ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሜሪካ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት አመት ሁለተኛዋ ከኢትዮጵያ ቡና ገዢ አገር መሆኗ ተሰማ፡፡ ባለፈው በጀመት አመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት 4ኛ ደረጃ ይዛ የነበረችው አሜሪካ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ በመቀጠል ከፍተኛዋ የኢትዮጵያ ቡና ገዢ አገር ለመሆን እንደቻለች ነው የተነገረው፡፡
አሜሪካ በ2011 በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ 20 ሺህ 221 ነጥብ 73 ሜትሪክ ቶን መጠን ያለው ቡና መግዛቷን የገለጸው የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከተሸጠው ቡናም ኢትዮጵያ 106 ነጥብ 31 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አመላክቷል፡፡
የግብይት መጠኑም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከላከችው የቡና ምርት በመጠን 10 በመቶ በገቢ ደግሞ 16 በመቶ ይሸፍናል ነው የተባለው። ለግብይት መጠኑ ከፍ ማለት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የኢትዮጵያን ቡና በተመለከተ የተሰሩ የማስታወቂያ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የግንቦት ወር የቡና ምርት ግብይት ካለፈው በጀት አመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም 28 ሺህ 448 ነጥብ 99 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቦ፣ ከ95 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ይህም ካለፈው በጀት አመት አንጻር በመጠን የ 3 ነጥብ 82 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ የ 0 ነጥብ 70 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ነው የሚያሳየው፡፡
የኢትዮጵያን የቡና ምርት በመግዛት ሳዑዲ ዓረቢያ፣ አሜሪካ እና ጀርመን ቀዳሚውን ደረጃ የያዙ ሲሆን፣ከተላኩት የቡና አይነቶች ደግሞ ሲዳማ፣ ነቀምት እና ጅማ በተከታታይ የ31፣ 26 እና 15 በመቶ ድርሻ አላቸው።