ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከአዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ጋር በተያያዘ በትክክለኛው መንገድ የከተማዋ የባለቤትነት መብት የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የነዋሪዎቿ መሆኑን በመናገር ከታከለ ኡማ አስተዳደር ጋር በይፋ የሚሟገተው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚደርስበት ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በቅርቡ እስክንድር ነጋ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ስለሚመሰርተው “ሰናይ” የቴሌቪዥን ጣቢያ አክስዮን ሽያጭና ቀጣይ የስራ ሂደት አስመልክቶ ማብራሪያ ለመስጠት በኢትዮጵያ ሆቴልና በግዮን ሆቴል የጠራቸው ሁለት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ተከልክለዋል፡፡
ፖሊስ ጋዜጣዊ መግለጫውን አልከለከልኩም ቢልም በተለያዩ መንገዶች በተደረገው የማጣራት ስራ በክልከላዎቹ ላይ የከተማው ከፍተኛ አመራሮችና የፀጥታ ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ትክክለኛ የህዝብ ሚዲያ እስክናቋቁም ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን ሲል የተናገረው እስክንድር ነጋ ለሶስተኛ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ተዘጋጅቷል፡፡
ነገ ረቡዕ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ለሁሉም ሚዲያዎች ጥሪ ቀርቧል:: ጋዜጣዊ መግለጫውም አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ወረድ ብሎ በሚገኘው “ኢክላስ” ሕንጻ ሁለተኛ ፎቅ በሚገኘው “ጌት አማካሪዎች “ ንግድና ኢንቨስትመንት የማማከር ቢሮ መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸውልናል፡፡
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚሰራው የባለአደራው ም/ቤት የሚሰጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎችና የሚጠራቸውን ስብሰባዎች በመከልከል ከፍተኛ የመብት ጥሰት የሚፈጸመው በኢንጅነር ታከለ ኡማ ስር የሚተዳደረው የከተማው የጸጥታ ኃይል ክልከላውን አልፈጸምኩም ሲል ሲያስተባብሉ ተስተውልዋል:: ጋዜጣዊ መግለጫዎቹ የደህንነት ሰዎች ነን በሚሉ አካላት ማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ እንደ እንደሚፈጸሙ ምስክሮች ተናግረዋል::