አገሩን እንደሚወድ ህዝብ መስማት የምትፈልጉትን አውቃለሁና እንደኔም እንደናንተም ምኞት ሁሉንም በሰላም ፈትተን ወደ ቀደመው መስመራችን ተመልሰናል የሚል ዜና ይዤ ብቅ ብል ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር።
ያ’ ግን አልሆነም ! ሁላችንም ካለፈ ታሪካችን ተምረን ተሸንፈን እያሸነፍን ልዩነትን ተቀብለን አንድ በሚያደርገን በጋራ እየቆምን ወደፊት ለመጓዝ እንደተሳነን ነው።
እንደሚታወቀው ኢሳት ማለት ህንፃው (ስቱዲዮው) አይደለም፣ ሰርተፊኬቱም አይደለም፣ ባዶ ነው የሚባለው የባንክ አካውንቱም አይደለም።
ኢሳት ሃሳብ ነው፣ በልቦናም በህሊናም ያለ፤ ኢሳት ኢትዮጵያን በሚወዱ የግፍ ሥርዓትን ከእናት አገራቸው ትከሻ ላይ ለማውረድ እና በአንፃሩ ከእኩልነት መርህ ዝንፍ የማትል ዴሞክራሲያዊት አገር እውን እንድትሆን ገንዘባቸውን ዕውቀታቸውን ጊዜያቸውን ከሁሉ የላቀ ውድ ሂወታቸውን ለመገበር በተዘጋጁ ቁርጠኞች ውስጥ ሲንቀለቀል የነበረ ወደፊትም የሚኖር የትግል ስሜት ዓላማና ሃሳብ ነው።
የተነሳንለት ዓላማ እጅግ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡ አያከራክርም፤ ነገር ግን ከተሻገርነው ይልቅ ገና ያልተሻገርነው ከሞከርነው ይልቅ ያልሞከርነው እንደሚበልጥ ግን አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ በላይ ምስክር የለም። የኢሳት ተልዕኮ እና አላማ ተብሎ ሲገለፅ የኖረው የሁላችንም የጋራ ፍላጎትና አላማ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንኳን እውን ቢሆን የዲሞክራሲ ምሶሶ፤ እውነተኛ የመረጃ ምንጭ፤ ነፃ የኢትዮጵያ የህዝብ ሚዲያ ሆኖ እንዲቀጥል እንጂ የሆነ ወቅት ሩጫዬን ጨርሻለሁ ተብሎ የሚከሰምበት አላማ እንዳልነበረም ሁላችንም እናውቃለን።
ለጋራ ዓላማችን እንደ ትላንቱ በአንድ ተቋም ብንዘልቅ በእጅጉ ተመራጭ ነበር። በዓላማ ሳንለያይ በአካሄድ እና በአተያይ መለያየታችን እውን ከሆነ ግን እንደምንኖርበት አሜሪካ ያሉ የበለፀጉና ዴሞክራሲያዊ አገሮች እንኳን ከ6ሺህ በላይ ሚዲያ እንዳላቸው አስታውሰን ሁሉም በመረጠው መንገድ አገሩን ያገልግል ከማለት በቀር አማራጭ እንደሌለ ማሰቡ ጠቃሚ ይመስለኛል።
በተለይ በዛሬ ልዩነታችን ከመከራከር አልፈን ወደ ኋላ ተመልሰን አብረን ያሳለፍነውን ትላንት ጭምር ጭቃ ለመቀባት መሞከር ግን ህዝብ መናቅ ነው። ኢሳት ውስጥ ሲሰሩ የነበሩም ሆኑ ዛሬ እየሰሩ ያሉ አካላት ከኢሳት በፊትም ሆነ በኋላ በራሳቸው ስብዕና ህዝብ የሚያውቃቸው፤ እንኳን ጊዜና ገንዘብ ህይወታቸውን ለመስጠት ያልሳሱ እንደነበሩ ጠንቅቆ ለሚያውቀው ህዝብ ሌላ ትርክት ለመንገር መሞከር እራሳችንን ትዝብት ውስጥ ከመጣል የሚያልፍ እንዳልሆነም መረዳት ይኖርብናል።
ለኔ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ገብቼ የማውቀውን እውነት ሁሉ መናገር ከባድ አይደለም። በዚህ ጊዜ ባናጠፋ ግን ጠቃሚ ይመስለኛል። ከአሁን በኋላ በሁለቱም ወገን ያለውን ስራ እየተመለከተ ባለፈውም በወደፊቱም የመመዘኑን ድርሻ ለህዝብ በመተው ወደስራ ማተኮሩን እመክራለሁ።
በእኔ በኩል የምችለውን ጥረት ሁሉ አድርጌአለሁ ለጊዜው እንዳሰብኩት አልሆነም። የእኔን ድርሻ በተመለከተ ግን ትናንትም ዛሬም ሆነ ወደፊትም ሀገሬን ይጠቅማል ብዬ ባሰብኩት ነገር ሁሉ ዝንፍ ሳልል የማምንበትን ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማልል ቃል እገባለሁ።
የመጨረሻ ምክሬ በሁለቱም ወገን ያላችሁ ባልደረቦቼም ሆናችሁ ደጋፊዎች አገርን በማስቀደም በመረጣችሁት መንገድ እንቀጥላለን እስካላችሁ ድረስ ወደ ስራችሁ ከማተኮር በቀር አንዱን አፍራሽ አንዱን ገንቢ ፤ አንዱን መጤ ሌላውን ቋሚ ለማስመሰል የሚደረገው ግብዝነት አይጠቅምምና እንድታቆሙት ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ !!