ዜና ኢትዮጵያ ነገ || በአዲስ አበባ መስተዳድር በም/ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶር ሰለሞን ኪዳኔ የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የሞተር ብስክሌት እና የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች መመሪያ ዙሪያ ሰፊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በከተማዋ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣው የትራፊክ መጨናነ፣ ፈቃድ የሌላቸው የሞተር ብስክሌቶች መብዛትና ለቁጥጥር አዳጋች መሆን ለአዲሱ መመሪያ መውጣት እንደዋነኛ ምክንያት ቀርበዋል፡፡ በዚህም በከተማ አስተዳደሩ ሁለት መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል ያሉት የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው፡-
አንደኛ የሞተር ብስክሌት ፈቃድ እና ቁጥጥር መመርያን በተመለከተ፣ በመመርያው ከተፈቀደላቸው (መከላከያ፣ የፀጥታ አስከባሪዎች ፣ የድንገተኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ፣ ፖስታ ቤት ፣ ኤምባሲዎች እና እቃ ከሚያመላልሱ) ተቋማት ውጪ፣ ከትራንስፖርት ቢሮ ፈቃድ ሳያገኝ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ተቋም ሞተር ብስክሌት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ማሽከርከር አይችልም” ብለዋል፡፡
መመሪያው የሞተር ብስክሌት አገልግሎትን ሙሉ በመሉ የሚከለክል ሳይሆን፣ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ተቋም ከትራንስፖርት ቢሮ ፈቃድና እውቅና ውጪ በከተማዋ የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር አይችልም፡፡ ለዚህም ከትራንስፖርት ቢሮ ፈቃድ በመውሰድ ማንነታቸውን/ተቋማቸውን የሚገልፅ መታወቂያ እና ዩኒፎርም በመጠቀም በከተማዋ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡
በGPS ቁጥጥር የሚደረግበት አዲሱ የሞተር ብስክሌት ሰሌዳ ቁጥጥሩን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚረዳ እና በቀላሉ የማይፈታ እንደሆነም የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን ግለሰቦች ሆኑ ተቋማት ሰሌዳውን ሲወስዱ በተቋሙ የተመዘገበው ሞተር ብስክሌት ለሚያደርሰው ማንኛውም አደጋ ተጠያቂ እንደሆኑ ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር ቀድመ ስምምነት ይፈራረማሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል በከተማዋ ኑሮአቸውን በሞተር ብስክሌት ያደረጉ ግለሰቦችም፣ በማህበር በመደራጀት በህጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመነጋገር አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ የጠቆሙት ኃላፊ፤ አዲሱ መመሪያ የወጣው የሞተር ብስክሌቶችን ከገበያ ለማስወጣት ሳይሆን ተጠያቂ መሆን ወደሚያስችል ስርአት ለማስገባት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የተጠቀሱት መመርያዎች የማይተገብሩና የአዲስ አበባ ሰሌዳ ያልለጠፉ የሞተር ብስክሌቶች ከሰኔ 30/2011ዓ.ም በኃላ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፈጽሞ መንቀሳቀስ አይችሉምም ተብሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ አዲስ በወጣው የከተማዋ የጭነት፣ የማሽነሪዎች እና ሌሎች ከባድ ተሽከርካሪዎች መቆጣጠርያ መመርያ፤ ከ3.5 ቶን በላይ የሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ማለዳው 12 ሰዓት ብቻ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡
“ከ2.5 እስከ 3.5 ቶን የሆኑ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ማለዳው 12 ሰዓት ካለው የአገልግሎት ሰዓት ፈቃድ በተጨማሪ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ቀኑ 10 ሰዓት በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ ይችላሉ” የሚለው መመሪያ ነገር ግን በስራ መውጫ እና መግቢያ ሰዓት ላይ በከተማዋ ውስጥ ፈጽሞ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አረጋግጧል፡፡
ከእነዚህ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በተጨማሪ የውሃ ስራ ፣ የቆሻሻ ማንሻ ፣ የመከላከያ ፣ የፀጥታ ተቋማት እና አትክልት ውሃ የሚያጠጡ ተሽከርካሪዎች፣ በቀን በከተማዋ ውስጥ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ መመርያው በተጨማሪም እነዚህ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይም መቆምንም ይከለክላል፡፡
ይህን መመርያው ሳያከብሩ በሚንቀሳቀሱ እና በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ በቀን በሚቆሙ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ከከባድ የገንዘብ ቅጣት እስከ መንጃ ፈቃድ መቀማት ድረስ ያሉ ቅጣቶች ይወሰዳሉያሉት ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ ከሰኔ 30 ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆነው የሞተርና የጭነት ተሽከርካሪዎች መመሪያ የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባሻገር አደጋንም ይቀንሳሉ ብለዋል፡፡