ከተኩስ የተረፉት አቶ ላቀ አያሌው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተሾሙ

ከተኩስ የተረፉት አቶ ላቀ አያሌው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተሾሙ

ዲ ደብሊው || ትናንትና በባሕር ዳር ከተማ መፈንቅለ-መንግሥት የሞከሩ ጸጥታ አስከባሪዎች ከከፈቱት ተኩስ የተረፉት አቶ ላቀ አያሌው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተሾሙ። አቶ ላቀ በትናንትናው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የርዕሰ-መስተዳድሩ ቢሮ ለስብሰባ በተቀመጡበት የጸጥታ አስባሪዎች መለዮ በለበሱ ሰዎች ተኩስ እንደተከፈተባቸው ተናግረዋል።

«አስር ሰዓት ስብሰባ ጀምርን። አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ የተወሰኑ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ልብስ የለበሱ መጥተው ቢሯችን ላይ ተኩስ ተኮሱብን። ሁለት ጓዶቻችን እና አመራሮቻችን ሕይወታቸው አለፈ። አንድ ጓዳችን ደግሞ ቆስሎ በሕክምና ላይ ይገኛል» ብለዋል።

በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ቢሮ በነበረው ተኩስ ርዕሰ-መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ መገደላቸው ተረጋግጧል። የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥይት ቆስለው ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።

ከጥቃቱ የተረፉት እና በዶክተር አምባቸው ምትክ ክልሉን የማስተዳደር ኃላፊነት በጊዜያዊነት የተጣለባቸው አቶ ላቀ መፈንቅለ-መንግሥት የሞከሩት «አብዛኞቹ ተይዘዋል። በተኩስ ልውውጡ ሕይወታቸው ያለፈ አሉ» ሲሉ ለአማራ ክልል የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

«ጥቂት ይቀራሉ፤ በተደራጀ መንገድ በፌድራል ፖሊስ እና በክልሉ ፖሊስ ክትትል እያደረግን ነው» ያሉት አቶ ላቀ በባሕር ዳር የተሞከረው እና ዳፋው እስከ አዲስ አበባ የዘለቀውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ «እጅግ የሚያሳፍር፤አንገት የሚያስደፋ ነው» ሲሉ ገልጸውታል።

አቶ ላቀ «የክልሉ መንግሥት በክልሉ እና በባሕር ዳር ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት በቅንጅት ከሕብረተሰቡ ጋር እየሰራ ነው። ይኸንንም ለማድረግ ህብረተሰቡ ከጎናችን እንዲሆን እንዲተባበረን ጥሪ አቀርባለሁ» ብለዋል።
ካለፈው የካቲት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ክልሉን በምክትል ርዕሰ-መስተዳድርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ላቀ «የዞን የወረዳ እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ህብረተሰቡን እንዲያረጋጉ ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ እንዲያደርጉ እያደረግን ነው» ሲሉ ተደምጠዋል።

LEAVE A REPLY