“ጀኔራል ሠዓረ ስለሞተ ኢትየጵያ አትፈርስም፤ እኛ ጠንክረን ከቆምን ኢትዮጵያን አንድ እናደርጋታለን” መአሾ ሠዓረ
“የአባቴ ደም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው” መዐዛ አምባቸው
“የሟቾቹ (የብ/ጀ/ አሳምነው ጽጌ፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ ሌ/ጀ ሠዓረ መኮንን፣ የአቶ ምግባሩ ከበደ፣ የአቶ እዘዝ ዋሴ፣ የሜ/ጀ ገዛኢ አበራ) ሞት የእኛ ሞት ነው” የላሊበላ ሕዝብ
እጅግ የሚያጽናኑ ንግሮች ናቸው፡፡ ከበረታ ልብ የሚፈልቁ ጥሩ አንጀት አርስ የውኃ ምንጮች፡፡ በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን ተስፋ ማየት ይገባናል፡፡ ጨለማን ማወቃችን ብርሃንን ለማድነቅ፣ ለመውደድ፣ በብርሃን ለመጠቀም ሊያበቃን ይገባል፡፡ እነዚህ ንግግሮች ጭልጭል ማለት የጀመረችውን ተስፋ ብሩኅ የማድረግ አቅማቸው ታላቅ ነው፡፡ የቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ልጆች ሁላችን በእነዚህ ተስፈኛ ፍልስፍናዎች እንታነጽ፡፡
የሰሞኑን ቅስፈት ከዚህ ድባብ ውጭ ኾኖ ማየት አገር ያፈርሳል፡፡ እገሌ ወእገሌ ሳይባል ሞቱ የጋራችን ነው ብሎ ማሰቡ ይበጃል፡፡ ይህ ማለት ጉዳዩ ተደፋፍኖ ይቅር ማለት አይደለም፡፡ ያጣናቸውን አጥተናል፣ በምንም ሁኔታ ትናንት ዛሬን አይኾንም፡፡ ገለልተኛ የኾነ አካል አጣርቶ ከሁላችንም ግምታዊ እሳቤ ነፃ እስኪያወጣን ድረስ መታገስ ይኖርብናል፡፡ ባይኾን መንግሥት በገለልተኛ ወገን ነገሩ እንዲጣራ በሩን መክፈት እንዳለበት መወትወት ይገባል፡፡ ከርችሜ እቀራለሁ ካለ ከመጠርጠር ነፃ ሊኾን አይችልም፡፡ ገና በማለዳ የከፈታቸው የጥርጣሬ ፍንጮች ሽንቁሮች ሳይኾኑ በር አክለዋልና፡፡
ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ በአንድ ሠዓት ሦስት ቦታ እንደተገኘ በሚነገር ምትሐታዊ ምሥክርነት የሴራ መዋቅሩ አልጸናም፡፡ ፲፩ ሠዓት ላይ ክልል ምክር ቤት ግራውንድ ላይ የታየው ሰውዬ ከመቅጽበት እንግዳ ማረፊያ (GUEST HOUSE) በሚባለው ቦታ ይታያል፡፡ እዚህም ሲታይ ደግሞ ዐየነው የሚሉት ሰዎች አንዱ ኹለተኛ ፎቅ ላይ ሌላው አንደኛ ፎቅ ላይ እያሉ በግድ እመኗቸው ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ በአንደኛው እማኝ ቃል መሠረት “ወንበር ቀይሩልኝ” ብሎ ከካፌ ወንበር እስከማስመጣት ጊዜ የነበረውን ሰው እንዴት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ልባችን ይጠርጥረው? በእርግጥ ብትንትኑ የወጣውን እማኝነት ከሥር ከሥሩ እንደ ውኃ የሚያፈልቀውን ብዙኀን መገናኛ ሳያመሰግኑ ማለፍ ንፉግነት ይኾናል፡፡
የማይበጠሰውን የኢትዮጵያዊነት ማሠሪያ ገመድ መቁረጥ አይቻልም፡፡ በጅምላ እስር ሀገር አታተርፍም፡፡ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዘመን ኹለተኛው ዙር የአፈሳ እስር ተጀምሯል፡፡ ማሰርና መተሳሰር ለኢትዮጵያ መፍትሔ ኾኖ አያውቅም፡፡ ለዚህም ከእኛ በላይ ምስክር ከየትም አይመጣም፡፡ ደግሞስ ሕዝብ መንግሥትን የመጠርጠር መብት የለውም ያለው ማን ነው? የተጠረጠረ ሁሉ የሚታሰር ከኾነ አሳሪውም ታሳሪ መኾን አለበት፡፡ በአጭሩ አንደኛው ታሳሪ መንግሥት ይኾናል ማለት ነው፡፡ እገሌን አትንኩብኝ በሚለው ዘመቻ ብቻ መገላገል አይቻልም፡፡ ማንኛውም ወገን እውነቱ እስኪጣራ ድረስ ደጋፊ እንዳለው ሁሉ ተቃዋሚም እንዳለው ሊታወቅ ይገባል፡፡ እኔን ብቻ ስሙኝ ሲያጠፋን ኖረ እኮ! የተጀመረው የጅምላ እስር ውጤቱ ክፉ ሊኾን ይችላል፡፡ መቆሳሰሉ ከቀጠለ ከመቼውም የከፋ እልቂት ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ ይህ ሰይጣናዊ መንገድ ጊዜ እየጠበቀ እንጅ ከደጃችን ቀርቧል፡፡ ጥቂት የሚለኩስለት እስኪያገኝ ነው የሰይጣን ትዕግስቱ፡፡ ከዚህ ግርግር ለመውጣት መንገዱ መተሳሰር ሳይኾን ሦስት ዕድል አለን፡፡
አንደኛው የውሾን ነገር ያነሣ ውሾ ብሎ ነገሩን አዳፍኖ መርሳት፡፡ ይህ ሲኾን ማንም ወደማንም ጣት አይቀስርም፡፡ የሞትነውም እኛ የገደልነውም እኛ የሚለው እሳቤ ቦታውን ይይዛል፡፡ እኛ እኛን አንከስም፣ እኛ እኛን አንወቅስም፣ እኛ እኛን አንጠረጥርም፣ እኛ በእኛ ላይ ቂም አንይዝም፣ እኛ ለእኛ ጠላት አንኾንም ብሎ መዝገቡን መዝጋት፡፡
ኹለተኛው መንገድ ደግሞ ገለልተኛ አጣሪ አካል ሰይሞ ጉዳዩ ተመርምሮ እውነታው ሲታወቅ መጠየቅ ያለበት ወገን በሕግ እንዲጠየቅ ማድረግ፡፡ እስከዚያው ድረስ መንግሥት ጠረጠርኋቸው ያላቸውን እና በየ እስር ቤቱ የጎሰጎሳቸውን መልቀቅ ሲኖርበት ከተጨማሪ እስርም መታቀብ፡፡
ሦስተኛው ፍጹም ይቅርታ እንዲወርድ የጋሞ ሽማግሌዎችን የቅርብ ታሪክ መልሶ ማቋቋም፡፡ ይቅርታ የሁሉ መድኃኒት ነውና ከላይኞቹ ይህኛው የበለጠ ይመረጣል፡፡ በዚህም ኮናኝ እና ተኮናኝ ሳይኖር ያለጠባሳ ቁስሉን ማሻር ይቻላል፡፡ እግዚአብሔርም ደስ ይሰኝበታል፡፡ ለዚህ የተመረጡት ሽማግሌዎቹም ኾኑ ሌሎች ተጨምረው በአስቸኳይ መላ ሊፈልጉ ይገባል፡፡ መንግሥት ያልመረጣቸው አዳዲሶችም በራሳቸው ቢነሣሱ እንዴት በተመሰገነ!
ምንም እንኳ የሁሉም ሟቾች ቤተሰቦች ሁላችንም ብንኾንም የቅርብ የኾኑቱ እንደዚህ ያለ የሚያስማማ እና የሚያሳርፍ ቃል ከተናገሩ በእርሱ ላይ መረማመድ ብዙ አይፈትንም፡፡ ወደሚበጀን ፍቅርና ሰላም እንገስግስ፡፡ አይርፈድብን እንቅሳቀስ፡፡ ፍቅር ሰይጣንን መግደያ ትጥቃችን ነው፡፡ እናም የሟች ቤተሶብችን ቃል አናርክስ፡፡ የነገሩንን ሰምተን እንቀደስ፡፡ በሉ ወደ ፍቅር አምባ እንድረስ፡፡ በምግባር ፈረስ፡፡ ልባችንን አሳምነን እንዘዝ፡፡ የሰላምን መንገድ እንያዝ፡፡ ሞተ ከመይሥዓሮ ለሞት እንበል፡፡ ይግዛን የፍቅር ማዕበል፡፡