድ ዓመት ቁጭ አልኩ፡፡” ብሏል::
ደራሲ ከመሆኑ አስቀድሞ መጻሕፍ መነገድን በጓደኛው ጥቆማ የጀመረው አውግቸው ከመጻሕፍ ንግዱ ጎን ለጎን ዘመናዊ ትምህርቱን በንጉሡ ወልደጊዮርጊስ ትምህርት ቤት በማታ ፕሮግራም ከ3ኛ ክፍል ጀመረ፡፡
በቀለም ትምህርቱ ትጉህ የነበረው ይህ ወጣት ግማሽ ቀን ሊስትሮ እየጠረገ፣ 12ኛን ክፍል በመጨረስ ዩንቨርስቲ የመግባት ዕድል ቢያገኝም የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያለ በወቅቱ የኢህአፓ እንቅስቃሴ ስለነበርና እሱም የድርጅቱ አባል በመሆኑ ከጓደኞቹ ጋር በወሰዱት “ትምህርት መማር የለብንም” በሚል የትግል አቋም አቋርጦ ወጣ፡፡
በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በአርታኢነት ተቀጠሮ ለሰባት ዓመታት ያህልም ሠርቷል፡፡ አውግቸው የአዕምሮ ህመም የጀመረው በዚህ ወቅት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የአውግቸው ተረፈ የመጀመሪያ ጽሑፍ “እነወተቴ” የሚል በ1972 ዓ.ም የጻፈው አጭር ልብወለድ ሲሆን ያልታተሙና የጠፉ ሥራዎቹን ጨምሮ ከ20 በላይ መጻሕትን የጻፈና የተረጐመ ታላቅ ጸሐፊ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ስብሐት ገብረእግዚአብሔር “አንድ ጊዜ ርዕስ የሌለው ረዥም ልቦለድ ደርሶ አንብቤው ከመጠን በላይ ተገርሜበት ነበር ግን በኋላ ጉድጓድ ጣለው፡፡” ሲል የደራሲውን ብቃትና ችግሮች በማያያዝ ገልጾት ነበር፡፡
ዛሬ ሕልፈተ ሕይወቱ የተሰማው አነጋጋሪው ደራሲ አውግቸው ተረፈ እነዚህን መጻህፍትና ታሪካዊ ጽሑፎች ለአንባቢያን አድርሶ ነበር፡-
1. ወይ አዲስ አበባ /1979/
2. ማሞ ቢጩ /1979/
3. እነ ወተቴ /1972/
4. ኒኒ በርጋጊዋ /በአዲስ ዘመን ላይ የወጣ /
5. ስሊሺና ስምንተኛው ሺ/1985/
6. ሁለት ሌሊት ከዲያቢሎስ ጋር /1985/
7. የሙኒት ምርጫ /1986/
8. እብዱ /2002/