1. የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሌትናንት ጀኔራል ሰዓረ መኮንንና የጡረተኛው ሜጀር ጀኔራል ገዛዒ አበራ ቀብር ስነ ሥርዓት ዛሬ በመቀሌ ቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስትያን ተፈጽሟል፡፡ ቀብሩ የተፈጸመው በሰማዕታት መታሰቢያ የሐዘን ስነ ሥርዓት ከተካሄደ በኋላ ነው፡፡ ለሟቾቹ መድፍ ተተኩሶላቸዋል፡፡ በስነ ሥርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካዔል፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡
2. የሟቾቹ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን፣ አማካሪያቸው አዘዝ ዋሴና ዐቃቤ ሕጉ ምግባሩ ከበደ ቀብር ዛሬ በባሕር ዳር ቅዱስ ገብርዔል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ ቀን ላይ በተካሄደው የአስከሬን ሽኝት ስነ ሥርዓት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ባለፈው ቅዳሜ አሜሪካ እንደደረስኩ መጀመሪያ የሰማሁት የስልክ መልዕክት ስለ 3ቱ የክልላችን ባለስልጣናት መገደል ነበር በማለት ሳግ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡ ለቀብሩ የፌደራልና ክልሎች ከፍተኛ ባለ ስልጣናትና የሱዳንና ኤርትራ ልዑኮች ተገኝተዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የጀኔራል አሳምነው ጽጌ ቀብር ዛሬ በላሊበላ ከተማ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡ የከተማዋና አካባቢው ሕዝብ ከትናንት ጀምሮ በነቂስ በመውጣት የጄኔራሉንና የሌሎችንም ሟች ባለሥልጣናት ስም እየጠራ በሽለላና ፉከራ ሐዘኑን እንደገለጸ DW ዘግቧል፡፡
3. ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን መዝጋቷ በቀን 4.5 ሚሊዮን ዶላር ያሳጣታል ብሏል- ኔት ብሎክስ የተሰኘው የሀገራትን ኤንተርኔት መቋረጥ የሚከታተለው ዐለም ዐቀፍ ድርጅት፡፡ ከቅዳሜ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ የተቋረጠው ኢንተርኔት ዛሬም አልተለቀቀም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የንግግር ነጻነትን የሚያበረታቱ ርምጃዎችን መውሰድ በጀመሩ ልክ በዐመቱ ኢንተርኔት ማቋረጣቸውን እንደሚያወግዙት የድርጅቱ ዋና ሃላፊ አልፕ ቶከር ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡ ዜጎች በሰሞኑ የባለ ሥልጣናት ግድያ በቂ መረጃ አግኝተው ሐዘናቸውን መግለጽ ሲገባቸው፣ የመረጃ ምንጮችን መዝጋት ክብራቸውን ማሳጣት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
4. ትናንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ስንታየሁ ቸኮልና ሌሎች 4 አባላት ዛሬ አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡ ሌሎቹ 4 ተጠርጣሪዎች መርከቡ ሃይሌ፣ በሪሁን አዳነ፣ ጌዲዮን ወንደወሰንና ማስተዋል አረጋ እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ባለፈው ቅዳሜ ባሕር ዳር በተሞከረው መፈንቅለ መንግሥትና ግድያ ጋር በተያያዘ በጸረ ሽብር አዋጁ አግባብ በወንጀል እፈልጋቸዋለሁ- ብሏል ፖሊስ፡፡ ለምርመራም 28 ቀን እንዲሰጠው ጠይቆ እንደተፈቀደለት የተለያዩ የሀገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል፡፡ በተያያዘ ዜና የባላደራው ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ከጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በግል የተወያየሁበት አጋጣሚ የለም- ሲል ለቢቢሲ አማርኛ ተናግሯል፡፡
5. ፖሊስ ዛሬም በአዲስ አበባ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር እያዋለ መሆኑን DW የከተማይቱን ነዋሪዎች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብንና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ ፓርቲ/አዜማ አንድ አንድ አባል እንደታሰረባቸውም ጠቁሟል፡፡ ፓርቲዎቹ ግን እስካሁን ስለ ዘገባው ያሉት ነገር የለም፡፡ ጸጥታ ሃይሎች በከተማዋ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ እንደሆነ የዐይን እማኞች ገልጸዋል፡፡
6. ዐለም ዐቀፉ የግጭት ተቋም ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ትናንት ባወጣው አጭር ሪፖርት ኢትዮጵያ በሰሞኑ የባለ ሥልጣናት ግድያ ወደባሰ ፖለቲካዊ ቀውስ መግባቷን አውስቷል፡፡ የአሁኑን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማረገብ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መውሰድ ካለባቸው ርምጃዎች መካከልም ጦር ሠራዊቱን ለፖለቲካ ዐላማ ማስፈጸሚያነት አለመጠቀም እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ፖለቲከኞች ግጭትን ከሚያባባሱ ንግግሮችና ድርጊቶች እንዲቆጠቡም መክሯል፡፡