ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ ሁለት ጊዜ አስከፊ አደጋዎች ያጋጠማቸውን የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ስያሜን ለመቀየር ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የኩባንያው የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ግሬግ ስሚዝ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ስያሜ ሊቀየር እንደሚችል የተናገሩት ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው፡፡
ኩባንያው ማንኛውንም አስተያየትና ግብዓት ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው፣ ስያሜ መቀየሩን ጨምሮ ኩባንያውን አስቀድሞ ወደ ነበረበት ቁመናው ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ወቅት ትኩረት የተሰጠበት 737 ማክስን ደህንነት በማረጋገጥ፣ ለበረራ ዝግጁ ማድረግ ከመሆኑ አኳያ በአጭር ጊዜ ስያሜ የመቀየር ዕቅድ እንደሌለውም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ በማክስ አውሮፕላኖች የደረሰውን አደጋ ተከትሎ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደዋል፡፡ እነዚህ አውሮፕላኖች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ፍቃድ አግኝተው ወደ በረራ እንደሚመለሱም እስካሁን ድረስ አልታወቀም። የ737 ማክስ
አውሮፕላኖች ከበረራ ከመታገዳቸው በፊት ኩባንያው 5 ሺህ አውሮፕላኖችን እንዲያቀርብ ከተለያዩ አገራት ትዕዛዝ የተቀበለ ቢሆንም ከአደጋው በኋላ ግን ምንም አይነት የምርቱን ትዕዛዝ አልተቀበለም፡፡