ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘው የድሬዳዋ” ደወሌ ኮንክሪት አስፋልት የክፍያ መንገድ” ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል፡፡
ከአራት ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ መንገድ 220 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን እስከ ጅቡቲ ድንበር ድረስ የሚዘልቅ መሆኑ ታውቋል፡፡ የመንገድ ግንባታው ወጪም 85 በመቶ በቻይና ኤግዚም ባንክ የተሸፈነ ሲሆን፣ ቀሪውን 15 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሸፍኖታል ተብሏል።
እስከ ጅቡቲ የሚደርሰው ይህ መንገድ ሊያስተናግድ የሚችለውን የተሽከርካሪ ብዛትና መጠን ግምት በድጋሚ በመከለስ በአስፋልት ውፍረት መጠኑ ላይ የ5 ሴንቲ ሜትር ጭማሪ በመደረጉ ቀድሞ ከተያዘለት በጀት በላይ ወጪ እንዲወጣበት ተደርጓል፡፡
ከድሬዳዋ አንስቶ አድኑ፣ ሀርሙካሌ፣ ኢንዲቤድ፣ አይሻና ደወል ከተሞችን የሚያገናኘው መንገድ ሶስት የክፍያ ጣቢያዎች አሉት። በግራና በቀኝ ስምንት የክፍያ ቦታዎችን የሚይዙት ጣቢያዎች ስራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችል የተሸከርካሪ ሚዛን መለኪያም ተገጥሞላቸዋል።
የድሬደዋ ደዋሌ የክፍያ መንገድ በዞንና ወረዳ ከተሞች 21 ነጥብ 5 ሜትር የጎን ስፋት ሲኖረው፤ በቀበሌ ከተሞች 12 ሜትር እና በገጠር 10 ሜትር የጎን ስፋት እንዳለው በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። አስቀድሞ መስመሩ ከነበረው የጠጠር መንገድ በ100 ኪሎ ሜትር ያጠረ ሲሆን፣ ለጉዞ የሚወስደውንም ጊዜ ከ10 ሰዓት ወደ 4 ሰዓት አሳጥሮታል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ መንገዱ የሀገሪቱን የወጪ ገቢ ንግድ በማቀላጠፉ የበኩሉን ድርሻ እንደሚጫወት ግምታቸውን ከወዲሁ አስቀምጠዋል። በሀገር አቋራጩ መንገዱ የሚጓዙ ትላልቅ ተጎታች ያላቸው ተሸከርካሪዎች 250 ብር፣ ሌሎች ትላልቅ ተሸከርካሪዎች 200 ብር፣ መካከለኛ አውቶብሶች እና የጭነት ተሸከርካሪዎች 150 ብር እንዲሁም የቤት አውቶሞቢሎች 100 ብር የሚከፍሉ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም 438 ሺህ ተሸከርካሪዎችን በማስተናገድ ከአገልግሎት ዘርፉ 90 ሚሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ ተነድፏል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የክፍያ መንገድ የአዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ሰሆን፣በአሁኑ ሰአት ግንባታው እየተፋጠነ እንደሆነ የተነገረለት የሞጆ ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ስራም በቀጣይ ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡