ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓም
ሰናይ መልቲ ሚዲያ በበሳል ባለሙያዎችና በፕሬስ እድገት ውስጥ ከፍተኛ ሚና በተጫወቱ አንጋፋና ወጣት ጋዜጠኞች አስተባባሪነት የተቋቋመ የህዝብ የሚዲያ ነው ፡፡
ትላንት፣ ዛሬ እና ነገን እንደ-ድልድይ የሚያስተሳስር ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ የዛሬን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት አስገብቶ፤ ነገ ላይ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚረዱ አዳዲስ ፕሮግራሞች እና አቀራረቦችን ማስተዋወቅና አሁን በስራ ላይ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ክፍቶችን መሙላት ዋንኛ ዓላማዉ በማድረግ፤ ህዝብ በእኩልነት ሃሳቡን መግለጽ የሚቻልበት ሚዲያ ነው፡፡ ለዚህም ‹‹ሰናይ›› ብለን ብዙሃኑ ባለው አቅሙ የድርሻው ባለቤት ሆኖ የኔ የሚለውን ታላቅ የመልቲ ሚዲያ ተቋም ይፋ ለማድረግ እንወዳለን ፡፡
ሰናይ የህዝብ፣ ለህዝብ፣ በህዝብ የሆነ የመጀመሪያ ሚዲያ፤ እያንዳንዱ ዜጋ ያለብሔር ልዩነት፣ ያለጾታ፣ ያለ-እድሜና ክልል ገደብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰናይ ቲቪ፡-
የተሻለ ፕሮግራም የሚሰራበት የራሱ ቲቪ አክሲዮን ባለድርሻ ይሆናል፤ ምርትና አገልግሎት የሚያስተዋውቅበት ቲቪ አክሲዮን ባለድርሻ ይሆናል፤ የመረጃ፣ የቁም-ነገር እና የመዝናኛ ፍላጎትንና ጥምን የሚያረካ ቲቪ አክሲዮን ባለድርሻ ይሆናል ፡፡
የሰናይ ቲቪ የመጀመሪያው የህዝብ ሚዲያ ኔትወርክ ሲሆን በመጀመሪያ በቴሌቭዥን ሳተላይት ስርጭት ጀምሮ በመቀጠል ወደ ሬድዮ፣ ድህረ-ገፅ እና በሶሻል ሚዲያ የሚያካትት ይሆናል፡፡
በሰናይ ቲቪ እያንዳንዱ ዜጋ ካለበት ቦታ የኔ በሚለው መልኩ በቀጥታ እንዲሳተፍና እቅድ ውስጥ መካተት የሚችልበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ እውነተኛና ነፃ አማራጭ ሚዲያ ይሆናል፡፡ ድምፅ አልባ ለሆነውም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቡን በነፃነት የሚገልጽበት መንገድ ይከፈታል፡፡ የተለያዩ አመለካከቶችና መልዕክቶች የሚተላለፉበት ጭምር ይሆናል፡፡
ሰናይ መልቲ ሚዲያ የተመሰረተው እየታሰሩ፣ እየተፈቱ ለህዝብ መሰዋትነት ሲከፍሉ በቆዩ ነባር የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች አስተባባሪነት፤ ብዙሃኑ ህዝብ ሊገዛው በሚያስችል መልኩ ሰላሳ አምስት ሺህ አክሲዮኖችን በማቅርብ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው በአጠቃላይ የሰላሳ አምስት ሚሊዮን ብር ዕጣ ለሽያጭ አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሰረት፤ የአንድ አክሲዮን ዋጋ 1,000.00 (አንድ ሺህ) ብር ሲሆን፤ ዝቅተኛውና አንድ ሰው ሊገዛ የሚችለው የአክሲዮን መጠን 5,000.00 ብር (አምስት ሺህ ብር) ዋጋ ያላቸው 5 ዕጣዎች ሲሆን፤ አንድ ሰው ሊገዛ የሚችለው ከፍተኛው የአክሲዩን ብር መጠን 2,800,000.00 ( ሁለት ሚሊየን ስምንት መቶ ሺህ ብር ) ዋጋ ያላቸው 2,800 ( ሁለት ሺህ ስምንት መቶ) የአክሲዮን ዕጣዎች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ፤ማንም ወገን ከስምንት ከመቶ በላይ አክሲዮን አንዳይገዛ ገደብ ተጥሎበታል፤ ሰናይ በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር እንዳይወድቅ የሚደረግበት ማዕቀፍ ተበጅቷል፡፡
ሰናይ ቲቪ የማንኛውንም የፖለቲካ ወገንተኝነትን የማያስተናግድ፤ የግለሰቦች የፖለቲካ እምነት የማያንጸባርቅ፤ ፍጹም ገለልተኛ ሚዲያ ነው፡፡ በመሆኑም፤ ማንኛውም ሰው፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት በስተቀር፣ የአክሲዮን ባለድርሻ መሆን ይችላል፡፡ ለበለጠ መረጃ የፕሮጀክት አማካሪውን ‹‹ጌት አማካሪዎች ›› የንግድና ኢንቨስትመንት ማማከር ድርጀትን በግንባር በመቅረብ ወይም በስልክ-ቁጥር 011 8 12 12 33 / 34 በመደወል መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡