ጀግና?
ደግ ሰው እሺ። ትሁት ሰው፥ አዋቂ ሰው፥ አስተማሪ ሰው፥ ታታሪ ሰው፥ ቢባል ይሁን ያስማማናል። ግን አንዳንዶች ጀግንነትን ከዶ/ር አብይ ብርታት ጎራ አይመድቡትም። ይልቁንም የጀግነንት ማነስ ከድክመቱ ጋር ያያይዙታል። ጀግና አይደለም ይሉናል። ወሬ ብቻ ተባለ። እኔም ብሆን በዶ/ር አብይ ክስተት ተስፋ ሰንቄ፥ ከዚያ ፈንጥዤ፥ ደግሞም ተደናግሬ ሳበቃ የማታ ማታ የደረስኩበትን ላካፍላችሁ። ትንሽ በሞኝነቴ ታገሡኝና፥ ዶ/ር አብይን ለመግለፅ ጠቅላይ ገላጭ ቃል ቢኖር “ጀግና” ብቻ ነው። ሰውዬው በቃ ጀግና ነው ለካ። ቃሌን ጥቂት ላድርግና ለአንባቢ ህሊና ፍርዱን እተዋለሁ። ያለወትሮዬ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድን “አንተ” ማለቴ በይቅርታ ይታለፍልኝ፥ ወደፊት አይለመደኝም። በወግና በባህላችን ጀግናን “አንተ” ማለት እንግዳ ስላልሆነ ቅር እንደማትሰኙ ተስፋ አደርጋለሁ።
ኢትዮጵያ እንዴት ሰነበተች?
1ኛ/ በመጀመሪያ፡ ተስፋና ስጋት ተይዞ አብይ የኢትዮጵያ ሙሴ ሆነ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣ በሕዝብ ስነልቦና ያደረው ትልቅ ተስፋ ሲሆን፥ ካለው ፈተና ጋር በማገናዘብ የሚመጣ ስጋትም ጭምር ነበር። ያም ሆኖ ስጋት ቢኖርም በተስፋ ማነቆ ተይዞ ነበር። ተስፋና ስጋት ሞልቶን ዶ/ር አብይን እንደ ሙሴ ቆጠርን። ለዘመናት የተቆራኘንን ድቅድቅ ጨለማ የሚገፍና ወደ ብሩህ ተስፋ የሚያሻግረን ነብይ አድርገን ቆጠርነው። እኛ በእኛ ዓለም ተውጠን በተስፋና ስጋት ስንዋኝ፥ ጀግናው አብይ በሕይወቱ ተወራርዶ ራሱን አቀረበ።
2ኛ/ በመካከል ላይ፡ ተስፋና ስሜታዊ ፍቅር ተይዞ አብይ የኢትዮጵያ ንጉስ ሆነ አብይ አሕመድ በብርሃን ፍጥነት ለውጥን ሲያሽጎደጉድ ጉድ ተባለ። ትንፋሽ እንስኪያጥረን ድረስ በየማለዳው ትንግርት ማየት ጀመርን። በሕዝብ ልብ ውስጥ ገብቶ በአንድ ጀንበር ውስጥ ሀገር የወደደው መሪ ከአብይ ሌላ ይኖር ይሆን?
ተስፋና ስሜታዊ ፍቅር አንሳፎን ዶ/ር አብይን ወደንና አወድሰን ስናበቃ አብይን ንጉስ ማድረግ ብቻ ቀረን። ከስብዕናው ከሚገለጠው መልዕክትና ከልብ የመነጩት የእውነት ቃላት ተወስደን ስናበቃ፤ ጅማሬ ላይ ያለን ሳይሆን መዳረሻ እንደ ደረሰ ሰው ተሰምቶን በራሳችን ዓለም በደስታ ሰከርን። ይህ ሁሉ ሲሆን ጀግናው አብይ እንቅልፍ አጥቶ፥ በራዕይ አርቆ የሚያያትን ኢትዮጵያ በፀጋ በተሞሉ ቃላት ከመግለጥ ባለፈ፥ ወደ ዕውን ለመቀየር በሙሉ እምነት ተሞልቶ ላይ ታች የሚራወጥ ጀግና መሆኑን አየን። ለዘመኑ ያለምርጫ በሙሉ የሕዝብ ልብ በጎ ፍቃድ ሀገር የሚገዛ መሪ ሆኖ ነበር።
3ኛ/ ዛሬ ዛሬ፡ ተስፋና ግራ መጋባት ተይዞ አብይ የኢትዮጵያ መሪ ሆነ የዶ/ር አብይ አመራር እንደ ፈጣን ባቡር ሽው እያለ ሲያስገመግም ሰንብቶ፥ ኮረኮንች መንገድ ላይ ደረሰ። ያኔ መንገጫገጭ ጀመረ። ሰው ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ከፍቅር ሰመመን ሲነቃ ማጣፊያው ቸገረው፤ ዱብ እዳ ሆነበት እናም ግራ መጋባት ሰፈነ። አሁን ሁላችንም ከደመናው ላይ ወርደን መሬት ረገጥን። እስካሁን ያልተቀየረ አንድ ስሜት
ቢኖረን “ተስፋ” የሚለው ቃል ነው። ይህንን የስራ ጀግና በማየት እስካሁን ድረስ፥ በክፉም ሆነ በደጉ፥ ሕዝብ ተስፋን ፈፅሞ አልለቀቀም። ዛሬም በግራ መጋባት ዳራ ውስጥ ቢሆንም፥ ተስፋ ያንን ብዥታ ገርቶ ይዞታል። ይህ አይገርምም? አብይና ተስፋ አንለያይ አሉ። አሁን ያለንበት ጊዜ ግራ የመጋባት ስለሆነ ለዚህ ቃላት አላባክንም። ግን ይህም ስሜት ያልፋል።
ከዚህ በኋላ የሚመጣውና በዘለቄታነት የሚቀጥለው ምን እንደሆነ ከመነጋገራችን በፊት፤ ሁላችንንም ወደዚህ አዲስ ቋሚ ስፍራ የሚወስደንን ቁምነገር መረዳት እንቻል። ወደዚያ የሚወስደን ደግሞ ባለ ሦስት ኮከብ ጀግና የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስቴራችንን በአጉሊ መነፅር መመልከት ስንጀምር ነው።
ባለ ሦስት ኮከብ ጀግና
1ኛ/ የጀግናው አብይ መገለጥ፥ በዓይነት የተለየውና በቁጥር የበዛው ሀሳቡ ፍቅር ያሸንፋል ብሎ በሀገር ደረጃ ለማስተዳደር የደፈረ ማነው? በይቅርታ እንሻገር ብሎ ያወጀ ደፋር ማን አለ? እንደመር ብሎ ምድርን ያነቃነቀ ፈላስፋ ማነው? ክርስቲያኑን ሙስሊሙን አቅፎ በፍጥነት ተሳክቶለት ከጥል ወደ ፍቅር ያደረሰ ማነው? ከኤርትራ ጋር ያለውን የጥል ግድግዳ በአንድ እጁ ነቅንቆ የደረመሰ አንበሳ ማነው? ሀሳቡ ወርቅ፥n የማይታሰበውን የሚያስብ፥ ለኢትዮጵያ የሚመጥናትን ለማለም ልቦናው የበራ ጀግና ኢትዮጵያ ማፍራት መቻሏ ያስደንቃል። በአደባባይ የሚናገረው፥ በልቡ ህሊና ያገናዘበውን ሲሆን፥ ጀግንነቱ ሩቅ አሻግሮ አይቶ የመጣው ይምጣ ብሎ ሁሉን ለእኛ መዘርገፉ ነው። እኛ ዛሬ ይሆናል ብለን የምጠብቀው ተዐምር በገሃዱ ዓለም የተገለጠው ዶክተሩ መናገር ስለቻለ ነው።
አብይ የሚናገረውና የሚያስበው ግን እንዲሆን የትውልድ ርብርቦሽ የሚጠይቅ ነው። ዛሬ በምድር ላይ ያለን ሰዎች የዶክተር አብይን ሀሳብ በሙላት መገለጥ ሳናይ እንደምንሞት ማን ይንገረን? የምንደሰተው ለልጆቻችን መትረፉ እንደሆነ ብናውቅ ይበጀናል። አሁን አሁን ገደብ አበጅቶ ጋብ አለ እንጂ ያለውን ሁሉ ቢዘረግፍማ ጉድ ፈላ። መልካም ሀሳብ ማሰብ መቻል ብቻ ሳይሆን፥ ይቻላል ብሎ ለዓለም የሚያውጅ ጀግና አለን። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ምን ያህል እምነት ቢጥል ነው? ጀግና ማለት እንዲህ ነው፤ ሕዝብ ላይ ተማምኖ ህልም የሚመስልና የማይታመነውን ለመግለጥ የሚራመድ።
2ኛ/ የጀግናው አብይ ጥሪ፥ አንዱ ብቸኛ ዓላማው ዶ/ር አብይ ሀሳቡ ብዙ ቢሆንም ዓላማው ደግሞ አንድና አንድ ብቻ ነው። ያም የዲሞክራሲ አዋላጅ መሆን ነው። ይህንን ታሪካዊ ጥሪ ለአንድ አፍታም አለመዘንጋቱ ግርም ይላል። ወደ ግራና ቀኝ የሚጎትተው ቢበዛም፥ የሚያዋክበው ዳይ ቢበረክትም፥ እሱ ግን አንድ ነገር ብቻ ላይ አነጣጥሮ ይመዘገዘጋል። ትኩረቱ ዲሞክራሲን በምድረ ኢትዮጵያ ማስፈን ነው። የበዛው ሀሳቡ ወደ ተግባራዊነት የሚመነዝረው አንድ መንገድ ቢኖር፥ ያ መንገድ ዲሞክራሲ ብቻ እንደሆነ ጠንቅቆ አውቋል። አሁን ያለውን የመሪነት ስልጣን ለዚሁ አንድ ዓላማ ብቻ ላይ ያነጣጠረ ነው።
ብዙ መልካምና ውብ ሀሳብ ቢኖረውም፥ የሕዝብ ፍቅር ማዕበል ከወዲህ ወዲያ ቢንጠውም፥ እሱ ግን ዓይኑን ካነጣጠረበት አንድ ዓላማ ላይ ሊያስነሳው የሚችል ሃይል እስካሁን አልተገኘም። ተቃዋሚዎቹና ተችዎቹ ሁሉ ብዙ ምክንያት ይፈልጉበትና ያንን ውጋት የሚሰነዝሩበት፥ እሱ ራሱ ሊሞትለት ራሱን ለሰጠለት ዲሞክራሲን በመጠቀም ነው። ሁሉም ሰድቦት፥ ከፍና ዝቅ አድርጎት በየሚዲያው ሲጮህ፥ ዶክተሩ ሲተኛ ዓላማው እንዳልተዛነፈ እንዲያውቅ የሚረዳው ይመስለኛል። ሲያስብና ሲናገር ብዙ፥ ሲንቀሳቀስ ግን አንድ ብቻ። የሚገርም ጀግና ነው። በፍርሃትና በመደናገር ያንን ይዞ ሌላኛውን አይለቅም። መጀመሪያ የያዘውን ይዞ መሪውን እየመረሸ ነው። ውሎ ሲያድር እኛም ዓላማችን ዲሞክራሲ እንዲሆን አድርገን ብናግዘው ይበጀናል። ጀግናው ይጠራናል።
3ኛ/ የጀግናው አብይ ሃይል፥ ጥበብ ተኮር አመራሩ አብይ ጉልበትን ከመደገፍ ጥበብን መጠቀም መምረጡ ሌላው ጀግንነቱ ነው። የለመድነው “ዘራፍ!” የሚለውና የሚያቅራራውን ገዳይ ነው። አብይ ሰፊውን መንገድ ከመውሰድ ይልቅ፥ ማንም የማይወስደውን የጥበብ መንገድ መረጠ። የዶ/ር አብይን የፍቅር፥ የትዕግስት፥ የትህትና፥ የማስተዋል፥ የውይይት መንገድ እንደ ሞኝነት ቆጥሮ፤ ዶ/ር አብይን እንደ አቅመ ቢስ መሪ የሚያጣጥል ሰው አይፈረድበትም። ምክንያቱም በ “ቆፍጣና አፋኝና አምባገነን” መሪ ተቃኝቶ ያደገ ሰው የሚያወቀው ያንኑ ብቻ ነው።
ጫማ በማይደረግበት መንደር ለመጀመሪያ ጊዜ ጫማ መሸጥ ከባድ ነው። ምንም እንኳን ጫማው ጠቃሚ ቢሆንም፥ ለማያውቁት ጫማ ገንዘባቸውን መስጠት ይከብዳቸዋል። ኢትዮጵያ ከሁሉም ይበልጥ የሚያስፈልጋት መድሃኒት ፍቅርና ይቅርታ ነው። ግን በመሪዎቻችን ዘንድ እነዚህ እሴቶች ባዕዳን ሆነው ባደግንበት ምድር፥ ዶክተሩ ይህንን እሴቶች ሊሸጥልን ድፋ ቀና ሲል፥ መዘባበቻ የሚያደርግ ሰው ቢኖር ምን ይገርማል? የዶ/ር አብይ ጀግንነት ከጥበብ ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ዘወር አለማለቱ ነው። የሚሰራ ሰው ሁሌ ይሳሳታል። ግን በጥበብ ለሚመላለስ ሰው ጥበብ ወደ ትህትና መርታ ታስተካክልና ወደ በረከት ታደርሳለች።
የነገሩ ፍፃሜ ይህ ነው
ሰውዬውን እንደ ነፃ አውጭ መሢህ፤ ወይም በፍቅሩ ተማርከን በራሳችን ላይ የምናነግሰው ንጉሥ፤ ወይም እንደ ወትሮው የለመድነው ዓይነት አንቀጥቃጭ የሀገር መሪ እንዲሆን አድርገን ማሰብ ይብቃ። ተስፋን ከስጋት እናፋታ።
ተስፋን ከስሜታዊ ፍቅርም እናፋታ። በመጨረሻ ተስፋን ከግራ መጋባት እናፋታ። ተስፋን ከስሜታዊነት ነጥለን ስናበቃ ተስፋን ከሥራ ጋር አጋብተን ጠበቅ አድርገን እንያዝ። ተስፋን ከሥራ ጋር አዋህደን ከዶ/ር አብይ ጎን እንቁም። እርሱ ሰርቶ ምሳሌ በሆነባቸው ሥራዎች አብረነው እንሰለፍ፥ እንስራ። ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በኢትዮጵያ አምላክ የተሰጠን ታላቅ ስጦታና፥ አይተን የማናውቀው “አገልጋይ መሪ” ነው። ሰሚ ያጣ ሕዝብ ሆነን ለዘመናት ኖርን። ታዲያ ጊዜ ተቀይሮ ዘመኑ የኛ ሲሆን፥ ዶ/ር አብይን በምድራችን የሚኳትን ሰሚ ያጣ አገልጋይ መሪ እናደርገው ዘንድ አይገባምና ይህ ከእኛ ይራቅ። ሲያጠፋ ተናግረን፥ ሲስት መልሰን፥ ሲዝል ደግፈን ደጀን እንሁንለት።
የብዙ ዘመን ፀሎታችን ሲመለስልን፥ ትላንትን ረስተንና፥ በራሳችን ታብየን፤ የኢትዮጵያን አብይ ዕንቁ ሳንጠቀምበት ረጋግጠን ጥለን፥ ለበይዎችና አባይዎች ራሳችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ በማስተዋል እንጠበቅ። ኢትዮጵያን በመንደር የከፋፈለውን አጥር እንዲያፈርስልን ከመጠየቅ ይልቅ፥ እስቲ እኛ በዙሪያው ደጀን ሆነን እንቁምለት። የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ በማያሻማ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ አሳይቶ ካረካን፥ የዚህችን ኢትዮጵያ ትንሳዔ ለማድመቅ ሁሉም ወደ ሥራ ይሰማራ ዘንድ ይጠበቃል። ምክንያቱም ቀልባችንን የሳበችው ኢትዮጵያ ከዶ/ር አብይ በስጦታ የምንቀበላት ሀገር ሳትሆን፥ ከአገልጋዩ መሪያችን ጎን ቆመን በዲሞክራሲ አዋላጅነት የምትወለድ የዓለም ተስፋና የአፍሪካ ኩራት የሆነች ድንቅዬ እምዬ ናት። ለዚህ ግብአት እንዲሆን ዶ/ር አብይ የዲሞክራሲ አዋላጅነቱን በብቃት እንዲወጣ ሁሉም ራሱን የዲሞክራሲ ተማሪ ያድርግ። ፈጣሪ ይርዳው፥ እኛንም ይርዳን።
እግዚአብሔር አሰበን
እንወቅበት።
ኢሜል፡ Z@myEthiopia.com