የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች || ሰኔ 15/2011 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ነገ ዜናዎች || ሰኔ 15/2011 ዓ.ም

ግብጽ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ14 አገሮች ነጻ የጉበት በሽታ ሕክምና ልትሰጥ ነው

ግብጽ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ14 የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የጉበት በሽታ ህክምና ልታደርግ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የግብጽ ጤና እና ስነ ሕዝብ ሚኒስትር ዶክተር ሃላ ዛይድ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የጉብት በሽታ በስፋት በሚከሰትባቸው 14 ሀገራት ሀገራቸው ሄፓታይተስ ሲ ለተባለው የጉበት በሽታ ህሙማን ነፃ ምርመራ እና ህክምና ልታደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኡጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ባለው የአውሮፓዊያኑ 2019 የጉበት በሽታ ስብሰባ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ እንዲህ ዓይነቱን ንግግር ያስደመጡት ዶክተር ሃላ ይህ የሕክምና ዘመቻ በዓለም ጤና ድርጅት ትብብር የሚደገፍ እንደሆነና በሶስት ወራት ውስጥ በፕሮግራሙ በትንሹ አንድ ሚሊየን ያህል ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መነደፉን ተናግረዋል፡፡

ብሩንዲ፣ ቻድ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐሊክ ኮንጎ፣ ጅቡቲ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ግብጽ በዚህ ፕሮግራም ላይ የቴክኒክ ድጋፍ፣የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የበሽታ መለያ ሶፍትዌሮችን እንዲሁም የነጻ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ተሳታፊ ትሆናለች፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ግምታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በአፍሪካ በየዓመቱ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በሄፓታይተስ ሲ እና ቢ በተባሉ የጉበት በሽታዎች ጋር በተያያ ህይወታቸውን ያጣሉ፡

በአማራ ክልል 600 ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ
የአማራ ክልል መንግስት በድጎማ እያቀረበ ያለውን የዳቦ ዱቄት ላልተገባ ጥቅም ባዋሉ ከ600 በላይ ዳቦ አምራቾች ላይ እርምጃ መውሰዱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል፡፡
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ፤ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ 2 ሺህ 728 ዳቦ ጋጋሪዎች፣ በየወሩ በድጎማ ከሚቀርበው 26ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄት 60 በመቶ የሚሆነው ለእነዚህ የዳቦ አምራቾች በትስስር የሚቀርብም፣ ቀሪው 40 በመቶ የሚሆነው የዳቦ ዱቄት ደግሞ ለመንግስት ሠራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሰራጭ ይናገራሉ።
ሆኖም በተደረገ ጥናትና ክተትል መሰረት ለዳቦ አምራቾች ከሚሰራጨው ዱቄት ከ50 በመቶ በላዩ በህገወጥ መንገድ አየር በአየር እንደሚሸጥ ተደርሶበታል፡፡ የተጋገረው ዳቦም ለተጠቃሚው ሳይደርስ ለንግድ ድርጅቶች እንደሚሸጥም ተረጋግጧል፡፡
“ለተጠቃሚዎች የሚቀርበው የአንድ ዳቦ መጠንም 150 ግራም መሆን ሲገባው አንዳንድ ዳቦ አምራቾች እስከ 85 ግራም ቀንሰው እንደሚያቀርቡም ተደርሶባቸዋል” ያሉት ኃላፊ ፣ጥናቱን መሰረት በማድረግ ከ600 በላይ ዳቦ አምራቾች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በዚህ መሰረት እነዚህ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩት ዳቦ ቤቶች፣ ከመንግስት የዳቦ ዱቄት አንዳያገኙ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ “ለመርማሪ ዓይጦች” ከፍተኛ ምስጋና ቀረበ
የቲቪ በሽታን እንዲመረ ምሩ ስልጠና የወሰዱ ዓይጦች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እያከናወኑ በመሆኑ ከፍተኛ ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡ ለአይጦቹ “ወገቡን ሰብሮ” ምስጋናውን ያቀረበው በጤና ሚኒስቴር ስር የሚተዳደረው አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት እንደሆነም ተሰምቷል፡፡
የአርማወር ሀንሰን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ገነቱ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤ ዓይጦቹ የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡ እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ በህክምናው ላይ ትልቅ እምርታ እንደሚያመጣ ተስፋ ሰጪ ምልክት ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ዓይጦቹ “ በአክታ የቲቪ በሽታን” በመመርመር ረገድ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ነው። በላብራቶሪ ውስጥ በማይክሮስኮፕ በመታገዝ ከሚደረገው ምርመራ ጋር የተቀራረበ ውጤት እየተናገሩ ሲሆን፤ 90 ከመቶ የሚሆነውን ውጤትም በትክክል መለየት ችለዋል፡፡ ለዚህም ስራቸው ምስጋና ሊሰጣቸው ግድ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት በ20 ዲዛይነሮች ይደምቃል

“የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት” ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 12:30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይን ማኅበር ኘሬዚዳንት ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃ/ጊዮርጊስ፤ በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ይህ የኢትዮጵያ ፋሽን ሳምንት ነው፡፡ ETHIOPIA FASHION WEEK – አዘጋጁ ደግሞ የኢትዮጵያ የፋሽን ዲዛይን ማኅበር ነው፡፡ አሁን በሀገራችን ለ4ኛ ጊዜ ይካሄዳል” ብለዋል፡፡

በፋሽን ሳምንቱ ከ20 በላይ ምርጥ ዲዛይነሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶችን ያካተተው ፕሮግራም የኮክቴል ምግብን ባካተተ የመግቢያው ዋጋ 500 ብር እንደሆነ አዘጋጅ ክፍሉ አስታውቋል፡፡

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በአሜሪካ ሊሸለም ነው

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ለወጣት አፍሪካዊያን አርአያ በመሆን ላበረከተው አስተዋጽኦ በአፍሪካ ህብረት የዋሽንግተን ዲሲ ፅህፈት ቤት የእውቅና ሽልማት ሊበረከትለት መሆኑ ታውቋል፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ የአፍሪካ ሕብረት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አሪካና ችሆምቦሪኮ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከኢትዮጵያም አልፎ ለመላ አፍሪካ ወጣቶች በአርዓያነት የሚጠቀስ አርቲስት በመሆኑ፣ በመጪው ሃምሌ ወር በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄደው ከአፍሪካ ሩጫ ጋር ተያይዞ በሚሰናዳው ዝግጅት ላይ ሽልማቱ እንደሚበረከትለት ገልጸዋል ።

ለድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሙዚቃው ዘርፍ ተግቶ በመስራት ለአፍሪካ ወጣቶች ያበረከተዉ አስተዋፆ የጎላ በመሆኑ የሚሰጠው እዉቅና ትርጉም ያለው መሆኑን ያመላከቱት የሕብረቱ ኃላፊ ከመድረክ ሥራዎቹ ባሻገር የበጎ አድራጎት ተግባሮቹ፣ የአፍሪካ ህብረት ዝግጅቶችን ተጠቅሞ ለማጉላትና የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ከተነሳባቸዉ ዓላማዎች መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ ውድድር ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው ፤ ለአርቲስቱ የሚበረከተው ሽልማት ወቅታዊ፣ ምክንያታዊና ለኢትዮጵያዊያንም አኩሪ እንደሆነ ገልፀዋል።

ለድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የሚሰጠው ዕውቅና ካበረከተው ተምሳሌታዊ ሚና ባሻገር ለአፍሪካ አህጉርም ኩራት መሆኑን የተናገሩት ዶክተር በጋሻው የሩጫ ውድድሩ የሚዘጋጀው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካ ሶስት ከተሞችና በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኙ ኢትዮጵያን ጋር በነበራቸው ውይይት፣ ቀኑ የኢትዮጵያ ቀን ሆኖ እንዲከበር የከተማው ከንቲባ መወሰናቸውን ተከትሎ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም “ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ” በሚል የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል።

ዓለም ባንክ ለንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውል የ8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጠ

የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ለአካባቢ ፅዳት እና ለጤና አጠባበቅ የሚውል 8 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ የብድር ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን መሀል ተፈጽሟል፡፡

የስምምነት ፕሮጅክቱ ተግባራዊ ሲሆን 3 ሚሊዮን የሚሆን በገጠር እና በከተማ የሚኖር ህዝብን የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣በአካባቢ ፅዳትና በጤና አጠባበቅ ላይ በሚሰሩ ስራዎች ተጠቃሚ ይሆናል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ፕሮጅክቱ ሙሉለሙሉ ሲጠናቀቅ በከተማ እና በገጠር የንፁህ የውሃ አቅርቦትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ መሻሻሎች እንዲኖሩ ያደረጋል፡፡ የዓለም ባንክ በኢትዮጲያ ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ ; ብድሩ በሁለተኛው የእድገት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በንጹህ ውሃ አቅርቦትና በአካባቢ ፅዳት ለሚከናወኑ ስራዎች አገሪቱ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ የሚውል እንደሆነ ጠቁመው፣ የዓለም ባንክ በሚቀጥሉት ዓመታትም በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የሚያደረገው ድጋፍ አጠክሮ እንደሚቀጥል
አረጋግጠዋል፡፡

ነገ በኦሮሚያ ከ300 ሚሊየን በላይ የችግኝ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ
እሁድ ሰኔ16 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ከ300 ሚሊየን በላይ የችግኝ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ አዲሱ ዳምጠው በክልሉ ከ300 ሚሊየን በላይ የችግኝ ጉድጎዶችን ለማስቆፈር ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ከጠዋቱ 12 ሰአት ጀምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በዚሁ መሰረት ከ2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ ስፋት ላይ የችግኝ ተከላው ይከናወናል፡፡
የችግኝ ተከላው ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን የ4ቢሊየን የችግኝ ተከላ ጥሪን ለማሳካት እና በሰኔ 16ቱ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ለማክሸፍ የተሰውና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን መታሰቢያ እንዲሆን የታቀደ መሆኑም ታውቋል፡፡
ተሳታፊዎች እያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ 40 ጉድጓድ ያዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የአየር ንብረት ለውጥን ሊታደጉ የሚችሉ፣ ለእንስሳት መኖ እና የፍራፍሬ ዝርያ ያላቸው ቢሊዮን የሚጠጉ ችግኞች ተከላ ፕሮግራም በመከናወን ላይ ነው፡፡
የትግራይ ሰማዕታት በመቀሌ እየተከበረ ነው

የትግራይ ሰማዕታት ቀን በመቀሌ ከተማ እየተከበረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን በሰማዕታት ሀውልት ላይ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

“ ጀግኖች ሰማዕታትን ስንዘክር፣ የወደቁለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ የበኩላችንን ድርሻ በመወጣት መሆን አለበት። የትግራይ ሰማዕታት ዕለትን ስንዘክር በደማቸው የተከሉትን ህገመንግስትና የፌደራል ስርዓት በመጠበቅ መሆን ይኖርበታል” ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን “ዕለቱን ስንዘክር የትግራይ ሰማዕታትን ብቻ ሳይሆን ፣በትግሉ ወቅት ህይወታቸውን የከፈሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጭምር በማሰብ ነው” ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የሰማዕታት ቤተሰቦች፣ የትግራይ የጦር ጉዳተኞች፣ ነባር ታጋዮች፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

አምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በ15 ካሜራዎች ሊቀርጹ ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል፣ በአምስቱ ላይ በ15 ካሜራዎች
የሚታገዝ ቀረጻ ሊያካሂድ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ከጨዋታዎቹ አጓጊነትና ከውጤቱ ተጠባቂነት አንጻር፣ ውጤት ሊያስቀይሩ ይችላሉ በተባሉ አምስት ጨዋታዎች ላይ ቀረጻውን አካሂዳለሁ ያለው ፌዴሬሽኑ፣ በተጨማሪም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን ችግር ለመፍታት ቀረጻው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል፡፡

በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ሶስት ካሜራዎችን ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ነው ከፌዴሬሽኑ ያገኘው መረጃ ያመላክታል። መቐለ 70 እንደርታ ከደቡብ ፖሊስ፣ ሃዋሳ ከተማ ከመከላከያ፣ ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ፣ ስሹል ሽረ ከደደቢት እና አዳማ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በአጠቃላይ በ15 ካሜራዎች ሙሉ በሙሉ ቀረጻ ይካሄድባቸዋል፡፡

LEAVE A REPLY