ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ከዛሬ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቀያቸው መመለስ እንደሚጀምሩ ተነግሯል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ እነዚህን ወገኖች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡
በአማራ ክልል በመጠለያ እና ቤተዘመድ ጋር ተጠግተው የእለታዊ ድጋፍ ብቻ እየተደረገላቸው ያሉ ተፈናቃዮችን፤ ከየመጡበት ክልል አመራሮች ጋር በመወያየት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ቁጥራቸው 11 ሺህ 900 የሚሆኑት እነዚህ ተፈናቃዮች ከምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ጅማ ዞኖች እንዲሁም ቡኖ በደሌ የተፈናቀሉ ናቸዉ ተብሏል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው እነዚህን ተፈናቃዮቹ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ለመመለስ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ተፈናቃዮቹን የመመለሱ ስራ ከመከናወኑ አስቀድሞ በየአካባቢዎቹ ሰላም መኖሩ በደንብ ተረጋግጦ፣ እንዲሁም ሁኔታዎች ተመቻችተው መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሯ የመመለስ ስራው የተፈናቃዮችን ፍላጎት ባካተተ መልኩ ለማከናወን መታሰቡን አክለው ገልጸዋል፡፡
በዚህ ወቅት በብሔር ተኮር ግጭቶች የተነሳ በመላ ሀገሪቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ከኑሯቸው የተፈናቀሉ መሆኑ ይታመናል፡፡